ቤተሰብ፡ ልጆቻችን ስልክና ፊልም ላይ ተጥደው መዋላቸው ምን አደጋ አለው?

የፎቶው ባለመብት, SDI Productions
የዘመኑ ልጆች የስክሪን ትውልድ ናቸው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
እንግዳ ሲመጣ ሰውየውን ሳይሆን ስልኩን ይናፍቃሉ፡፡ ዐይናቸው ይቁለጨለጫል፡፡ ስልክ የሚሰጣቸው ዘመድ ምርጡ የቤተሰብ አባል ነው፡፡
ሐፍረት የሚባል አልፈጠረባቸውም፡፡ ስልክ ጎልጉለው ጌም የሚከፍቱበት ፍጥነት አስደናቂ ነው፡፡ የተቆለፈ ስልክ ሰብረው ሲገቡ በብርሃን ፍጥነት ነው፡፡
የዛሬ ልጆች ማህጸን ውስጥ አጭር የኮምፒውተር ስልጠና ወስደው ወደዚህ ምድር የመጡ ነው የሚመስሉት፡፡
ይህ እንደ ወላጅ እኛን ሊያሳስበን ይገባል?
መልሱ 'አዎ'ም 'አይ'ም ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ አሰናጅ ስለ ልጇ ባህርይ በመተረክ ትጀምራለች፡፡
"…ልጄ ከሰው ጋር መነጋገር ከመጀመሯ በፊት ከስልኬ ጋር ነው የተነጋገረችው፡፡ ሰዎችን ከመለየቷ በፊት ስልኬን ነው የለየችው፡፡
የኔን ስልክ አባቷ ሲነካ ታለቅሳለች፡፡ የአባቷን ስልክ እኔ ከነካሁት ይከፋታል፡፡ የአባቷና የኔ ስልክ ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ እንዴት እንደምትለየው ከፈጣሪ በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ እኛ ራሱ ለመለየት የምንቸገረውን እሷ እንዴት አትቸገርም?
ስልኬ ላይ የሚገኝን ፎቶ ለሰው ለማሳየት እንኳ ስሞክር ልጄ ይከፋታል፡፡ ያ ስልክ የኔ ብቻ መሆኑን ነው የምታውቀው፤ ከኔ ቀጥሎ ደግሞ የሷ ነው፡፡ የሌላ የማንም አይደለም፡፡"
የዚች ልጅ ባህሪ የብዙ ልጆችን ባህሪ ይወክላል፡፡ አደገኛ የስክሪን ትውልድ ነው እየመጣ ያለው፡፡
የዛሬ ልጆችን ምንም ነገር እንደ ፊልም ቀልባቸውን አይሰርቅም፡፡ ምንም ነገር እንደ ጌም አይገዛቸውም፡፡ ጠዋት ማታ ታብሌትና ላፕቶፕ ላይ ነው የሚጣዱት፡፡ ብርድ ልብሳቸው ከስክሪን ቢሰራላቸው ደስታቸውን አይችሉትም፡፡ እንቅልፍን የሚጠሉት ከስክሪን ስለሚለያቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡
ይህ ታዲያ እንዴት አያስጨንቅም? እንደ ወላጅ ያስጨንቃል፡፡
ለነገሩ ልጆችን በስክሪን ሱስ እንከሳለን እንጂ እኛ ብንሆን? አንብስም?
‹እኔ ለምሳሌ የስክሪን ጊዜ ለመቀነስ ብዙ ጥሬ አልተሳካልኝም› ትላለች የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ፡፡
"…እጄ ተምዘግዝጎ ቦርሳዬ ውስጥ ገብቶ ስልኬን መዞ ያወጣዋል፡፡ በስልክ ጉዳይ እጄን አእምሮዬ አያዘውም፡፡ የራሱ ጭንቅላት አለው፡፡ ስልኬን ይነካካል፡፡ ከጀመረ ማቆም ያቅተዋል፡፡ ምሽቴ በቴሌቪዥን የተሞላ ነው፡፡ መሥሪያ ቤት ላፕቶፕ ላይ ተጥጄ ነው የምውለው፡፡…
በስልኬ ማኅበራዊ ሚዲያን እቃኛለሁ፣ ከዲጂታል ጉሊት አስቤዛ እገዛበታለሁ፣ መኪና ስነዳ አቅጣጫ ይመራኛል፣ ከዚህም ሁሉ አልፎ መጻሕፍትን ማንበብ ስፈልግ የድምጽ ንባብ አደርግበታለሁ፡፡ ታዲያ እኔ ማን ነኝ?"
