ዶናልድ ትራምፕ የመከላከያ ሠራዊቱን ሕዝባቸው ላይ የማዝመት ሥልጣን አላቸው?

በፖሊስ የተከበበች ተቃዋሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ሳምንት በሚኒያፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ ተጣብቆ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ለአስር ደቂቃ ተጭኖት ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ በበርካታ ግዛቶች ተቃውሞች ተቀጣጥለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፀረ-ዘረኝነት ተቃውሞ የተነሳውን አመፅ ለማብረድ የመከላከያ ሠራዊቱን እንደሚያሰማሩ ዝተዋል።

የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች የተቀሰቀሰውን አመፅ ማብረድ ከተሳናቸው የመከላከያ ሠራዊቱንን እንደሚልኩም እየተናገሩ ነው።

Getty Images
If a city or a state refuses to take the actions that are necessary...then I will deploy the US military
Donald Trump
US President

ሆኖም የተለያዩ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ፕሬዚዳንት ትራምፕ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመላክ የግዛቶቹ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸውና፤ ጣልቃ ገብነትም አይቻልም እያሉ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ሰራዊቱን በግዛቶቹ ማሰማራት ይችላሉ?

በአጭሩ አዎ ይችላሉ፤ ይህም የሚሆነው ባልተለመዱ ክስተቶች ነው።

በተለያዩ ግዛቶች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ተሰማርተዋል። እነዚህ ወታደሮች የአሜሪካ ሰራዊት ተጠባባቂ ኃይሎች ናቸው።

በአሜሪካ ከሃያ በበለጡ ግዛቶችም ተቃውሞዎችን ለማብረድ በሚል ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ወታደሮች በከተሞቹ ወይም በግዛቶቹ ጥያቄ የተላኩ ናቸው።

ነገር ግን በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በተደነገገው የአሜሪካ ህግ መሰረት የግዛቶች ጥያቄ ሳያስፈልግ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ የሚገባባቸውን ሁኔታዎች ዝርዝር ተቀምጧል።

ተጠባባቂ ብሔራዊ ዘብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዘ ኢንዘሬክሽን አክት ተብሎ የሚታወቀው ይህ ህግ ግዛቶች የአሜሪካን ህገ መንግሥት ማስከበር በሚሳናቸው ወቅት ወይም የዜጎች መብት በሚጣስበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ ያለ ግዛቶች ፈቃድ መወሰን ይችላሉ።

በጎርጎሳውያኑ 1807 የፀደቀው ይህ ህግ " ቀደምት አሜሪካውያን ጥቃት ሲያደርሱ" ፕሬዚዳንቱ ያንን ለመከላከል ሰራዊት ማሰማራት እንደሚችሉ የተደነገገ ሲሆን፤ በቀጣይም አመታትም በሃገሪቱ የሚፈጠሩ ረብሻዎችን ለማረጋጋት እንዲሁም የሲቪል መብቶችን ለማስከበር በሚልም ተጨማሪ ሃሳቦች እንዲካተቱበት ሆኗል።

በጎርጎሳውያኑ 1878 ይህንኑ አስመልክቶ ተጨማሪ ህግ የተላለፈ ሲሆን ይህም በሃገር ውስጥ ወታደራዊ ሃይል ለመጠቀም የኮንግረስ ፍቃድ እንደሚያስፈልግ የሚያዝ ነው።

ነገር ግን አንድ የህግ ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢንዘሬክሽን አክት በራሱ ፕሬዚዳንቱ ሰራዊት እንዲያሰማሩ ህጋዊ ስልጣን እንደሚሰጣቸው ነው።

ባለው የሃገሪቱ ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ የግዛቶቹን አስተዳደር ሳይጠይቁ የመከላከያ ሰራዊት የማዝመት ህጋዊ መሰረት እንዳላቸውም ተቀባይነት አለው።

በቴክሳስ ዩኒቨርስቲ የህግ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቴፈን ቫልዴክ በበኩላቸው "በታሪክም ሆነ በልምድም እንደታየው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት የፌደራል ወታደሮችን በተለያዩ ግዛቶች ላይ ለማሰማራት ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋቸው ነው" ማለታቸውን የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ከዚህ ቀደም ይህንን ህግ የተጠቀመበት ይኖር ይሆን?

የኮንግረስ አገልግሎት በሰራው ምርምር መሰረት የኢንዘሬክሽን አክት በሃገሪቷ ውስጥ በበርካታ ጊዜያት ተግባራዊ ቢሆንም በባለፉት ሶስት አስርት አመታት ግን ተፈፃሚ አልሆነም።

ለመጨረሻ ጊዜም የተተገበረው በጎርጎሳውያኑ 1992 በፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ የስልጣን ዘመት ወቅት ሲሆን፤ ይህም በሎስ አንጀለስ የተካሄደን ፀረ-ዘረኝነት ተቃውሞን ለመቆጣጠር ነው።

በጎርጎሳውያኑ 1950ና 60ዎቹ የሲቪል መብቶች ተጠናክረው በነበረበት ወቅት፣ የግዛቱ አስተዳዳሪዎች ቢቃወሙም የተለያዩ ሶስት መሪዎች ተግባራዊ አድርገውታል።

በጎርጎሳውያኑ 1957 በአርካንሰስ ግዛት ውስጥ ነጮችና ጥቁር ተማሪዎች አብረው ይማሩ የሚለውን ተከትሎ የተነሳውን ሁከት ለማረጋጋት ፕሬዚዳንት ድዋይት አይዘንአወር የመከላከያ ሰራዊት አሰማርተዋል። በወቅቱም ተቃውሞዎች ገጥሟቸው ነበር።

ከ1960ዎቹ መጨረሻ በኋላ የዚህን ህግ ተፈፃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

የካትሪና አውሎ ንፋስ ያስከተለውንም ቀውስ ተከትሎ ለተለያዩ ግዛቶች ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግ በሚልም በጎርጎሳውያኑ 2006 ማሻሻያ ቢደረግበትም፤ ግዛቶቹ በመቃወማቸው ማሻሻያው ውድቅ ተደርጓል።