የቤተሰቦቻቸውን ናፍቆት ፎቶዎችን በማህበራዊ ሚዲያ በማጋራት የሚገልፁት የትግራይ ተወላጆች #sendlovetotigray

በስደት ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላለፉት በርካታ ወራት የቤተሰቦቻቸውን ድምጽ ባለመስማታቸው ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ

ከአገር ውጪ የሚኖሩ ሰዎች፡ አንድን ሰው ወደ አገር ቤት ሲመለስ 'እባክህ ይህቺን እቃ ውሰድልኝ? ቤተሰብ ጋር አድርሽልኝ? ማለቱ የተለመደ ነው።

ድምጽ እንደ እቃ ግን በአደራ ሲላክ ግን ብዙ አልተሰማም ነበር። ነገር ግን አስራ ስምንት ወራት ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተነሳ ከመላው ዓለም ተቆራርጣ በምትገኘው የትግራይ ክልል ሰዎች ድምጻቸውን ቀርፀው በአደራ እየላኩ ይገኛሉ።

አንድ አመት ከስድስት ወር ለሚሆን ጊዜ በትግራይ የስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ባንክ እና መሰል ማህበራዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ምክንያት በርካታ የክልሉ ተወላጆች የቤተሰቦቻቸው ወይ የጓደኞቻቸው ሁኔታ ማወቅ አለመቻላቸው ይናገራሉ።

ስለዚህ ከቻሉ ድምጽ ነው የሚልኩት።

መልዕክቱን ማድረስ ለሚችለው ሰው ድምጻቸውን ቀርፀው በመላክ መልስ ይጠብቃሉ

መልዕክቱ 'እማዬ ደህና ነኝ አታስቢ' ይሆናል። ወይንም ደግሞ 'አባ ጤናህን እንዴት ነህ?' ይሆናል።

ይህንን የሚሰሙ የቤተሰብ አባላት መልዕክት ካላቸው 'ልጄ እኛ ደህና ነን' የሚል በተስፋና በፍቅር የተሸመነ ቃል ይልካሉ።

ከዚያ መልዕክተኛው ኢንተርኔት ባለበት ስፍራ መልዕክቱን ይልካል። መልዕክቱ የደረሰው እድለኛ ሰው ይህንን የፍቅር ሸማ የተከናነበ ድምጽ ለብሶ መቆዘም ነው።

ይህ ግን ለሚሊዮኖች ቅንጦት ነው። ጥቂት እድል እና አጋጣሚ የሰመረላቸው የሚያደርጉት መሆኑን ይናገራሉ፤ ከስንት አንድ በማለት።

ሄርሞን ገብረሐዋርያ ድምጿን ለቤተሰቦቻቸው ከላኩት መካከል አንዷ ነች።

"ከሁለት ሳምንት በፊት በቀይ መስቀል በኩል እድል ተገኝቶ ቤተሰቦቼ እንዲደውሉልኝ ስጠብቅ ነበር፤ ግን አልተሳካም። አላገኘኋቸውም። አልፎ አልፎ ኢንተርኔት ወዳለበት ቦታ የሚሄዱ ሰዎችን ግን እጠይቃለሁ፤ እድል ከቀናኝ መልእክት ይደርሰኛል። በተስፋ ነው የምኖረው" ትላለች።

ይህ ግን ሁሉም የሚያገኙት አጋጣሚ አይደለም።

በፌስቡክ ከተጋሩ ምስሎች መካከል ጥቂቶቹ

የፎቶው ባለመብት, facebook/screenshot

ለዚህም ይሆናል፣ ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተጀመረው #sendlovetotigray በተሰኘ ዘመቻ ብዙዎች በጦርነቱ ምክንያት የቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ማወቅ አለመቻላቸው በመግለጽ የተለያዩ ፎቶዎቻቸውን ሲያጋሩ የታየው።

ምስሎቹ በፈገግታ የደመቀ ፊት፣ መሰባሰብ፣ የፈካ ማህበራዊ ሕይወት፣ ድግስ፣ አውዳመት፣ ዝምድና፣ እናትነት፣ ጉርብትና ይታይባቸዋል።

ከእነዚህ ካሜራ ካስቀራቸው የትናንት ምስሎች ዛሬ የሚመዘዝ ናፍቆት አለ። ፎቶውን የሚያዩ ግን ናፍቆትን ብቻ ሳይሆን ተስፋንም ማጋራት ያስባሉ።

ብዙ ነገዎችን አልፎ በመጣው ነገ ውስጥ ዳግም ለአይነ ስጋ መብቃትን፣ የፈረሰ ማህበራዊ ሕይወትን መገንባት ያቅዳሉ።

ይህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሲጀመር አብዛኛዎቹ ወደ ፎቶ አልበማቸው በመሄድ ከልጅነት እስከ እውቀት ያላቸውን፣ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር የነበራቸውን ትዝታ ማጋራት ጀመሩ።

በዘመቻው ከተሳተፉ ሰዎች መልዕክቶች መካከል ደግሞ "እናቴን ለመጨረሻ ግዜ ካነጋገርኳት 314 ቀናት አለፉ . . . ቤተሰቦቼ ስላሉበት ነገር ከሰማሁ አንድ አመት አለፈኝ . . . አገሬን ናፈቀኝ . . . " የሚሉ ይገኙበታል።

ናፍቆት ከተነሳ፣ ዳግማዊት አሁን የሚሰማት ስሜት ከተለመደው የተለየ መሆኑን ትናገራለች።

"ይህ የለመድነው መናፈቅ ብቻ አይደለም። በተለያየ ምክንያት ከቤተሰብ ተለይተን ስንቆይ እንናፍቃቸዋለን። አሁን ያለው ግን የተለየ ነው፤ ሃዘን ያለው ናፍቆት ነው። የመናፈቅ ስሜቱ ውስጥ በህይወት ይኖሩ ይሆን? አገኛቸዋለው? ስንገናኝ ምንድን ነው የሚሆነው? የሚሉ ብዙ ስጋቶች አሉት" ትላለች።

ዳግማዊት ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ጥቂት ሳምንታት ነው በስራ ምክንያት ከትግራይ የወጣችው።

17 ወራት ባለፈው በዚህ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተነሳም ቤተሰቦችዋን፣ ጓደኞችዋንም ሆነ ሌሎች የምታውቃቸውን ሰዎች ማግኘት አለመቻልዋን ትናገራለች።

በዚህ ላይ ጦርነቱን ከነአካቴው አለመቆሙ፣ ቤተሰቦቿ ያሉበት ሁኔታ የምታውቅበት መንገድ አለመኖሩ እንቅልፍ ይነሳኛል ትላለች።

ባለፉት ቀናት፡ የተለያዩ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን፣ አብሮ አደጎቻቸውን ፣ የሚኖሩበት የሚኖሩበት ከተማን የመሳሰሉት ፎቶዎች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት፡ ለሚያስቡላቸው ሰዎች አለን የሚሉት ስሜት እና ፍቅር ሲገልጹ ዳግማዊትም ተቀላቀለች።

"ሰዎች የለጠፏቸው ፎቶዎች ላይ የማውቃቸው ሰዎች ሳይ 'የት ይሆኑ?' ብዬ ብዙ አስባለሁ። ይህን ስሜታዊ ያደርጋል። አሁን ላይ ከሰዎች ጋር የምናወራበት፣ ስሜታችን የምንገልጽበት አማራጭ ማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ነው። የምናውቃቸው ሰዎች ፎቶ ማየት ደግሞ ያሳለፍነውን ወደ ኋላ ተመልሰን እንድናስታውስ አድርጎናል" ትላለች።

'ተስፋ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ'

በትዊተር ከተጋሩ ምስሎች መካከል ጥቂቶቹ

የፎቶው ባለመብት, Twitter

ፎቶ ኃይል አለው። ትዝታን ከንፋስ አፍጥኖ ያቀብላል። ትናንትን እስከነ ጥዑመ መዐዛው የማድረስ ፀጋ አለው።

በአካል የተለያዩ ሰዎች በመንፈስ የማገናኘት ምስጢር አለው ብለው የሚያምኑ ሰዎችም ቀላል ቁጥር የላቸውም።

"እኛ ለትግራይ ያለን ናፍቆት ውስጣችን በሚኖር ፍቅር ውስጥ አለ። ይህ በብዙ ነገር ይገለጻል፤ ባህላችን በሚያሳዩ፣ በታዋቂ ሰዎች ወይም የኀብረተሰቡ ማህበራዊ እንቅስቃሴ በሚያሳዩ ፎቶዎች ሊገለጽ ይችላል" የሚለው የማህበራዊ ድር አምባው ዘመቻ ሃሳብ አምንጪ ጎይቶም ተገኝ ነው።