ጸሐፊዋ ትቀጥላለች…
ሕይወቴ መቼ ከስክሪን ተላቆ አያውቅም፡፡ አሁን ደግሞ ይህ አባዜ ወደ ልጄ ተዛምቷል፡፡
ከኔ ይልቅ የልጄ በስክሪን ሱስ መጠመድ ያሳስበኛል፡፡ ሳይንስ ስለዚህ ነገር ምን ይል ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Vystekimages
የስክሪን ጥሩና መጥፎዎች
ሳይንስ ስክሪን ለልጆች መጥፎ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በድፍኑ! ነገር ግን ሊያሳስበን አይገባም ይላል፡፡ ምክንያቱም በአግባቡ ከሆነ ብዙ ትሩፋቶችም አሉት፡፡
አዲስ ቴክኖሎጂዎች በየዘመኑ ሲመጡ ኅብረተሰብ ላይ ሽብር ይነዛል፡፡ ሬዲዮ ሲፈጠር እንዲያ ነበር፡፡ ቴሌቪዥን ሲፈጠር ጉድ ፈላ ተብሏል፡፡
ፈላስፋው ፕላቶ ሳይቀር ግጥምና ድራማ በተፈጠረበት በዚያ ዘመን ወጣቶች አእምሯቸው ሊበከል ይችላል ሲል ስጋት ገብቶት ነበር፡፡
በተለይ ቴሌቪዥን ቤት ውስጥ በገባበት ዘመን የቤተሰብ ሕይወት አበቃለት ተብሎ ነበር፡፡ ‹‹ይሄ አራት መአዘን ሳጥን የማያሳየው ጉድ የለም፣ ኅብረተሰብ ተበከለ፣ ባሕል ተቀየጠ፣ እሴት ተናደ›› ተብሎ ብዙ እዬዬ ተብሏል፣ በዚያ ዘመን፡፡ ምናልባት ለዚህ ይሆን ‹‹ቻርሊ ኤንድ ዘ ቼኮሌት ፋክተሪ›› በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፉ የሚታወቀው ደራሲ ሮልድ ዳህል ድሮ በ1964 እንዲህ ሲል የገጠመው፡-
"So please, oh please, we beg, we pray,
"Go throw your TV set away,
"And in its place you can install
"A lovely bookshelf on the wall."
የግጥሙን መንፈስ ብንተረጉመው ይህን ሊመስል ይችላል፡-
እረ እናንተ ሰዎች ተው ተለመኑ፣ ሰው የሚላችሁን ስሙ
ይሄን ቴሌቪዥን አውጥታችሁ ጣሉ፣ ልጃችሁን ሳሙ
ይልቅ በዚያ ስፍራ ስቀሉ ሳጥን
መጽሐፍ ደርድሩበት በዕውቀት የሚያጥን፡፡
ምንም እንኳ መጻሕፍት ለልጆች ዕውቀትን ለመመገብ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም ይህ ማለት ግን ልጆች ቴክኖሎጂ አመጣሽ ከሆኑ ነገሮች ምንም አያተርፉም ማለት አይደለም፡፡
ልጆች እያደጉ ያሉት በስክሪን ተከብበው ነው፡፡ ወደፊት የሚጠብቃቸው ዓለም ከስክሪን የራቀ አይደለም፡፡ ስለዚህ በተመጠነ መልኩ ከስክሪን ጋር ዕውቂያ ቢኖራቸው ልንሰጋ በፍጹም አይገባም፡፡ በዚህ ዓረፍተ ነገር ሊሰመርበት የሚገባው ‹የተመጠነ› የሚለው ቃል ነው፡፡
እርግጥ ነው የልጆች የስክሪን ሱስ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስፈሪ ስለመሆኑ አሐዞች ያሳብቃሉ፡፡ ገና 2 ዓመት ያልሞላቸው ሕጻናት በቀን በአማካይ 3 ሰዓት በስክሪን አፍጥጠው ይቆያሉ፣ በአሜሪካ፡፡ ይህ አሐዝ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ይህ ጥሩ ዜና አይደለም፡፡
ይልቅ የልጆቻችን የስክሪን ቆይታ በበዛ ቁጥር ልንደነግጥ ይገባል፡፡ ለምን?
