ልደቱ አያሌው ፡ በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ ፍርድ ቤት ወሰነ

አቶ ልደቱ አያሌው

ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌውን ለማስለቀቅ የሚያስፈልገው የዋስትና ገንዘብ ተከፍሎ ከእስር መውጣታቸው እየተጠበቀ መሆኑ ተገለጸ።

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሚያስፈልገው 100 ሺህ ብር ዋስትና ለሚመለከተው አካል ገቢ ተደርጎ አቶ ልደቱን ለማስፈታት ታስረው ወደሚገኙበት ቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ የአቶ ልደቱን ጉዳይ የተመለከተው የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት ነው አቶ ልደቱ በዋስ ከእስር እንዲወጡ የወሰነው ሲሉ ከጠበቆቻቸው መካከል አንዱ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ከቀናት በፊት ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበረ ይታወሳል።

ጠበቃ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ የክስ መቃወሚያና የዋስትና መብት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

የቀረበው የክስ መቃወሚያ አቶ ልደቱ ከቀረበባቸው የልተፈቀደ የጦር መሳሪያ አያያዝ ጋር የተገናኘ መሆኑን አቶ አብዱልጀባር ይናገራሉ።

ዐቃቤ ሕግ አቶ ልደቱ ላይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበባቸው ክስ የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3ን በመተላለፍ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ መሆኑ ይታወሳል።

ይህን አንቀጽ በመተላለፍ ክስ ሊመሰረት የሚችለው ሁለት እና ከሁለት በላይ የጦር መሳሪያ ሲገኝ ነው ይላሉ ጠበቃው አቶ አብዱልጀባር።

በአቶ ልደቱ መኖሪያ ቤት ተገኘ የተባለው አንድ የጦር መሳሪያ ብቻ መሆኑንም የጠቀሱት ጠበቃው፤ ስለዚህም በዚህ አዋጅ ሊከሰሱ እንደማይችሉ መቃወሚያ ማቅረባቸውን ጠበቃው ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የዋስትና መብት ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ አስታውሰዋል።

በዛሬው የችሎት ውሎ ፍርድ ቤቱ በቀረበው መቃወሚያ ላይ በቂ ጊዜ አግንቶ ውሳኔ ለመስጠት አለመቻሉን ጠቅሶ የቀረበው የዋትስና መብት ላይ ግን ውሳኔ መስጠቱን ጠበቃው አብዱልጀባር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በዚህም መሠረት በ100 ሺህ ብር ዋስ ከውጪ ሆነው እየተመላለሱ እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱ ወስኗል" ብለዋል።

"በአሁኑ ወቅት የአቶ ልደቱ ቤተሰቦች የተጠየቀውን የዋትስና መብት የግንዘብ መጠን ፍርድ ቤት ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ" ሲሉም አክለዋል።

አቶ ልደቱ አባል የሆኑበት ኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ አስፈላጊው የዋስትና ገንዘብ ማስያዙ ሂደት በመጠናቀቁ አቶ ልደቱ ዛሬ [ማክሰኞ] ካልሆነም በቀጣይ ቀን [ረቡዕ] ሊፈቱ እንደሚችሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ልደቱ አያሌው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ በተከሰተው አለመረጋጋት ሁከት በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርትረው ከአዲስ አበባ ተይዘው ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ታስረው እንደቆዩ ይታወሳል።

በኋላ ላይም ጉዳያቸውን ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት የክስ መዝገባቸውን ቢዘጋም በእስር ላእ ቆይተው ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ የመገኘት ክስ ተመስርቶባቸዋል።