በአሜሪካ ግዛቶች የሰዓት እላፊ አዋጅ ቢጣልም በተቃውሞዎች እየተናጡ ነው

በአሜሪካ እየተደረጉ ያሉ ተቃውሞዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ነጭ ፖሊስ አንገቱ ላይ ተንበርክኮበት የሞተውን ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት ለመቃወም በወጡ ተቃዋሚዎችና በፖሊስ መካከል ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የሰዓት እላፊ ታውጇል።

ሚኒሶታ ውስጥ የተገደለው የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በበርካታ አሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ቁጣን አቀጣጥሏል።

በዓመታት ውስጥ ጥቁር አሜሪካውያን እየደረሰባቸው ያለውን ጭቆና፣ ግፍና በደል ሊቃወሙ ብዙዎች ወጥተዋል። ፖሊሶች በአስለቃሽ ጋዝ ሰልፈኞቹን ለመበተን የሞከሩ ሲሆን በምላሹም የፖሊስ መኪኖች ተቃጥለዋል።

በበርካታ ግዛቶች ቁጣና ተቃውሞው የገነፈለ ሲሆን፤ ቢያንስ በ30 ግዛቶች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በቺካጎ ተቃዋሚዎች ድንጋይ በመወርወር ቁጣቸውን የገለፁ ሲሆን ፖሊሶችም አስለቃሽ ጭስና ጋዝ ረጭተዋል፤ በርካታ ተቃዋሚዎችንም በቁጥጥር ስር አውለዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጆርጅ ፍሎይድ የግፍ አገዳደል ቁጣቸው የገነገፈለው ተቃዋሚዎችን "ዘራፊዎችና ሥርዓት አልበኞች" ብለው መወረፋቸው ቁጣን ቀስቅሷል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ዴሪክ ቾቪን የተባለ ነጭ ፖሊስ የአርባ ስድስት ዓመቱ ጆርጅ ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ፤ ለዘጠኝ ደቂቃዎች ያህል አንገቱ ላይ በመንበርከኩ መተንፈስ ሳይችል ህይወቱ አልፏል።

መላው ዓለምን ያስደነገጠው ቪዲዮ ላይ እንደሚታየው ጆርጅ ፍሎይድ "እባክህ መተንፈስ አልቻልኩም" እያለ ሲማፀን ነበር።

በበርካታ ግዛቶች የተነሳውን ቁጣም ተከትሎ ዴሪክ ቾቪን እንዲሁም አብረውት የነበሩት ሦስት ፖሊሶች ከሥራ ተባረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዴሪክ ቾቪን በጆርጅ ፍሎይድ ግድያም በቁጥጥር ስር ውሏል።.

ተቃውሞዎችም ወደ ዋሺንግተን ያመራ ሲሆን በዋይት ሐውስም በርካቶች ተሰብስበው የትራምፕን አስተዳደር ተቃውመዋል።

በአትላንታ አንዳንድ ህንፃዎች መሰባበራቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፏል።

በአትላንታ እየተደረገ ያለው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጆርጅ ፍሎይድ በሞተባት ሚኒያፖሊስ ከፖሊስ በተጨማሪ የአገሪቱ ብሔራዊ ዘብ አካባቢውን አጥሮት የሚገኝ ሲሆን የሰዓት እላፊ አዋጅም ተጥሏል።

ዘ ስታር ትሪቡን እንደዘገበው ብሔራዊ ዘብ የአገሪቱ ተጠባባቂ ኃይል ሲሆን በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ወይም በአካካቢው ገዢ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ሲደረግላቸው ይመጣሉ ተብሏል።

በአትላንታ፣ ሚኒያፖሊስ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ፖርትላንድና ሉስቪልና ሌሎች ከተሞች የሰዓት እላፊ አዋጅ ቢጣልም አሁንም ተቃውሞች ቀጥለዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚኒያፖሊስ ከንቲባን ተቃውሞችን በቁጥጥር ስር አለማዋላቸውን ተችተው ብሔራዊ ዘቡ ጣልቃ በመግባት በቁጥጥር ስር ያውለዋል ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ ተቀናቃኝ ጆ ባይደን በበኩላቸው ጆርጅ ፍሎይድን የገደሉት ፖሊሶች ወደ ፍትህ ማቅረብ እንደሚገባቸውና ባለው መከፋፈል እሳት እያቀጣጠሉ ነው በማለት ወርፈዋቸዋል።