ምክንያቱም የስክሪን ቆይታቸው ስለልጆቻችን ብዙ የሚነግረን ነገር ስላለ ነው፡፡ አንደኛ ልጆች ስክሪን ላይ አፈጠጡ ማለት እንቅስቃሴያቸው ተገደበ ማለት ነው፡፡
ወደ ደጅ ወጥተው መጫወት እያስጠላቸው ይመጣል ማለት ነው፡፡
ከሰው ጋር ማውራት ቶሎ ይሰለቻቸዋል ማለት ነው፡፡
ለእራት ወደ ጠረጴዛ ለመቅረብ እንኳን ይሰንፋሉ፡፡
ከሶፋው ጋር የተሰፉ ነው የሚመስሉት፡፡
ልጆችዎ ስክሪን ላይ ተጣብቀው ዋሉ ማለት ሌላም ትርጉም አለው፡፡
ይህ ማለት ልጅዎ ለአላስፈላጊ ውፍረት ተጋለጠ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የበሽታዎች ማደሪያና መዋያ ለመሆን በዝግጅት ላይ ነው ማለት ነው፡፡
ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር ደጅ ወጥተው ቢጫወቱ እጅግ ጤናማ መሆኑን ሳይንስ ደጋግሞ ደርሶበታል፡፡
የስክሪን ሰዓታቸው ሲጨምር ሌላም አደጋ አለው፡፡
እንቅልፍ እምቢኝ ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ ኢንሶምኒያ ይይዛቸዋል፤ የእንቅልፍ እጦት በሽታ፡፡
ቦዲ-ማስ-ኢንዴክስ (BMI) የክብደትና ቁመት ምጣኔ ማሳያ ነው፡፡ ሰውነት ብዙ ስብ እንዲያከማች የሚገደደው እዚያው በልተን እዚያ ተዘፍዝፈው በሚውሉ ልጆች ላይ ነው፡፡
ልጆች ደግሞ ወዲያ ወዲህ እያሉ ካልተንቀሳቀሱ አደጋ ነው፡፡ በልጅነታቸው ሰውነታቸው ለበሽታ የተመቸ ሜዳ ይሆናል፡፡
አንድ ጥናት በመኝታ ክፍላቸው ቲቪ የገባላቸው ልጆች፣ ቲቪ በመኝታቸው ከሌለ ልጆች ይልቅ በአማካይ ግማሽ ሰዓት ያነሰ እንቅልፍ እንደሚተኙ ያስረዳል፡፡ ይህ ጥሩ ዜና አይደለም፡፡ ቲቪውን ከክፍላቸው ያውጡት፡፡

የፎቶው ባለመብት, Vystekimages
የስክሪን ትሩፋቶች
እስካሁን የነዛነው መረጃ ሽብርና ፍርሃት ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ነገር ግን የጤና አዋቂዎች ወላጆችን ያን ያህልም ስጋት አይግባችሁ ሲሉ ይመክራሉ፡፡
ሁሉም ልጆች በስክሪን በኩል የሚያዩት ነገር መቅሰፍት ይዞ አይመጣም፡፡ እንዲያውም ካወቅንበት ልጆችን ከስክሪን ተጠቃሚ ልናደርጋቸው እንችላለን፡፡
በቅድሚያ ለስክሪን መጋለጥ ያለባቸው ልጆች ቢያንስ 2 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ብቻ ነው፡፡ ከ2 ዓመት በታች ላሉ ልጆች ግን ስክሪን አደጋ ነው፡፡
ልጆች የስክሪን ሰዓታቸውን ከገደብነው ቀጥሎ ሊያሳስበን የሚገባው የሚያዩት ነገር ይዘት ነው፡፡
ብዙ ወላጆች በዚህ ረገድ ነገሩ ግድም አይሰጣቸው፡፡ የልጆች ሥነ ልቡና አዋቂዎች ግን ይዘት ወሳኝ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ ልጆች ማየት ያለባቸው በባለሙያዎች የተፈቀዱ ይዘቶችን ብቻ ነው፡፡
በተለይም ከ3-5 ዓመት ያሉ ልጆች ለእድሜያቸው የተመጠነ ይዘት ያላቸውና የአእምሮ ልቀት (Cognitive skills) ላይ ያተኮሩ የቲቪ ትእይንቶችን ብቻ ቢመለከቱ ይመረጣል፡፡
