ትራምፕ ተቃውሞውን ለማብረድ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ወታደር ለማዝመት ዛቱ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ከተሞችና የግዛት አስተዳዳሪዎች እየተቀጣጠለ ያለውን ተቃውሞ ማብረድ የማይችሉ ከሆነ እኔ ራሴ ወታደር አዝምቼ አበርደዋለሁ ሲሉ ዛቱ።

ገዢዎች "የነዋሪዎቻችሁን ደኅንነት መጠበቅ ከተሳናችሁ ያን እኔ ላደርገው እችላለሁ" ብለዋል በሰጡት መግለጫ።

ይህን በማድረግም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ጸጥ ረጭ ላደርገው እችላለሁ ይላሉ ትራምፕ።

የ46 ዓመቱ ጆርጅ ፍሎይድ በግፍ መገደል በተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ድርአምባው እንደ ሰደድ እሳት ከጫፍ ጫፍ ከተዳረሰ በኋላ በሜኔሶታ ሚኒያፖሊስ ቁጣ መቀስቀሱ ይታወሳል። ይህም ወደ ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶችና ከተሞች ተስፋፍቶ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ቆይተዋል።

ዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች ሰዓት እላፊ እስከማወጅ ቢደርሱም ተቃዋሚዎች ግን ያ ግድ አልሰጥ ብሏቸዋል።

ለምሳሌ ኒውዮርክ እስከ ንጋት 11፡00 ሰዓት ዝግ ስታደርግ ዋሺንግተን ዲሲ ያወጀችውን ሰዓት እላፊ ለሁለት ቀናት አራዝማለች። ለጊዜው በዚያች አገር ኮሮናቫይረስንም ሆነ ሰዓት እላፊውን ቸል ተብለውታል።

ትራምፕ የተናገሩት ምንድነው?

ዶናልድ ትራምፕ በነጩ ቤተ መንግሥት ሮዝ ጋርደን ከተሰኘው አጸድ ሆነው ነበር መግለጫ የሰጡት።

የሚገርመው እርሳቸው መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ፖሊስ አስለቃሽ ጭስና አድማ መበተኛ ጥይት ሲተኩስ በቅርብ ርቀት ይሰማ ነበር።

"ሁሉም አሜሪካዊያን በሆነው ነገር ሐዘን ተሰምቷቸዋል። ነገር ግን የእርሱ ሞት መታወስ ያለበት በብጥብጥና በሥርዓት አልበኝነት መሆን የለበትም" ሲሉ ነው ንግግራቸውን የጀመሩት፤ ትራምፕ።

አሁን በከተሞች የታየው ዘረፋና ጋጠወጥነት "አሳፋሪ" ብለውታል ፕሬዝዳንቱ።

አሁን ነገሩ የማያበቃ ከሆነ "በሺህ የሚቆጠርና እስከ አፍንጫው የታጠቀ ወታደር፣ የመከላከያ ኃይል እና ሕግ አስከባሪዎችን አሰማርቼ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር አደርጋለሁ" ሲሉ ዝተዋል ዶናልድ ትራምፕ።

ከተሞችና የግዛት አስተዳዳሪዎች ነገሩን የማያቆሙት ከሆነ እኔ አቆመዋለሁ። መፍትሄውም መከላከያ ሠራዊትን መላክ ነው ሲሉ አክለዋል።

የትራምፕ ተገዳዳሪ የዲሞክራት ፓርቲ እጩው ጆ ባይደን መግለጫውን ተከትሎ ተቃውሞ ለማሰማት አልዘገዩም።

"በአሜሪካ ሕዝብ ላይ የአሜሪካ መከላከያ ሠራዊት አሰማራለሁ ማለት ምን የሚሉት እብደት ነው?" ሲሉ የትራምፕን ንግግር ተችተዋል።

የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባል ቸክ ሹመር በበኩላቸው "ይሄ ፕሬዝዳንት ወርዶ ወርዶ ዘቀጠ፤ ንግግሩ ማንነቱን ነው የሚነግረን" ሲሉ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

በአሜሪካ ሕግ የውስጥ ተቃውሞን ለማብረድ መከላከያ ሠራዊት በአገሪቱ ላይ ማዝመት ይቻላል ወይ? የሚለው የሕግ አዋቂዎችንና ሚዲያውን እያከራከረ ይገኛል።

ጆርጅ ፍሎይድን ጉሮሮውን በጉልበቱ ረግጦ በመግደል ተጠርጥሮ የተከሰሰው የቀድመው የፖሊስ ባልደረባ ዴሪክ ቾቪን በሦስተኛ ደረጃ ነፍስ በማጥፋት ወንጀል ተከሶ ወህኒ ቤት ይገኛል። በሚቀጥለው ሳምንት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ትናንት የሟች ቤተሰብ ጠበቃ ክሱ መሆን ያለበት አንደኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ነው ሲል ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ መናገሩ ይታወሳል።

ሦስተኛ ደረጃ የግድያ ክስ በቸልተኝነት ነፍስ ማጥፋት ጋር የሚያያዝ ቀለል ያለ ክስ ሲሆን፤ የአንደኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ክስ ግን ገዳይ ሆን ብሎ፣ አቅዶና አልሞ በክፋት ተነሳስቶ ነፍስ ሲያጠፋ የሚመዘዝ የክስ አንቀጽ ነው።

ከፖሊስ መኮንኑ ዴሪክ ጋር በወቅቱ አብረው የነበሩት ሦስት የፖሊስ መኮንኖች ከሥራ የተባረሩ ሲሆን እስከዛሬም ድረስ በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸው ብዙ ሰልፈኞችን አበሳጭቷል፤ አስቆጥቷል።

የተጠርጣሪው ፖሊስ መኮንን ባለቤት የፍቺ ፋይል መክፈቷን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።