ለጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ደማቅ ሽኝት ተደረገ

ለጆርጅ ፍሎይድ በተደረገው መታሰቢያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ለጆርጅ ፍሎይድ በተደረገው መታሰቢያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል

በነጭ ፖሊስ በግፍ ለተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ደማቅ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ተደርጎለታል። ስመ ጥር የጥቁር መብት ተሟጋቾች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር አድርገዋል።

የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቃ "ደንበኛዬን ለሞት ያበቃው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው ይላሉ፤ በዘረኝነት ወረርሽኝ መሞቱን ማን በነገራቸው. . ." ሲል ስሜታዊ ንግግር አሰምቷል።

በሟች ጆርጅ ፍሎይድ የሽኝትና መታሰቢያው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ሁሉ ተነስተው እንዲቆሙና ለ8 ደቂቃ ከ46 ሴኮንዶች የሕሊና ጸሎት እንዲያደርጉ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም ነጩ የፖሊስ ባልደረባ ዴሪክ ሟች ፍሎይድ አንገት ላይ በጉልበቱ ቆሞ ትንፋሹን እስኪያጣ የቆየበትን ጊዜን ለመዘከር የተደረገ ነበር።

የጆርጅ ፍሎይድ የሕይወት ታሪክም በታዋቂው የጥቁር መብት አቀንቃኝ ሬቭ አል ሻርፐን አማካኝነት ተነቧል።

አል ሻርፐን ባደረጉት ንግግር በመላው አሜሪካ የምትገኙ ጥቁር ወንድሞቼ፣ አሁን ሁላችንም "ከአንገቴ ጉልበትህን አንሳልኝ" የምንለበት ሰዓት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የጆርጅ ፍሎይድ የመጨረሻ ሰዓት ትንቅንቅ በቪዲዮ ተቀርጾ ማኅበራዊ ድር አምባው በከፍተኛ ፍጥነት ከተጋራው በኋላ በአሜሪካ አብዛኞቹ ግዛቶች ለቀናት የዘለቀ ተቃውሞን ቀስቅሶ ቆይቷል። ተቃውሞቹን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋትም ሆነ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊያቆማቸው አልቻለም ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ከሚካሄድበት ቅርብ ርቀት በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ላይ ተባባሪነት አሳይተዋል የተባሉት ሦስት ተጨማሪ የፖሊስ ባልደረቦች ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የዋስ መብታቸው እንዲከበር 1 ሚሊዮን ዶላር እንዲያቀርቡ የተጠየቁ ሲሆን ይህም የገንዘብ መጠን የጦር መሣሪያዎቻቸውን በፈቃዳቸው ከመለሱና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟሉ ወደ 750 ሺህ ዶላር ዝቅ ሊል እንደሚችል ተነግሯቸዋል።

በጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ ለደቂቃዎች በመቆም ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል በሚል የተጠረጠረው የቀድሞው ፖሊስ ባልደረባ ዴሪክ ቾቪን ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ አባላት፣ እውቁ የመብት ታጋይ ጄሴ ልዊስ ጃክሰን፣ የሜኔሶታ ገዢ ቲም ዋዝ፣ የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ታድመዋል።

የጆርጅ ፍሎይድ ወንድም ፍሎናይዝ ፍሎይድ በበኩሉ ባደረገው ንግግር የልጅነት አስተዳደጋቸው ምን ይመስል እንደነበር አስታውሷል።

"ድሆች ከመሆናችን የተነሳ ልብሳችንን በሳፋ አጥበን በምድጃ እሳት ሙቀት ነበር የምናደርቀው…" ሲል በስሜት የታጀበ ንግግር አድርጓል። የወንድሜ ሕይወቱ ሳይደምቅ ሞቱ በዚህ ደረጃ መድመቁ ይደንቀኛል ሲልም ተናግሯል።

የመብት ታጋዩ አል ሻርፕተን በበከላቸው ለፍሎይድ ሞት ተጠያቂ መኖር አለበት ሲል አሳስቧል።

"የፍትህ ሥርዓቱ መልክ እስኪይዝና እኩልነት እስኪያንጸባርቅ ድረስ ዝም አንልም" ሲል ተቃውሞው ወደፊትም እንደሚቀጥል ጥቆማ ሰጥተዋል።

"የፍሎይድ ሕይወት የመላው ጥቁሮችን ሕይወት ይወክላል፤ ሞቱም ሕይወቱም የእኛው ሞትና ሕይወት ነው" ብለዋል።

"በእርሱ የደረሰው ነገር በሁሉም ጥቁር አሜሪካዊያን እየደረሰ ያለው ነው፤ በትምህርት፣ በጤና፣ በፍትህ ሥርዓት መበደል ፍሎይድ የደረሰበት ብቻ ሳይሆን የእኛም ሕይወት ነው፤ አሁን ጊዜው 'አንተ ነጭ ጉልበትክን ከአንገቴ አንሳልኝ' የምንልበት ነው" ብለዋል።

ለጆርጅ ፍሎይድ የሚደረገው የሽኝት ሥነ ሥርዓት በትወልድ ቦታው ኖርዝ ካሮላይና ቅዳሜ፣ እንዲሁም ባደገበት ሂውስተን ደግሞ ሰኞ ይቀጥላል።