ሩሃኒ አሜሪካ ለምታደርሰው ትንኮሳ ሽንፈት ትከናነባለች አሉ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሃኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP PHOTO / HO / IRANIAN PRESIDENCY

የኢራኑ ፕሬዝደንት ሃሰን ሩሃኒ አሜሪካ በአገራቸው ላይ ዳግም የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብን ለመጣል እየወሰደች ያለቸው እርምጃ “ሽንፈት ያከናንባታል” ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዝደንቱ ይህን ያሉት በቀጥታ የቴሌቪዥን ንግግራቸው ሲሆን፤ የአውሮፓ አገራት ማዕቀቡ ሕጋዊነት እንደሌለው እየገለጹ የትራምፕ አስተዳደር ማዕቀቡን ለመጣል የሚያደርገው ጥረት መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ አጣጥለዋል።

ዩናይትድ ኪንግድም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን አሜሪካ ኢራን ላይ ዳግመኛ ማዕቀብ መጣል ሕጋዊ አይሆንም ብለዋል።

ፈር ቀዳጅ ተብሎ በነበረው እና እአአ 2015 ላይ በተደረሰው ስምምነት ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና አሜሪካ ከኢራን ጋር በኒውክሌር መረሃ ግብሮቿ ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ግን ከሁለት ዓመታት በፊት ይህን ስምምነት ለኢራን ጥቅም ያደላ ነው በማለት አሜሪካ ስምምነቱን ጥላ መውጣቷን ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም። በዚህም ኢራን ከሚፈቀድላት በላይ ዩራኒየም ማበልጸግ ጀምራለች።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ እንዳለው ኢራን 2ሺህ 105 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበለጸገ ዩራኒየም እንዳከማቸች ያስታወቀው ከሶስት ሳምንታት በፊት ነበር።

ኢራን በፈረመችው ስምምነት መሠረት ማበልጸግ የምትችለው የዩራኒየም መጠን 300 ኪሎ ግራም ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ኢራን 2ሺህ 105 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበለጸገ ዩራኒየም አከማችታለች ብሏል።

በዚህም አሜሪካ በኢራን ላይ ተፈጻሚነቱ እንዲገታ ተደርጎ የነበረው የተመድ ማዕቀብ ተፈጻሚ እንዲሆን እንዲሁም በቀጣዩ ወር የሚያበቃው የጦር ማዕቀብ ቀጣይነት እንዲኖረው ጥሪ አቅርባለች።

ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት አባል አገራት የአሜሪካንን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።

አሜሪካ ከጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት አቋም በተጻረረ መልኩ ከኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ጋር ግነኙነት አላቸው ባለቻቸው ከ20 በላይ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ የራሷን ማዕቀብ እንደምትጥል ሬውተርስ ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ፕሬዝደንት ሩሃኒ ለህዝባቸው ባደረጉት የቴሌቪዥን ንግግር አሜሪካ ኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የተምትወስደውን እርምጃ “ትንኮሳ ነው” ያሉት ሲሆን፤ “አሜሪካ በማዕቀቦቿ ላይ ሽንፈት እያጋጠማት ነው . . . ከዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ተቀባይነት እያጣቸው ነው” ብለዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል አገራቱ ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን አሜሪካ በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ እንዲጣል ጫና መፍጠሯ ሕጋዊ መሠረት የለውም ብለዋል።

የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴርም በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል።