ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶቿን መልሳ ለመክፈት ምን አይነት ዝግጅቶችን አድርጋለች?

ተማሪዎች በመማር ላይ

የፎቶው ባለመብት, DEA / C. SAPPA

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ትምህርት ቤቶችን ዘግታ የነበረችው ኢትዮጵያ በያዘችው አዲሱ አመት እንዲከፈቱ ወስናለች።

የመማር ማስተማሩም ሂደቱ የትምህርት ቤት ማህበረሰቡን ደህንነትና ጤንነት ባስጠበቀ መልኩም እንዲሆን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችንም ትምህርት ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላትም እያካሄዱ ነው።

ከነዚህም መካከል በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስን ማቅረብም አንዱ እንደሆነም የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሚዩኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሐረግ ማሞ ለቢቢሲ እንደገለፁት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሙቀት መለኪያ፣ እና የንጽህና መጠበቂያ በአገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው።

ተማሪዎች፣ መምህራንና በአጠቃላይ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ አገሪቱ ተቀብላ ተግባራዊ ስታደርጋቸው የነበሩ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችንም በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ግዴታ መቀመጡንም ዳይሬክቶሬቷ አፅንኦት የሰጡበት ጉዳይ ነው።

የመማር ማስተማሩን በአዲስ መልኩ ከመመለስ ጋር ተያይዞም ሲነሳ የነበረው የ8ኛ ክፍልና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች የሚሰጡበት ቀንና በምን መንገድ የሚሉትም ጥያቄዎች ባለፈው ሳምንት ምላሽ አግኝቷል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ መሰረት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ. ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ መሆናቸውን አስታውቋል።

በተመሳሳይ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁ እና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ጠቁሟል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴሩ በኦንላይን (በበይነ መረብ) እንደሚሰጥም ገልጿል።

በአገሪቷ ካለው የኢንተርኔት ስርጭት ማነስና የአቅርቦቱ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ቢነሳም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መመረጣቸውን ኃላፊዋ ገልፀዋል። ከኢንተርኔት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችንም ለመቅረፍ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቴክኖሎጂ በኩል የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመስጠት ችግር ያጋጥመናል ብለው እንደማያስቡ የሚናገሩት ሐረግ ከኢንተርኔት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ነው ብለዋል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ዝግጅት ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንገዶች እገዛ ያገኙ የነበሩ ተማሪዎች ነበሩ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ምዘናው እንዴት ሁሉንም የአገሪቱን ተማሪዎች በእኩል ያማከለ መሆን ይችላል? ተብሎም ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊዋ የፈተና አወጣጥ ስርዓቱ ሁሉን ባማከለ መልኩ እንደሚሆንና "በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ያሉትን ተማሪዎች ባማከለ መልኩ እንዲሆን ነው ያደረግነው" ሲሉ መልሰዋል።

ተማሪዎቹ ለፈተናው እንዲዘጋጁ 45 ቀናት የሚሰጣቸው ሲሆን ቀዳሚው ስራ ተማሪዎቹን በስነልቦና ከትምህርት ቤቱ ጋር የማገናኘት ስራ እንደሚሆንም ያስረዳሉ። ጎን ለጎን ደግሞ ያልተሸፈኑ የትምህርት ክፍሎች፣ ክለሳዎች፣ የማካካሻ ስራዎች እንደሚሰሩ ይናገራሉ።

ብሔራዊ ፈተና ከሚወስዱት በተጨማሪ አገሪቷ በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶችን ከሶስት ሳምንት በኋላ እንደምትከፍት አስታውቃለች። ትምህርት ቤቶቹንም በሶስት ዙር ለመክፈትም ምክረ ኃሳብ ቀርቧል።

በዚህም መስረት በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መጀመሪያ በተባለው ዙር ጥቅምት 9/2013 ዓ.ም፣ በሁሉም ዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛው ዙር ጥቅምት 16/2013 እንዲጀምሩ ሃሳብ ቀርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን የሚገኙት ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር በሦስተኛ ዙር ብሎ ባስቀመጠው ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ይጀምሩ የሚል ምክረ ሐሳብ መቅረቡ ተገልጿል።

ትምህርት ቤቶቹን በተለያየ ጊዜ በሶስት ዙር ለመክፈት የተወሰነውም ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘም እንደሆነ ኃላፊዋ ይናገራሉ።

የቫይረሱ ስርጭት ሰፋ ብሎ የሚታይባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶቹ የሚከፈቱት በሶስተኛው ዙር መሆኑንም ያስረዳሉ።