ጎይቶም የኮምዩኒኬሽን እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሞያ ስለሆነ፣ የተለያዩ አጋጣሚዎች በስእል እና በቪድዮ የመያዝ የቆየ ልምድ እንዳለው ይናገራል።

ለዚህ የፎቶ ማጋራት ሃሳብ መነሻ የሆኑት ሁለት ምክንያቶች እንዳሉ የሚገልጸው ጎይቶም በዋናነት ሰዎች በአንድ መልካም ነገር ላይ በማምጣት ትርጉም ያለው መልእክት ማስተላለፍ እንዲችሉ ማድረግ ነው ብሏል።

"ቤሰተቦቻችን ስለ እነሱ እያሰብን እንዳለ መልእክት ከደረሳቸው ተስፋ ሊሆናቸው ይችላል። ያሉበት ሁኔታ ከባድ ነው፤ ጦርነት ሲጀመር ትግራይ ነበርኩ። የማህበራዊ አገልግሎቶች መቋረጥ፣ ሰዎች መገናኘት አለመቻላቸው፣ ሱቆች ዝግ መሆናቸው፣ ባንክ አለመኖሩ፣ ገንዘብ ማጣት ምን እንደሚመስል አይቸዋለሁ። ይህ ረዘም ላለ ጊዜ ሲቀጥል ማየት ይከብዳል። በአጋጣሚ ሰዎች የምንለጥፋቸው ምስሎች አይተው ሲገናኙ መልካም ማውራት ከቻሉ፣ እንደምናስብላቸው ከገባቸው ተስፋ ይሆናቸዋል የሚል እምነት አለኝ" ይላል።

አብኛዎቹ ከትግራይ ውጪ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር የሚገናኙበት እድል ጠባብ መሆኑ ይናገራሉ።

"ከወራቶች በኋላ ከእለታት አንድ ቀን መልእክት ይደርሰናል፤ ግን ስላሉበት ሁኔታ አናውቅም። ሁኔታዎች ከባድ ስለሆኑ ተስፋ የመቁረጥ፣ ሞራል የመነካት ስሜቶች አሉ። ይህ [ሃሽታግ] ይሄንን ከባድ ጊዜ በተወሰነ መልኩ ማለፍ ያስችለናል ብዬ ስላመንኩ ነው የጀመርነው" ሲል ይናገራል።

በተጨማሪ "ብዙ ሰዎች በአንድ መልካም ነገር ላይ በማምጣት ትልቅ መልእክት ማስተላለፍ ይቻላል። ለወራቶች በእጅጉ የሚረብሹ፣ የግጭት ዜናዎች፣ የአየር ጥቃት፣ የህጻናት ሞት፣ ስለ ረሃብ ሲደርሰን ቆይቷል። ይህ ሁኔታ የትግራይ ተወላጆችን ጤና ጎድቶታል፤ ብዙ በስነ ስርአት የማይተኙ እና ስራቸውን መስራት ያልቻሉ በርካቶች አሉ። ስለ ቤተሰቦቻችን በማሰብ እና ያለን ፍቅር በመግለጽ ግን ተስፋ ያላቸው መልካም ነገሮች ላይ መስራት እንችላለን" ብሏል።

ሰዎች እንዴት ተቀበሉት?

#sendlovetotigray ሲጀመር፡ ዳግማዊት በማህበራዊ ትስስሮች ላይ ካጋራችው ምስል አንዱ የእህቷ የሰርግ ፎቶ ነው።

መቼስ በሰርግ እና ጦርነት መካከል ያለው ርቀት ግልጽ ነው፤ አንዱ የደስታ ልክ መገለጫ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የከባድ ሃዘን እና ማጣት ምንጭ ነው።

"በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ትዝታዎቻችን ማጋራት መቻላችን መልካም ነገር ነው፤ ለምንወዳቸው ሰዎች ፍቅር መላክ ትልቅ ነገር ነው። ምናልባት አንድ ቀን አሁን የለጠፍናቸው ምስሎች ሊያዩዋቸው ይችላሉ። ሰዎች ስታስባቸው ደግሞ ያስቡሃል፤ ይህም ጠንካራ የትስስር ኃይል ነው" በማለት የፈጠረባትን ስሜት ትገልጻለች።

