የጥቁር አሜሪካዊያን ተቃውሞ ወደ ፈረንሳይ ተዛመተ

ፈረንሳይ ለተቃውⶁ የወጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሺ የሚቆጠሩ ፓሪሳዊያን የተጣለባቸውን እቀባ ቸል በመላት አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በአሜሪካ የተቀሰቀሰው የጥቁሮች የመብት ጥያቄ ነው፡፡

የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ፈረንሳዊያንን የእነርሱንም ቁስል ነካክቶባቸዋል፡፡

በ2016 በግፍ ተገድሏል የሚሉትን የ24 ዓመቱን ጥቁር ፈረንሳያዊ አዳማ ትራኦሬን ለማስታወስም ጭምር ነው አደባባይ የወጡት፡፡ ወጣቱ ትራኦሬ ሦስት ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ሲያውሉት መላ ሰውነታቸው ስለተጫነው መተንፈስ አቅቶት ነበር ለሞት የተዳረገው፡፡

ፖሊሶች በበኩላቸው "እኛ ለሞት በሚያበቃ ሁኔታ አልተጫንነውም፤ እሱን በቁጥጥር ለማስቻል የሚያበቃ ጉልበት ነው የተጠቀምነው" ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

በኋላ በተደረገ ምርመራ ወጣቱ የልብ ድካም ሕመም እንደነበረበት ተረጋግጧል፡፡ ከርሱ ግድያ ጋር ምርመራ ላይ የነበረው ፖሊስም ነጻ ተደርጓል፡፡

ትናንት ማክሰኞ በፓሪስ አቅራቢያ ባሉ ከተሞች ፖሊስና አድመኞች የተጋጩትም የትኻውኼን ሞት ከጆርጅ ፍሎይድ ጋር አስታከው ዘረኝነትን ለመቃወም ሰልፍ በመውጣታቸው ነበር፡፡

የፓሪስ የፖሊስ አለቃ አባሎቻቸው በዘረኝነት መወቀሳቸውን አጣጥለውታል፡፡

በአንድ መሰብሰብ የሚከለክለውን እቀባ ጥሰው አደባባይ የወጡ ሰልፎች ብዛት ከ20ሺ ይልቃል ተብሏል፡፡

ተቃውሞው መጀመርያ አካባቢ ሰላማዊ የነበረ ቢመስልም ኋላ ላይ ግን ግጭትን አስተናግዷል፡፡ ሰልፈኞች ፖሊስ ላይ ድንጋይ የወረወሩ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል፡፡

ተቃውሞው ከዋና ከተማዋ ፓሪስ አልፎ በማርሴይና በሌዮን አንዲሁም በሌሎች የፈረንሳይ ከተሞች ጭምር ተስፋፍቷል፡፡

ተቃዋሚዎቹ ‹‹ የጥቁር ሕይወት ዋጋው ስንት ነው›› (ብላክ ላይቭስ ማተር) የሚለውን መፈክር ይዘው ታይተዋል፡፡

ይህ የጥቁሮች የመብት እንቅስቃሴ በአሜሪካ ይጀመር እንጂ አድማሱን እያሰፋ የብዙ አገራት ጉዳይ ሆኗል፡፡

በጎርጎሳውያኑ 2016 የአዳማ ትራኦሬን ሞት ተከትሎ ለተከታታይ ቀናት በመላው ፈረንሳይ ተቃውሞ ተቀጣጥሎ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ በፈረንሳይ ከ10 ሰዎች በላይ በተመሳሳይ ቦታ መሰብሰብ ክልክል ተደርጓል፡፡

ኾኖም ለዚህ ክልከላ ተቃዋሚዎቹ ቁብ የሰጡት አይመስሉም።

የአዳማ ትራኦሬ እህት ለፈረንሳይ የዜና ወኪል እንደተናገረችው ‹‹ ዛሬ ተቃውሞ የወጣነው ለወንድሜ አዳማ ብቻ አይደለም፡፡ ለጆርጅ ፈሎይድ የግፍ ግድያ ብቻም አይደለም፡፡ ተጋድሎው ለሁሉም ተጨቋኞች ነው›› ብላለች፡፡