ጆርጅ ፍሎይድ፡ በጥቁር አሜሪካዊው ሞት ትብብር የተጠረጠሩ ሶስት ፖሊሶች ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ዙሪያ ተባብረዋል ተብለው የተረጠሩ ሦስት ፖሊሶች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ዋና ተጠርጣሪው የጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ በጉልበቱ ቆሞ የነበረው ዴሪክ ቾቪን የተሰኘ ነጭ ፖሊስ ሲሆን፤ ክስ ተመስርቶበት የነበረው በሦስተኛ ደረጃ ግድያ ነበር። ትላንት የወጡ የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚያሳዩት ግን የሰውየው ክስ ወደ ሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ከፍ እንዲል ተደርጓል።
በስፋት በተሰራጨው ምስል ላይ የሚታዩት የተቀሩት ሦስት ፖሊሶች በግድያ ውስጥ ተባብረዋል በሚል ተከሰዋል።
ምንም እንኳ ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት በኋላ ተቃውሟችን ለማሰማት የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች በቢረክቱም በአንዳንድ ቦታዎች ሁኔታው ወደለየት ሥርዓት አልበኝነትና ግጭት ተቀይሮ ነበር።
የሦስቱን ፖሊሶች ክስ ያነበቡት የሚኒሶታ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኪይዝ ኤሊሰን ፖሊሶቹን "ፍትህ ትፈልጋቸዋለች" ሲሉ ተደምጠዋል።
የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በሚኒያፖሊስ ከተማ ከፈጠረው ተቃውሞ በኋላ ከሥራቸው እንዲታገዱ የተደረጉት ሦስቱ ፖሊሶች ሁለተኛ ደረጃ ግድያን አስተባብረዋል፤ ወንጀሉን ማስቆም አልቻሉም በሚል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
የሚኒሶታ ሴናተር የሆኑት ኤሚ ክሎቡቻር በትዊተር ገፃቸው ላይ "ወደ ፍትህ ለምናደርገው ጉዞ አንድ ደረጃ የጨመረ" ሲሉ የፖሊሶቹ መከሰስ አግባብ እንደሆነ ፅፈዋል።
የፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቃ ቤንጃሚን ክራምፕ ባወጡት መግለጫ "ክሱ ፍትህን ለማስከበር ወሳኝ ነው። የጆርጅ ፍሎይድ ሬሳ አፈር ከመቅመሱ በፊት ክሱ በመመስረቱ ደስተኞች ነን" ብለዋል።
ነገር ግን ዘግየት ብሎ ሲኤንኤን የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ጠበቃው ቀርበው ዋና ተጠርጣሪው በአንደኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል መከሰስ ነበረበት ሲሉ ተደምጠዋል። አልፎም በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አሳውቀው ክሱ ሊቀየር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
የመብት ተሟጋቹ ቄስ አል ሻርፕተን የፍሎይድ ጉዳይ የፌዴራል ክስ መሆን አለበት ይላሉ።
"ይህ ጉዳይ የፌዴራል ክስ ሆኖ ካልታየ ዜጎች ከፖሊስ ጭካኔ ይድናሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ይሄ ሁሉ ድራማ ነው ማለት ነው። መንገድ ላይ የታየው ድራማ ለመሠረታዊ ለውጥ ደጀን ሊሆን ይገባል።"
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ኤሊሰን፤ "ፖሊሶቹ ተከሰሱ ማለት ፍርድ አገኙ ማለት አይደለም" ይላሉ። ''ይህን ፍርድ ማሸነፍ ከባድ ነው። ታሪክ እንደሚያሳየን ገና ብዙ ፈተናዎች እንደሚጠብቁን ነው።''
የሚኒሶታ የፍርድ ቤት ማህደር እንደሚያሳየው ከዚህ በፊት አንድ ፖሊስ ብቻ ነው ያልታጠቀ ዜጋ በመግደሉ ወንጀለኛ ሆኖ የተገኘው።
በሚኒሶታ ሕግ መሠረት በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ግድያ የተጠረጠሩ ሰዎች ወንጀሉን ለመፈፀም መነሳሳታቸውን የሚሳይ መረጃ እንዲቀርብ ግድ ይላል።
አንደኛ ደረጃ ነፍስ ማጥፋት የተቃደበት መሆን አለበት ይላል፤ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የወንጀል ጥማት ሊታይበት ይገባል ሲል የግዛቲቱ ሕግ ያትታል። ሦስተኛ ደረጃ ግድያ ማስረጃ እንዲቀርብ አያዝም። ነገር ግን ተጠርጣሪው አደገኛ የሆነ ወንጀል መፈፀሙ መረጋገእ አለበት።
በሁለተኛ ደረጃ ወንጀል የተፈረደበት ሰው እስከ 40 ዓመት እስር ሊቀጣ ይችላል። ይህም ከሦስተኛ ደረጃ ግድያ ወንጀል 15 ዓመት የላቀ ነው።
የ46 ዓመቱ ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ አንድ ነጭ ፖሊስ አስተኝቶት በጉልበቱ አንገቱ ላይ ቆሞ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መሠራጨቱ አይዘነጋም።
ከዚህ በኋላ በርካታ አሜሪካውያን ወደ አደባባይ ወጥተው የጥቁሮች ነብስ ዋጋ አላት በማለት በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከባድ ተቃውሞ ማሰማት ከጀመሩ ሳምንት አልፏቸዋል።












