ሴኔጋላዊ ወንዶችን ልጅ እንዲያዝሉ ያደረገችው የፎቶ ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
በሴኔጋል መዲና ዳካር ጎዳናዎች ላይ ወንዶች ልጆቻቸውን በጀርባቸው አዝለው ፎቶ ማንሳቷ ይህንን ያህል ግርምት ይፈጥራል ብላ ባታስብም ከማህበረሰቡ ያገኘችው አድናቆት እንዳስደመማት የፎቶ ባለሙያዋ ማርታ ሞሬይራስ ትናገራለች።
በጎዳናዎች ላይ ፎቶ በምታነሳበትም ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሕዝብ ተከብባ የነበረ ሲሆን ይሄም ለሥራዋ አስቸጋሪ እንደነበር ስፔናዊቷ የፎቶግራፍ ባለሙያ ትናገራለች፤ "የሚያጨበጭቡ ነበሩ፤ በአንዳንድ አጋጣሚም የተሰሰበው ሕዝብ ከፍተኛ በመሆኑ ፎቶ ለማንሳት እክል ፈጥሮብኝ ነበር" ብላለች።
አክላም "መንገድ ላይ ፎቶ ሳነሳ የሚያገኙኝ ሴቶች በሙሉ በደስታ ጨብጠውኝ 'እንዲህ ዓይነት ነገር በየቀኑ እኮ አያጋጥምም፤ እስቲ ባሌን ልደውልለት' ይሉኛል።
ሥራዎቿ በዚህ ዓመት የሶኒ ዓለም አቀፍ የፎቶ ሽልማት ላይ ለእጩነት ከተመረጡት መካከል ሲሆኑ ሃሳቡም የመጣላት ሴኔጋልን ከ11 ዓመታት በፊት በጎበኘችበት ወቅት ያነሳቻቸውን ፎቶዎች ስታገላብጥ አብዛኛው የፎቶዎቿ ስብስብም ሴቶች ልጆች አዝለው የሚያሳይ የነበረ ሲሆን፣ ያም ወንዶች ለምን እንደማያዝሉም ጥያቄ እንዳጫረባት ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
ሴኔጋል የሚገኙ ወንዶች ጓደኞቿም ጋር በመደወል ልጆቻቸውን ያዝሉ እንደሆነ በምትጠይቅበት ወቅትም ያገኘችው ምላሽም በቤት ውስጥ እንደሚይዙ ነገር ግን በአደባባይ በፍፁም እንደማያዝሉ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
ያደረገችው ጥናትና ቃለ መጠይቆች እንደሚያሳየው ዳካር በጣም ውድ ከሚባሉት ከተሞች አንዷ በመሆኗና ባልና ሚስቱም ውጭ ሥራ ስለሚሠሩ ባሎች ልጅ የመንከባከቡን ሚና እንደሚወጡ ነው።
ያነጋገረቻቸው ወንዶች እንደገለፁላት ከሆነ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ተከፋፈለው ይሠራሉ። ብዙዎቹ ልጅ የመንከባከቡንም ሆነ፣ የማስጠናቱን ጉዳይ ለባለቤቶቻቸው እንደማይተዉና በከፍተኛ ሁኔታ ይሳተፋሉ።
"ባለቤቴም እንደኔ ውጭ ትሠራለች፤ እና የቤቱን ሥራ እንዴት ብቻዋን ትወጣዋለች?" በሚልም አንደኛው አስተያየቱን ሰጥቷል።
"ምንም እንኳን ወንዶች በልጆች አስተዳደግ ላይ ቢሳተፉም አባቶች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ፣ ትምህርት ቤት ሲወስዷቸው ወይም ሲያጥቧቸው አይታዩም" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
ያነጋገረቻቸውን አባቶችም የአባትነት ሚናቸውን ሲወጡ በሚያጎላ መልኩ ፎቶ ማንሳትም ጀመረች።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
በመጀመሪያ ልጆቻቸውን አቅፈው ፎቶ ለመነሳት ሲስማሙ፤ አዝላችሁስ ብላ በምትጠይቅበት ወቅት በአብዛኛው ያገኘቸው ምላሽ ልጆች አዝለን ጎዳና ላይ አንወጣም የሚል ቢሆንም ማርታ ተስፋ ሳትቆርጥ ቀስ በቀስ ምቾት ሰጥቷቸው እንዲነሱ እንዳግባባቻቸው ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
ፎቶዎቹን ለማንሳት እሰከ ሦስት ወር የፈጀባት ሲሆን ባለፈው ዓመትም በነበረው በጥበቡ ዓለም ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠው የዳካር ኮንቴምፖራሪ ዓውደ ርዕይም ላይ ሥራዎቿን አቅርባለች።
ሥራዎቿም በአውደ ርዕዩ ላይ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
ፎቶዎቿ በማህበረሰቡ አመለካከት ላይ የተለየ ሃሳብን መፈንጠቅ የቻለ ሲሆን በተለይም ታዋቂው ራፐር ባዱ መሳተፍ ከፍተኛ ተፅዕኖን መፍጠር ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
"በማህበረሰቡ ዘንድ ስመጥር የሆኑ ወንዶች መሳተፋቸው ለብዙዎች አርዓያ ከመሆኑም በላይ ወንዶች ልጆች ማዘላቸው ምንም ማለት አይደለም የሚለውን ውይይት ለመፍጠር ምክንያት ሆኗል" ትላለች ማርታ
ሌሎች ታዋቂ ሰዎችንም በፎቶዎቿ እንዲካተቱ ብትጠይቅም ለስማቸው ፈርተው አይሆንም እንዳሏትም ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Marta Moreiras
ፎቶዎቹ የተገኙት ከማርታ ሞሬይራስ ነው