ሰዎች #sendlovetotigray ስር የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተጋሩት አጫጭር ቪድዮዎች እና ምስሎች የተለያዩ ግለሰቦች በህዝብ በአላት፣ የስፖርት ጨዋታዎች፣ ሰርግ እና ሌሎች ማህበራዊ መድረኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጉዞ እና ፌስቲቫሎችን ያሳለፉትን ጊዜ የሚያስታውሱ ናቸው።

አሁንም ቢሆን እንደነዚህ ያሉ የሰው ልጅ ህይወት አካል የሆኑ ነገሮች መዘንጋት የለብንም የምትለው ሄርሞን አጋጣሚውን በመጠቀም ለጓደኞቼ የተስፋ መልእክት ለማስተላለፍ እየተጠቀምኩበት ነው ትላለች።

"ህዝብ በረሃብ እና ስደት መሃል ነው ያለው። የማውቃቸው ሰዎች አሉ ወይ ብለን ስንጠይቅ መልስ የማናገኝበት ሁኔታ ውስጥ ነን። ስለዚህ አብረውን ለነበሩ፣ ስራ ላይ ያገኘናቸው ሰዎች ከጎናቸው መሆናችን እና ያሳለፍነው ነገር ተመልሰን ማድረግ እንደምንችል መልእክት ማስተላለፍ ችለናል" ብላለች።

በትግራይ ክልል የሚኖሩ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ፣ በተወሰኑ ሰዎች በኩል የሚያገኙዋቸው ሲሆን ከስክሪን የተወሰዱ ምስሎችን እየሸጡ እና እያጋሩ ምን ተባለ የሚለውን መረጃ ይለዋወጣሉ።

መረሳ* የተባለ አንድ የመቀለ ኗሪ " ከባድ ሁኔታ ውስጥ ስላለ እንዲህ ያሉ ነገሮች መርሳት ደረጃ ላይ ደርሷል። አንድ ቦታ ላይ የእኔ እና የጓደኞቼ ምስል ተለጥፎ ሲያሳዩኝ እንዲህም ነበርኩኝ ብዬ ያለፈውን ህይወቴን እና አሁን ያለውን በማሰብ አዝኛለሁ" ይላል።

"አሁን ዛሬ ስለምናገኘው ምግብ ነው የምናስበው፤ ስራ፣ ኢንተርኔት፣ ባንክ ስለሌለ አኗኗራችን ተቀይሯል። እየተነፈስን ተስፋ የሌለው ህይወት ነው የምንኖረው።"

ከክልሉ ውጪ በአገር ውስጥም በውጪ አገራትም የሚኖሩ እና የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች፣ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሰዎች ፍቅርን ማሳየት ላይ ያተኮረ ቢሆንም እንኳ ከዚህም ባሻገር በትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር እንዲወያዩበትም እድል ከፍቷል።

"አሁንም ያለንበት ሁኔታ መሰማት አለበት። ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ሲቀጥሉ ማየት ያሳዝናል። ግን ፎቶዎቻችን በመለጠፍ መልእክት ማስተላለፍ ብንችልም ለእኔ ደስታ እና ሃዘን ነው የፈጠረብኝ። አንዳንድ ምሰል እንቅስቃሴዎች ስቃያችን የሚፈወስበት መንገድም ሊሆኑ ይችላሉ" ትላለች ዳግማዊት።

በመሆኑም፡ ጦርነት እንዲቆም፣ ሰላም እንዲመጣ እና የተቋረጡ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተመልሰው ሰዎች ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው ጋር መድረስ እንዲችሉ የአስተያየት ሰጪዎቹ ምኞት ነው።

"ይህን እስኪያልፍ የምንተጋገዝበት መልካም መንፈስ የምንፈጥርበት ነገር ማድረግ አለብን" የሚለው ጎይቶም "ሁሉም ነገር ሲከፈት ያ አሁን የምንገነባው መንፈስ ነው ቤተሰቦቻችን ለማገዝ፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የሚያስችለን ነው" በማለት ተስፋውን አጋርቷል።