ኢራን ከተፈቀደላት በላይ የበለጸገ ዩራኒየም አከማችታለች ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢራን ከፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት በተጻረረ መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው የበለጸገ ዩራኒየም ማከማቸቷን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ እንዳለው ኢራን 2ሺህ 105 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበለጸገ ዩራኒየም አከማችታለች።
ኤጀንሲው ይህን ያለው ከሁለቱ የኢራን ዩራኒየም ማብለያ ጣቢያዎች በአንዱ ፍተሻ ካካሄደ በኋላ ነው።
ኢራን በተደጋጋሚ የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ግልጋሎቶች ብቻ እንደሚውል ስታሳወቅ ቆይታለች።
ኢራን እአአ 2015 ከፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ዩኬ እና አሜሪካ ጋር የፈረመችውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ወደጎን በመተው ባሳለፍነው ዓመት በይፋ ከተፈቀደላት በላይ ዩራኒየም ስታበለጽግ ነበር።
በዚህ ደስተኛ ያልነበሩት ዶናልድ ትራምፕ እአአ 2018 ላይ ከኢራን ጋር የተደረሰውን ስምምነት አሜሪካ ጥላ መውጣትን ይፋ በማድረግ በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ኢራን በፈረመችው ስምምነት መሠረት ማበልጸግ የምትችለው የዩራኒየም መጠን 300 ኪሎ ግራም ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ኢራን 2ሺህ 105 ኪሎ ግራም የሚመዝን የበለጸገ ዩራኒየም አከማችታለች እያለ ነው።
የዘረፉ ባለሙያች ግን ምንም እንኳ ኢራን ያከማቸችው የበለጸገ ዩራኒየም መጠን ከፍተኛ ይሁን እንጂ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት ገና ብዙ ርቀት ይቀራታል ይላሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት ኢራን የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ መርማሪ አባላት የዩራኒየም ማበልጸጊያ ማዕከሎቿን እንዲጎበኙ መፍቀዷን አሳውቃ ነበር።
ኤጀንሲው በበኩሉ ኢራን ይፋ ስላላደረገቻቸው የኒውክሌር ቁሶች ለሚቀርቡላት ጥያቄዎች ምላሽ አትሰጥም የሚል ቅሬታ ያቀርባል።












