አሜሪካ ኢራን ላይ የጣለችውን አዲስ ማዕቀብ ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ ጥላለች።
አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ እንዲጥል የጠየቀች ቢሆንም ሌሎች የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የአሜሪካንን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
እአአ 2015 ላይ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ኢራን የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሞቿ ላይ ገደብ ለማድረግ የተስማማች ሲሆን፤ ኃያላን አገራቱ ደግሞ በምላሹ ኢራን ላይ ተጥሎ የሚገኘውን ማዕቀብ ለማቃለል ተስማምተዋል።
ትራምፕ ግን ከሁለት ዓመታት በፊት ይህ ስምምነት ለኢራን ጥቅም ያደላ ነው በማለት አሜሪካ ስምምነቱን ጥላ መውጣቷን ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ትራምፕ በኢራን ላይ ማዕቀቡ ዳግም እንዲጣል ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ አሜሪካ በተናጠል ማዕቀብ ጥላለች።
በዚህ መሠረት ለኢራን የጦር መሳሪያ የሚሸጥ አገርም ሆነ ኩባንያ በአሜሪካ ቅጣት ይጣልበታል።
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ከጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት አቋም በተለየ መልኩ ከኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው ከ20 በላይ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ኢራን ከሚፈቀድላት በላይ ዩራኒየም ማበልጸግ ጀምራለች እያሉ ይከሳሉ።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲም በተመሳሳይ ኢራን የደረሰችበትን ስምምነት በመተላለፍ ዩራኒየም እያበለጸገች ነው ይላል።
ኤጀንሲው እንዳለው ኢራን 2ሺህ 105 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበለጸገ ዩራኒየም አከማችታለች።
በዚህም ምክንያት አሜሪካ በኢራን ላይ ተፈጻሚነቱ እንዲገታ ተደርጎ የነበረው የተመድ ማዕቀብ ተፈጻሚ እንዲሆን በተደጋጋሚ ስትወተውት ቆይታለች።
ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት አባል አገራት የአሜሪካንን ጥያቄ ወድቅ አድርገውታል።













