ሱዳን ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ልዑኮቿን ወደ ዱባይ ላከች

ማይክ ፖምፒዮና አብደላ ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, SUDAN GOVERNMENT

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ። [ፖምፔዮ ወደ ሱዳን በመጡበት ወቅት]

ሱዳን ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ለመደራደር ከፍተኛ ልዑኮች ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መላኳን አስታወቀች።

በአሜሪካ ለሽብር ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ለመውጣት ሱዳን ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

ከዚህ ቀደም የነበረው የአል-በሽር መንግሥት ከአሜሪካ ጋር የነበረው ግንኙነት መልካም የሚባል አልነበረም።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት አሜሪካ ሸብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ትፍቀኛለች ብሎ ተስፋ አድርጓል።

ይህ ማለት ሱዳን እጅግ የተጠማችውን ዓለም አቀፍ ብደር እና የውጭ ኢንቨስትመንት ማግኘት ትችላለች።

የሱዳን ልዑክ በሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር እና የሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ በሆኑት ሉቴናንት ጄነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራ ሲሆን ልዑኩ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በምን ጉዳዮች ሊያወራ እንደሚችል በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ የሱዳን እና የአሜሪካ ልዑኮች በዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች በሁለት ጉዳዮች ላይ ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ይታመናል።

ሱዳንን ለአሸባሪዎች ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ለመፋቅ ሱዳን መክፈል ስላለባት ካሳ እንዲሁም ከእስራኤል ጋር ግንኙነትን ማሻሻል የሚሉት አይቀሬ አጀንዳዎች ናቸው የሚሉት በርካቶች ናቸው።

አሜሪካ ከዚህ ለሽብር ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት ከሚለው ዝርዝር ውስጥ ሱዳንን የማስወጣው ሱዳን በሽብር ጥቃቶች ጉዳት ለደረሰባቸው አሜሪካውያን 330 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ስትችል ነው ትላለች።

ከዚህ በተጨማሪ የትራምፕ አስተዳደር ለመካከለኛው ምስራቅ ስላምን ለማምጣት እስራኤል ከአረቡ ዓለም ጋር ያላትን ግነኙነት የምታሻሽልበት ስምምነት ማምጣት ትልቁ አጀንዳቸው ነው። በትራምፕ እቅድ ውስጥ ሱዳን የዚህ አንድ አካል እንደምትሆን ይገመታል።

ባለቤትነቱ የሱዳን መንግሥት የሆነው ሱና የዜና ወኪል በሉቴናንት ጄነራል አብዱል ፋታህ የሚመራው ልዑክ ወደ ኤሜሬቶች የመራው ሱዳን ለሽብር ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት ዝርዝር ስለምትወጣበት መንገድ ለመምከር ነው ሲል ዘግቧል።

የአሜሪካው አክሲዎ በበኩሉ በኢሚሬቶች መዲና አቡ ዳቢ የሚደረገው ድርድር ዋነኛ አጀንዳ በእስራኤል እና ሱዳን መካከል ግነኙነትን ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው ሲል ዘግቧል። የአሜሪካው ልዑክም በመካከለኛው ምስራቅ የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ሚጉኤል ኮሬአ የሚመራ መሆኑን አክሲዮ ጠቅሷል።

በበርካታ ሱዳናውያን ዘንድ ከእስራኤል ጋር ግነኙነት የማሻሻል ሃሳብ አጨቃጫቂ ነው። ቀደም ሲል ሉቴናንት ጄነራል አብዱል ፋታህ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር በኡጋንዳ መገናኘታቸው በሱዳን እስላማዊ ሚሊሻዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ከሳምንታት በፊት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ ወደ ካርቱም ማቅናታቸው ይታወሳል። ይህም ፖምፔዮን ከረዥም ዓመታት በኋላ አሜሪካን የጎበኙ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል።

በፖምፔዮ ጉብኝት ወቅት የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አበደላ ሃምዶክ የሚመሩት የሽግግር መንግሥት ከእስራኤል ጋር ግንኙነትን በማሻሻል ጉዳይ ላይ ለመወያየት ሕጋዊ ስልጣን የለውም ብለው ነበር።

አሜሪካ ሱዳንን በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያካተተችው እአአ 1993 ሲሆን ለዚህም ከምክንያቶች መካከል አንዱ የቀድሞ የአል-ቃኢዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን በሱዳን ለአምስት ዓመታት መኖሩ ነው።