በተለያዩ ጊዜና ዙር ትምህርት ቤቶቹን ለመክፈትም ትምህርት ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ያገኘውን መረጃም በማጠናቀርም እንደሆነ ኃላፊዋ ያስረዳሉ።

ኃላፊዋ እንደሚገልፁት ትምህርት ቤቶችን መክፈትና መደረግ ያለባቸው ምክረ ኃሳቦች ከመቅረባቸው በፊትም ትምህርት ሚኒስቴሩ ያቋቋመው ግብረ ኃይል የመማሪያ ክፍሎች ጥበትና እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች ገምግሟል።

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ክልሎች ከሰጡት መረጃ በመነሳት በአንድ ክፍል የተማሪ ጥግግት ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ትምህርት በፈረቃ እንዲሆን መወሰኑን ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ምን ያህል ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ሊማሩ ይገባል ብሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባጤነው መሰረትም ከ20-25 ተማሪዎች እንዲሆኑም መስሪያ ቤቱ ወስኗል። ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፍም በትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚገኙ አንዳንድ ተቋማትን ታሳቢ ተደርገዋልም ይላሉ።

ተቋማት በሌሉበት ሁኔታም ደግሞ ጊዜያዊ መጠለያ በመገንባት በነዚያ ውስጥ ለማስተማርም ትምህርት ሚኒስቴር እቅድ ይዟል።

በአጠቃላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአንድ ጊዜ በትምህርት ቤት የሚገኙ የተማሪዎችን ቁጥርም ለመቀነስ የተለያዩ አማራጮችን የሚጠቀም ሲሆን ከነዚህም መካከል በሶስት ፈረቃ መክፈልና የትምህርት አሰጣጡን በቀናት መከፋፈልም ይገኙበታል።

ትምህርት በሚከፈትበት ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ የኮሮናቫይረስ ስጋቶችን ለመቀነስ ዝግጅት አድርጌያለሁ ያለው ሚኒስቴሩ የመምህራን እጥረትም ካጋጠመ አማራጭ እቅዶችን አቅርቧል።

በአካባቢው ያሉ በጎ ፈቃደኞችንና በጡረታ የተገለሉ ነገር ግን እድሜያቸው ያልገፉ መምህራን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግም ታስቧል።

ሆኖም በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን የመምህራንን ቁጥር በተመለከተ ተጨማሪ መምህራን ሳያስፈልጉ ባሉት ብቻ መሸፈን የሚቻልባቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም የመስሪያ ቤታቸውን መረጃ ዋቢ አድርገው ኃላፊዋ ያስረዳሉ።

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ መምምህራን ከተቀመጠላቸው የክፍለ ጊዜ መጠን በላይ እንደማይይዙና ይህንንም መደረግ በማይቻልባቸው ትምህርት ቤቶች ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ እንደሚደረግ እንዲሁም መመረቂያ ጊዜያቸው የደረሱ መምህራን በፍጥነት ተመርቀው ወሰደስራ እንደሚገቡ አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ተማሪዎች ለሰባት ወር ያህል ከትምህርት ገበታ ርቀው ቆይተዋል።

ከ12 እና ከስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች በስተቀር ተማሪዎች በግማሽ ዓመቱ በነበራቸው ውጤት መሰረት ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዘዋወሩም ተደርጓል።

ትምህርት ቤቶች ዝግ በነበሩባቸው በእነዚህ ወራት ልጆች ለተለያዩ የጉልበት ብዝበዛ ተዳርገዋል፣ በርካታ ህፃናት ያለ ዕድሜ ጋብቻ ተጋልጠዋል እንዲሁም ፆታዊ ጥቃቶችም ደርሶባቸዋል።

በዚህም የተነሳ ለስነልቦና ጫና ተጋልጠው መቆየታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚረዳ ኃላፊዋ አብራርተዋል።

እነዚህን ክፍተቶችና ችግሮችም በመረዳት በዘንድሮው የትምህርት ዓመት እነዚህ ልጆች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ ክልሎች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን አደረጃጀት ተጠቅመው ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ተቋማት እንዲመጡ እንዲያደርጉ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች ተጠናቅቀው የኮሮናይረስ ምልክቶች የሚታይባቸው መምህራን እና ተማሪዎች ቢኖሩ ከዚህ ቀደም ይደረጉ የነበሩ መካላከሎችና መመሪያዎችም ተግባራዊ ይሆናሉ ብለዋል።