‹‹ትምህርታዊ ይዘት ያላቸው የቲቪ ትእይንቶች ለልጆች ጎጂ አይደሉም፡፡ በተለይ ብዙ የልጆች ግብአት ለማያገኙ ልጆች እንዲያውም ጥሩ እድል ነው፡፡›› ይላሉ ካቲ ሂርሽ፤ ካቲ በቴምፕል ዩኒቨርስቲ፣ ፊላደልፊያ፣ የልጆች ቋንቋ ጥናት ተመራማሪ ናቸው፡፡
‹‹ነገር ግን ማታ የዓለም ዜና ቤተሰቡ ሲመለከት (አልጃዚራ፣ ቢቢሲ፣ ሲኤንሴን…) ልጆች አብረውን የሚመለከቱ ከሆነ እየጎዳናቸው እንጂ እየጠቀምናቸው አይደለም፡፡››
ለልጆች ያልተገቡ በይዘታቸው ነውጥ የሚበዛባቸው ጌሞች፣ ፊልሞችና አንዳንድ ጊዜም የዜና ዘገባዎች ለአዳጊዎች ጭንቅላት በፍጹም አይመከሩም፡፡ ያቀዣብሯቸዋል፡፡
በይዘታቸው አሳታፊ የሆኑ የስክሪን ቆይታዎች ይበልጥ ለልጆች ተመራጭ ናቸው ይላሉ ባለሞያዎች፡፡
ለምሳሌ በጥያቄ ቀስፎ የሚይዛቸው የጌም ዓይነት፣ ጠያቂና ሞጋች፣ አዝናኝና አስተማሪ የቲቪ ትእይንት እንዲሁም ታሪክን የሚነግር፣ ከሌላው ዓለም ካሉ ልጆች ጋር የሚያስተሳስር ማኅበራዊ ሚዲያ መጥፎ አይደለም፡፡
ልጆችን ከዘመድ አዝማድ፣ ከአክስት ልጆችና ሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር እንዲያወሩ ስክሪንን አንድ የመገናኛ መንገድ ማድረግም የሚበረታታ ነው፡፡
ከሁሉም አደጋ ተብሎ የሚታሰበው ልጆች ከስክሪን የሚመጣውን ነገር ተቀባይ ብቻ ሲሆኑ ነው፡፡ ይሄ ይጎዳቸዋል፡፡ አሳታፊ ይዘት ግን ይጠቅማቸዋል፡፡
አንድ ጥናት እንዳሳየው ልጆች አዲስ ቃላትን በመዝሙር ወይም ጠያቂና አሳታፊ በሆኑ ቪዲዮዎች የተሻለ መማር ይችላሉ፡፡ ያንን አዲስ ቃል በድግግሞሽ ከሚማሩት ይልቅ በተሳትፎ ቢማሩት የተሻለ ነው፡፡
ወላጆች በሥራ ይጠመዳሉ፡፡ ልጆች ሌላ ጣጣ እንዳይሆኑባቸው ይሰጋሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ፊልም ከፍተው ታብሌት/ስልክ/ላፕቶፕ ያስታቅፏቸውና ይገላገሏቸዋል፡፡ ልጆቹ ዝም ማለታቸው እንጂ የሚያዩት ነገር በልጆች አእምሮ ስለሚፈጥረው አሉታዊ ጎን ብዙም አይጨንቃቸውም፡፡
ይህ መጥፎ ነው፡፡ ስክሪን ልጆቹን ተቀባይ እንጂ ተሳታፊ አያደርጋቸውም፡፡ የስክሪን ሱሰኛ ሆነው እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል፡፡
ልጆች በስክሪን የሚያዩትን ነገር ከወላጆቻቸው ጋር ወይም ከእኩዮቻቸው ጋር እያወሩበት ቢመለከቱት በእጅጉ የተሻለ እንደሆነ ይመከራል፡፡
ይህ የሚመከረው የልጆች አእምሮ ዕድገት ገና ያልተጠናቀቀ ወሳኝ ሂደት ላይ በመሆኑና ለዕድገቱ ደግሞ ወሳኙ ነገር መቀበል ሳይሆን መሳተፍ በመሆኑ ነው፡፡ መቀበልና መሳተፍ ቁልፍ ቃላት እንደሆኑ ልብ ይበሉ፡፡
ለምሳሌ የ15 ወር ሕጻን ከስክሪን አዲስ ቃል ሊማር ይችላል፡፡ ትልቅ ልጅ እስኪሆን ግን ያንን ቃል ለመተግበር ሊቸገር ይችላል፡፡ አሳታፊ ስክሪኖች ግን ይህን ችግር ይቀርፉታል፡፡ ልጆቹ ቃሉን እንዲደግሙት፣ ከጓደኞቻቸው ጋር እንዲያወሩበት ያበረታታቸዋል፡፡
ሌላ አንድ ሰፋ ያለ ጥናት ስክሪን ላይ አድፍጠው የሚቀመጡ ልጆች የፈጠራና ምናባዊ ምሥሎችን የመፍጠር አቅማቸው እየተዳከመ እንደመጣ አሳይቷል፡፡
ምናባዊ ምሥል ማለት የሰውን፣ የቦታንና የጽንሰ ሐሳብን ሁኔታ በምሥለ አእምሮ ቅልብጫ አድርጎ መመልከትና ያንን ለሌሎች መግለጽ መቻል ማለት ነው፡፡
