የጣት አሻራ አልባው ቤተሰብ

የሰው ልጆች አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበት የጣት አሻራ በእነአፑ ቤተሰብ ውስጥ አይታወቅም።

የፎቶው ባለመብት, Sarker

የምስሉ መግለጫ, የሰው ልጆች አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበት የጣት አሻራ በእነአፑ ቤተሰብ ውስጥ አይታወቅም።

አፑ ሳርከር 22 ዓመቱ ነው። ባንግላዲሽ በሚገኘው ናቶሬ ግዛት ከቤተሰቡ ጋር ይኖራል።

አፑና ቤተሰቡ ከአብዛኞቻችን ይለያሉ። አሻራ የላቸውም።

የሰው ልጆች አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበት የጣት አሻራ በእነአፑ ቤተሰብ ውስጥ አይታወቅም።

አፑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሕክምና ባለሙያዎች ተባባሪነት ይሠራ ነበር። አባቱና አያቱ አርሶ አደሮች ናቸው።

ቤተሰቡ ውስጥ ያሉት ወንዶች የጣት አሻራን የሚያጠፋ የዘረ መል መዋቅር ነው ያላቸው። ይህ በመላው ዓለም በጣም ጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት ነው።

የአፑ አያት ያለ ጣት አሻራ መወለዳቸው ብዙም አይገርማቸውም ነበር። የእለት ከእለት ሕይወታቸውን ከማከናወንም አላገዳቸውም።

በዚህ ዘመን ግን ነገሮች ተለውጠዋል። የጣት አሻራ መታወቂያ ለማውጣት እና ለሌሎችም ክንውኖች ቁልፍ ግብአት ነው።

የአንድ ማኅበረሰብ ነዋሪዎችን በአስተዳደራዊ መዋቅር ለመመዝገብ እጅግ አስፈላጊ ከሆነው የግል መረጃ አንዱ አሻራ ነው።

የጣት አሻራ በዓለም ላይ በስፋት ከተመዘገቡ የግል መረጃዎች ቀዳሚነቱን ይዟል።

የጣት አሻራ ምዝገባ በምርጫ ድምጽ ለመስጠት፣ በአውሮፕላን ለመጓጓዝ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ ለመክፈት ወዘተ. . . ይውላል።

"አሻራ ስለሌለኝ መንጃ ፍቃድ ማግኘት አልቻልኩም"

እአአ በ2008 ባንግላዲሽ የብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት ዘረጋች።

መታወቂያ ለማውጣት አሻራ መስጠት ግዴታ ነበር።

የቀበሌ ሠራተኞች የአፑ አባት አማል ጣት ላይ አሻራ ሲያጡ ግራ ገባቸው።

አማራጭ ስላልነበራቸው መታወቂያው ላይ 'አሻራ አልባ' ብለው ጻፉበት።

2010 ላይ ደግሞ ፓስፖርትና መንጃ ፍቃድ ለማውጣት አሻራ ያስፈልጋል የሚል መርህ ወጣ።

አማል ከሕክምና ባለሙያዎች የተሰጣቸውን አሻራ አልባለታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ይዘው መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ሄዱ። ብዙ ጊዜ መመላለስ ነበረባቸው።

"ክፍያ ፈጽሜ፣ ፈተና ወስጄ ባልፍም አሻራ ስለሌለኝ መንጃ ፍቃድ ማግኘት አልቻልኩም" ይላሉ።

ሞተር ሳይክል መንዳት የሚመርጡት የጣት አሻራ የሚጠይቃቸው ስለሌለ ነው።

መኪና ሲነዱ መንጃ ፍቃድ ለማውጣት የከፈሉበትን ደረሰኝ ይዘው ነው። ትራፊክ ሲያስቆማቸው ሁኔታውን ለማስረዳት ቢጣጣሩም፤ የሚረዷቸው ፖሊሶች ጥቂት ናቸው። ከዚህ ቀደም ከአንድም ሁለቴ የትራፊክ ፖሊስ ገንዘብ ቀጥቷቸዋል።

