በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ተመልሶ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት የሚናፍቁት የትግራይ ዳያስፖራዎች

ሙዑዝ፣ ብርዛፍ እና ዘረሰናይ
የምስሉ መግለጫ, ሙዑዝ፣ ብርዛፍ እና ዘረሰናይ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት አስራ ስምንት ወራቶችን አስቆጥሯል። በጦርነቱ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸው እና መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በተለያዩ ወገኖች ሲወጡ የቆዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በትግራይ ክልል ደግሞ ማኅበራዊ አገልግሎቶች [ስልክ፣ ኢንተርኔት እና ሌሎች] በመቋረጣቸው ምክንያት በርካታ በውጪ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ለከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት መጋለጣቸው ይናገራሉ።

ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ባለመቻላቸው ከባድ ጭንቀት እና ሥነ ልቦናዊ ጫና እንደፈጠረባቸው ያነሳሉ።

"ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘኋቸው. . ."

ብርዛፍ ቅዱስ፡ አሜሪካ ነው የምትኖረው። በስልክም ሆነ በኢንተርኔት ቤተሰቦቿ በቀጥታ ካገኘቻቸው ወራት ተቆጥረዋል ትላለች።

"የትግራይ ኃይሎች መቀለን ሲቆጣጠሩ ነበር ወላጆቼን፣ እህት እና ወንድሞቼን ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ያነጋገርኳቸው። ያኔ ካገኘኋቸው በኋላ ስልክም ኢንተርኔትም ተቋረጠ።"

የፌደራል መንግሥት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ "ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት" በሚል ሠራዊቱን ከክልሉ ማስወጣቱን በገለጸበት ወቅት የትግራይ ኃይሎች የክልሉ መዲናን ጨምሮ አብዛኛውን የክልሉን ክፍሎች መቆጣጠራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ላይ የነበረው የስልክ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠ።

ብርዛፍ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት በነበረት ወቅት ከቤተሰቦቿ ጋር በቪድዮ እና በድምጽ ትገናኝ ነበር፤ አሁን ግን ይሄን ዕድል የላትም።

ሙዑዝ ግተት፣ በቱርክ የሚኖር የክልሉ ተወላጅ ሲሆን ከቤተሰቦቹ ጋር ከተገናኘ 11 ወራት አልፈዋል። በዚህ ምክንያት "በተለይ በአባቴ ምክንያት እንቅልፍ የለኝም" ይላል።

"አባቴ የ80 ዓመት አዛውንት ነው። በሽተኛ ስለሆነ ቀዶ ህክምና አድርጎ ነበር። አሁን ምን ሁኔታ ላይ ይሆን? ምን ችግር ገጥሞት ይሆን? ምንስ እየበላ ነው? ህክምናውን እየተከታተለ ይሆን? የማውቀው ነገር የለም።"

ከኢትዮጵያ ከወጣ እና ከቤተሰቦቹ ጋር ከተለያየ አስር ዓመት ያስቆጠረው ዘረሰናይ ካሕሳይ በበኩሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ከቤተሰቦቹ ጋር በስልክ አልያም በኢንተርኔት ይገናኝ ነበር።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም እስከ ሰኔ ወር ድረስ በነበረው የስልክ አግልግሎት ከተወሰኑት ጋር መገናኘት ይችል እንደነበር ያስታውሳል።

"ትግራይ ውስጥ ከሚገኙ ቤተሰቦቼ ጋር ከሰኔ ወር በፊት ነው የተገናኘሁት። በወቅቱ ስልክ በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ስለነበረ ከእህቶቼ፣ ከእናቴ እና ሌሎች ቤተሰቦቼ ጋር እገናኝ ነበር። ከሰኔ ወር በኋላ ግን ያገኘሁት ቤተሰብ የለም" ይላል።

እነዚህ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አልፎ አልፎ አንዳንድ የሳተላይት ኢንተርኔት የሚያገኙ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ እንደሚነግሯቸው ይናገራሉ።

ሆኖም በየቀኑ የቤተሰቦቻቸውን ድምጽ መስማት የለመዱ ሰዎች አሁን በቀጥታ ማግኘት ባለመቻላቸው ደኅንነታቸው እንደሚያስጨንቃቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

'ችን እና ጤናችን ተቃውሷል'

እነዚህ መሠረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለረጅም ወራት በመቋረጣቸው ምክንያት የቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት እና ጤንነት ባለማወቃቸው ምክንያት ከመጨነቅ አልፎ በራሳቸው ህይወት ላይ ጭምር ከባድ ጫና ማሳደሩን አስተያየት ሰጪዎቹ ያነሳሉ።

ብርዛፍ "ምን ሆነው ይሆን? ተርበው ይሆን? የሚል ነገር በማታውቅበት ሁኔታ ሰላም ሊኖርህ አይችልም። ውስጤ ፈጽሞ መረጋጋት አልቻለም፤ በመሆኑም የማይቻለውን ችለን ነው የምንሄደው" በማለት የችግሩን ክብደት ለማስረዳት ትሞክራለች።

በዚህ ምክንያት በሥራዬ እና በጤናዬ ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል በማለት ከዚህ በተነሳ ሥራዋን ማቋረጧን ትናገራለች።

ዘርአሰናይ በበኩሉ አሁን ያለውን ችግር ተከትሎ ጤንነቱ የተፈተነበት ጊዜ ማሳለፉን ገልጿል።

"ለረዥም ጊዜ ቤተሰሰቦቼ ስላሉበት ሁኔታ ሳላውቅ መቆየቴን ጨምሮ አሁን ያለው ሁኔታ ህይወቴን አክብዶታል። ከዚህ በፊት ያልነበረኝን የጨጓራ ህመም ታምሜያለሁ" የሚለው ዘረሰናይ ላለፉት ስምንት ወራት ጤንነቱ አለመመለሱን ተናግሯል።

መሰል ችግሮች ሌሎች የሚያውቃቸው ሰዎች ጋር ጭምር መታየቱን በመግለጽ "ብስጭት፣ ጭንቀት እና ናፍቆት ተደራርበው እስከ ዛሬ በህይወቴ መቆየቴ ተመስገን የሚያስብል ነው። በዚህ ምክንያት ሥራ አቁሜ ቤት ነው የተቀመጥኩት" በማለት ስላለበት ሁኔታ ያስረዳል።

ባለቤቱ ጨምሮ እጅግ ፈታኝ ጊዜያት እያለፉ መሆናቸውን የሚናገረው ሙዑዝ፣ በዚህ ወቅት ምግብ በአግባቡ መመገብ እንደሚቸገር ጨምሮ ገልጿል።

"በትክክል ማሰብ አልችልም፤ ሥራዬንም በአግባቡ መስራት አልቻልኩም" ይላል።

ሁሉንም በአገሪቷ ሰላም ተመልሶ ከቤተሰቦቻቸው የሚገናኙበት ቀን በተስፋ እየተጠባበቁ ነው።