ልጆች ይህን ክህሎት እንዲያዳብሩ ከእውናዊው ዓለም ጋር መስተጋብር እንዲፈጥሩ ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ በተለይ መጻሕፍት እያነበቡ ቢያድጉ የተሻለ ጽንሰ ሐሳብን የመረዳት፣ ምሥለ አእምሯቸውም በፍጥነት የመዳበር ዕድል ይኖረዋል ይላል ሳይንስ፡፡
ስክሪን የምሥለ አእምሮ ሥራን ያራክሳል፣ ስክሪን ዓይንና ጆሮን እንጂ ሌሎች የስሜት ህዋሳቶችን አያሳትፍም፡፡ ይህ በራሱ ለልጆች ሁለንተናዊ እድገት ደንቃራ ነው፡፡
አንድ ጥናት ተካሄደ፡፡
ጥናቱ ዕድሜያቸው 3-9 የሚደርሱ 266 ልጆችን ቀኑን ሙሉ የሚከታተል ነበር፡፡ በ10 ወራት ውስጥ የምሥለ አእምሮ ወይም ምናባዊ መረዳት (imagery) የሚለካ ፈተና ቀረበላቸው፡፡
የጥናቱ ውጤት እንዳሳየው በስክሪን ብቻ ዓለማቸው የተገደቡ ልጆች ስለነገሮች ምናባዊ መረዳታቸው አንሶ ተገኘ፡፡
ይህም ልጆች ይበልጥ መማር የሚችሉት ነገሮችን እያደረጉ፣ እየነኩ፣ እየኖሩ መሆኑን አሳየ፡፡
ልጆች በስክሪን አንድ ነገር ስላዩ ብቻ ተማሩት ማለት አይደለም፡፡ የሚሰጣቸው ትርጉም ውስብስብ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም አእምሯቸው አልጎለበተም፡፡
ስክሪን ቀጥተኛ ተሳትፎ (Active participation)ን ሳይሆን የተዘዋዋሪ ተሳትፎን (Passive participation) የሚያበረታታ መሣሪያ ስለሆነ ነው እምብዛምም ለልጆች የአእምሮ ልቀት የማይመከረው፡፡
ይህን ቀለል ባለ ቋንቋ ለማስቀመጥ እንሞክር፡-
አንዲት ሕጻን ልጅ በስክሪን ሳምንቱን ሙሉ ዳክዬ አሻንጉሊቶች ሲዋኙ የሚያሳይ ፊልም እየተመለከተች ቆየች እንበል፡፡ ይቺ ልጅ ይህንን የዋና ስሜት መረዳት፣ በምናብ ማቆየትና በአእምሮዋ ማደርጀት ይሳናታል፡፡ ለምን?
ምክንያቱም ሁሉም የስሜት ሕዋሳቶቿ ተሳትፎ አላደረጉም፡፡
ነገር ግን በሳምንት ሁለት ጊዜ ዋና ቦታ እናቱ ይዛው የምትሄድ ሌላ ሕጻን፣ ስለ ውሀው፣ ስለ ዋና ቦታ መስተጋብር፣ ስለ መቅዘፍ፣ መንሳፈፍና ተያያዥ ስሜቶች በስክሪን መቶ ጊዜ ከተመለከተች ልጅ የላቀ ግንዛቤን ያዳብራል፡፡
ይህ ለምን የሚሆን ይመስላችኋል? ምክንያቱም ስክሪን ለሕጻናቱ ያደርግላቸዋል እንጂ አያሳትፋቸውም፡፡ እንዳደረጉት እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ ሰነፍ ወይም ስልቹ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡
ሁሉም ነገር እንዲደረግላቸው ብቻ ፈላጊ ይሆናሉ፡፡ ተሳትፎን ይጠላሉ፡፡ እራት ብሉ ሲባሉ ይነጫነጫሉ፡፡ እራቱን ራሱ በስክሪን በኩል ቢመጣላቸው ይመርጣሉ፡፡
ተመራማሪዋ ሂርሽ ፓስክ ደምዳሚያቸው ይህ ነው፡-
በዚህ ዘመን ከስክሪን መላቀቀ የሚቻል አይደለም፡፡ የስክሪን ጊዜን መገደብ፣ የስክሪን ይዘትን መምረጥ፣ አሳታፊ የሆኑ የስክሪን ይዘቶችን ማበረታት መልካም ግን ይቻላል፡፡
ከዚሁ ሁሉ በላጩ ግን ልጆች ደጅ ወጥተው ሁሉንም ነገር እያደረጉት ቢማሩ ነው፡፡