የጣት አሻራ የሌለው ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, Sarker

"በጣም የሚሰለቸኝ ሁኔታዬን ለእያንዳንዱ ሰው ደጋግሞ ማስረዳት ነው"

2016 ላይ ባንግላዲሽ ውስጥ ሲም ካርድ ለማውጣት አሻራ መስጠት ግዴታ ሆነ። ይህ ሕግ ለአማል ልጅ አፑ መሰናክል ነበር።

"የጣት አሻራ የሚሰጥበት መተግበሪያ ላይ መዳፌን ሳስቀምጥ ምንም አያነብም" ሲል አፑ ያስታውሳል።

እሱና ሌሎቹም የቤተሰቡ ወንድ አባላት አሻራ ስለሌላቸው ሲም ካርድ ማውጣት አልቻሉም።

እናም የሁሉም ሲም ካርድ የተመዘገበው በእናትየው ስም ነው።

እንደነሱው ሁሉ የጣት አሻራ የሌላቸው ሰዎች በእንግሊዘኛው Adermatoglyphia የሚባል የዘረ መል መዋቅር አላቸው። ችግሩን የደረሰበት ስዊዛዊው የቆዳ ሀኪም ፕ/ር ፒተር ሊቲን ነው።

አንዲት ወጣት አሜሪካ መግባት እንዳልቻለች ስትገልጽለት ነበር ምርምር የጀመረው። ይህቺ ሴትና ሌሎች ስምንት ቤተሰቦቿ አሻራ የላቸውም።

ጣቶቻቸው ባለ መስመር ሳይሆን ልሙጥ ናቸው። እጃቸው ውስጥ ያሉ ላብ አመንጪ ህዋሳትም ጥቂት ናቸው።

ሰባት አሻራ ያላቸው እና ዘጠኝ አሻራ አልባ የቤተሰቡ አባላት ላይ የዘረ መል ምርመራ ከተደረገ በኋላ ነበር ውጤቱ የተገኘው።

ፕ/ር ፒተር ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ እስካሁን የጣት አሻራ አልባ ተብለው የተመዘገቡ ቤተሰቦች በጣም ውስን ናቸው።

የጣት አሻራ የሌላቸው ሰዎች ተያያዥ ህመም እንደሌላቸው ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰሩ ይህንን የቆዳ ሁኔታ "ጉዞ አሰናካዩ ህመም" ሲሉ ይጠሩታል። አንድ ሰው አሻራ ከሌለው በአውሮፕላን ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ እንደሚቸገር ከግምት በማስገባት ነው ስሙን ያወጡለት።

ህመሙ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር ይችላል።

የእነአፑ ቤተሰብ ቆዳቸው ይደርቃል። ብዙም አያልባቸውም። ፕ/ር ፒተር የቤተሰቡ ቆዳ ላይ ምርምር መሥራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የአፑ አባት በእሳቸው ዘመን ያለ ጣት አሻራ መኖር ብዙም እንደማይከብድ በማስታወስ፤ ለልጆቻቸው ይሰጋሉ።

እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከአሻራ ጋር እየተሳሰረ በመጣበት በዚህ ዘመን የወንድ ልጆቻቸው እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አሳስቧቸዋል።

አማል እና አፑ የሕክምና ማስረጃ አሳይተው በቅርቡ ልዩ ብሔራዊ መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል። መታወቂያው በጣት አሻራ ምትክ ፊት የሚያነብ ነው።

"በጣም የሚሰለቸኝ ሁኔታዬን ለእያንዳንዱ ሰው ደጋግሞ ማስረዳት ነው። ሌላ አማራጭ ካላገኘሁ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ" ይላል አፑ።

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፓስፖርት አውጥቶ ከባንግላዲሽ ውጪ የሚጓዝበትን ይናፍቃል።