ታዋቂው ቦክሰኛ ሜይዌዘር ለጆርጅ ፍሎይድ የሐዘን ሥነ ሥርዓት ወጪን እሸፍናለሁ አለ

ፍሎይድ ሜይዌዘር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው የዓለም ቦክስ ሻምፒዮን ፍሎይድ ሜይዌዘር በቅርቡ በነጭ ፖሊስ የተገደለውን የጆርጅ ፍሎይድን የሐዘን ሥነ ሥርዓት ወጪውን ሙሉ በሙሉ እንደሚሸፍን አስታውቋል።

በሚኒያፖሊስ ከሚገኝ መደብር ውጪ በፖሊስ ህይወቱ ያለፈው ጆርጅ ፍሎይድ፤ ነጭ ፖሊስ አንገቱን መሬት ላይ አጣብቆ ለአስር ደቂቃ ያህል በመንበርከኩ ትንፋሽ አጥሮት ህይወቱ አልፏል።

አሟሟቱንም ተከትሎ የፖሊስ ጭካኔን የሚያወግዙ ቁጣዎችና ተቃውሞች ተቀጣጥለው በአገሪቱ ቀጥለዋል።

አንገቱን በጉልበቱ መሬት ላይ በማጣበቅ ያነቀው ነጩ ፖሊስ፣ ዴሪክ ቾቪንም በግድያ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውሏል።

በርካታ የአሜሪካ ሚዲያዎችም እንደዘገቡት የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦችም የቦክሰኛውን ችሮታም በፀጋ ተቀብለዋል ተብሏል።

በሁኔታው ልቡ እንደተሰበረ የተገለፀው የ43 አመቱ ቦክሰኛ በጆርጅ ትውልድ ቦታ ሂውስተን እንዲሁም ሚኒሶታና ቻርሎት ለሚደረጉ የኃዘን ስርአቶች ወጪውን ይሸፍናል ተብሏል።

የጆርጅ ቤተሰቦች አራተኛ የኃዘን ስነ ስርአት ለማድረግ መፈለጋቸውን መግለፃቸውን ተከትሎም ከሶስቱ በተጨማሪ አራተኛውንም እሸፍናለሁ ማለቱን ሆሊውድ አንሎክድ ዘግቧል።

"ይህንን በመናገሬ ሜይዌዘር ብዙ ደስተኛ ላይሆን ይችላል ነገር ግን ለሚደረጉት የሐዘን ስርአቶች በሙሉ ወጪያቸውን ይሸፍናል" ማለቱን ኢኤስፒኤን የፍሎይድ ሜይዌዘር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

አክሎም "ፍሎይድ ለባለፉት ሃያ አመታት እንዲህ አይነት ተግባራትን ሲፈፅም ነበር" ብሏል።