ከቁማር ጋር በተያያዘ በፖሊስ ይዞታ የቆየችው አህያ ነጻ እንድትወጣ ተወሰነ

ከቁማር ጋር በተያያዘ በፖሊስ ይዞታ የቆየችው አህያ ነጻ እንድትወጣ የፓኪስታን ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Farooq Sindhu

ከሕገ-ወጥ ቁማር ጋር በተያያዘ በፖሊስ ይዞታ ሥር የቆየችው አህያ እንድትለቀቅ የፓኪስታን ፍርድ ቤት ወሰነ።

በገጠራማ ፓኪስታን የአህያ ፍጥነትን መሰረት በማድረግ ሕገ-ወጥ ውርርድ ማድረግ የተለመደ ነው።

ፖሊስ እንዳለው አህያዋ 600 ሜትር የሚሆን ርቀትን በ40 ሰከንድ ውስጥ ሮጣ ትጨርሳለች፤ አትጨርስም በሚል ውርርድ እያደረጉ የነበሩ 8 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ነበር።

ከቀናት በኋላም አህያዋ ከፖሊስ ይዞታ ነጻ ስትሆን፤ ስምንቱ ሰዎችም በዋስ ከእስር ተለቀዋል ተብሏል።

በፓኪስታን ይህ ዜና "አህያ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለች" ተብሎ ከተዘገበ በኋላ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበር። ፖሊስ ግን ለቢቢሲ በሰጠው ቃል አህያዋን ላልተወሰ ጊዜ ለመያዝ ተገደድኩ እንጂ በቁጥጥር ሥር አላዋልኩም ብሏል።

ፖሊስ ጨምሮ እንዳለው ስምንቱን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ባዋለበት ወቅት፤ መሬት ላይ ጨርቅ ተዘርግቶ የተሰበሰበ 121ሺህ ሩፒስ (740 ዶላር) የውርርድ ገንዘብ በኤግዚቢትነት መያዙን አስታውቋል።

የአከባቢው ፖሊስ አዛዥ ፖሊስ በኤግዚቢት ከያዘው ገንዘብ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Farooq Sindhu

የምስሉ መግለጫ, የአከባቢው ፖሊስ አዛዥ ፖሊስ በኤግዚቢት ከያዘው ገንዘብ ጋር

አህያዋ ከፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ለአራት ቀናት ገደማ ታስራ ቆይታለች። የፓኪስታን ጋዜጠኖች አህያዋ ታስራ በቆችበት ፎቶግራፍ ሲያነሷት እና የፖሊስ አባላትን በጥያቄ ሲያጣድፉ ታይተዋል።

አህያዋ ከፖሊስ ይዞታ ነጻ ከወጣች በኋላ ባለንብረቷ እንዲረከባት መደረጉ ተነግሯል።