አማርኛ ቋንቋ : ቻይና ውስጥ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ሊሰጥ ነው

ቻይና እና ኢትዮጵያ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Pool

ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ባለፉት አስር ዓመታት በፈጠረችው በቻይና ዜጎች መካከል የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ፍላጎት እጨመረ መምታቱ ተነገረ።

በቤይጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ በሚንስትር ማዕረግ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ፍጹምብርሃን ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በቻይና መዲና በሚገኘው የቤይጂንግ የውጪ ጥናት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የአማርኛ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ሊሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ዲፕሎማቱ ጨምረውም በቻይናውያን ዘንድ የአማርኛ ቋንቋን ለመማር ያለው ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱና የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየጠነከረ ስለሆነም ቋንቋውን በመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት መወሰኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት በቤይጂንግ የሚገኘው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባለው የአፍሪካ ጥናት ማዕከል ከዚህ ዓመት ጀምሮ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ይሰጣል።

አቶ ሳሙኤል ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እያጠናከረች መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህል ትስስርም እየተፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ናት። አማርኛ ቋንቋም የረዥም ዘመን የጽሑፍ ታሪክ ስላለው ቋንቋውን ማወቅ የአገሪቱን ባህልና እሴት ለማወቅ ያስችላል” ብለዋል።

የአማርኛ ቋንቋን ለመማር ፍላጎት ያላቸው እንዲመዘገቡ የተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ 30 ቻይናውያን ተመዝግበው፤12ቱ የትምህርቱን የመጀመሪያ ክፍል መከታተላቸውንም አቶ ሳሙኤል አክለዋል።

በቻይና የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ በዲግሪ ደረጃ መስጠት ሲጀመር በመምህርነት አዲሱን የቋንቋ ትምህርት የሚሰጡት፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዶ/ር ስንቅነሽ አጣለ እና በአማርኛ ቋንቋ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሠሩ ቻይናዊት አማካይነት ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በቻይና ውስጥ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የሌሎችም ዘርፎች ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋን በተጨማሪነት ይወስዱ እንደነበር ተገልጿል።

በዚህም በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ ተማሪዎች አማርኛን በተጨማሪነት (ኢሌክቲቭ ኮርስ) ይማሩ እንደነበርና አሁን ወደ ሙሉ ጊዜ የዲግሪ ትምህርት መሸጋገሩን አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል።

ዲፕሎማቶች፣ ነጋዴዎችና በሌላም ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦች አማርኛ የመማር ፍላጎት እንዳላቸው ኃላፊው ይናገራሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ ጥናት መሥራት ለሚፈልጉ እንደሚረዳም ያክላሉ።

“ቻይናውያን ኢትዮጵያ ሲሄዱ አስተርጓሚ ይፈለጋሉ። ለወደፊት በዲፕሎማትነት ተመድበው የሚሠሩም አሉ። ትምህርቱ ለሥራና ከኅብረተሰቡ ጋር ለመግባባትም ይረዳል” ይላሉ።