1ሺ ሄክታር የሚሰፋው የማይክል ጃክሰን የመኖርያ ግቢ በ22 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

ማይክል ጃክሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ዘ ኔቨርላንድ' በሚል ስሙ የሚታወቀው የሟቹ ማይክል ጃክሰን መኖርያ ቤት መሸጡን ለጉዳዩ ቅርብ ነን የሚሉ ሰዎች ተናገሩ።

ይህ እጅግ ግዙፍ መኖርያ የሚገኘው ከሎስ ኦሊቮስ ከተማ ቀረብ ባለ ጫካ በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ነው።

ንብረቱን የገዙት ቢሊየነር ቤቱ ያወጣል ተብሎ ከተጠበቀው አንድ አራተኛውን ብቻ ከፍለው ነው የራሳቸው ያደረጉት።

ይህ የማይክል ጃክሰን የቀድሞ መኖርያ ግቢ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ ይችላል ተብሎ ተገምቶ ነበር።

ቤቱን የገዙት ቢሊየነር ሮን በርከል የሚባሉ ሰው ናቸው ተብሏል።

ዜናውን የዘገበው ዎል ስትሪት ጆርናል ሲሆን በዚህ ግዢኛ ሽያጭ በቀጥታ የተሳተፉ ሦስት ሰዎችን በምንጭነት ጠቅሷል።

ይህ የማይክል ጃክሰን ግቢ ስፋቱ 2ሺ 700 ኤከር ወይም 1ሺ 100 ሄክታር የሚሸፍን እጅግ ግዙፍ መኖርያ ግቢ ነው።

በካሊፎርኒያ ግዛት ከሳንታ ባራባራ ከተማ በስተ ሰሜን አቅጣጫ የሚገኘው ይህ እጅግ ግዙፍ መኖርያ ግቢ የማይክል ጃክሰንን ሞት ተከትሎ ሊሸጥ ዋጋ ሲወጣለት ለዓመታት ሲንከባለል ቆይቷል።

በ2015 የቤቱ ግምት 100 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ግን በ31 ሚሊዮን ዶላር ሊሸጥ ነው የሚሉ ዜናዎች መውጣት ጀምረው ነበር።

ማይክል ጃክሰን ቤቱን መጀመርያ ሲገዛው በ19 ሚሊዮን ዶላር ተኩል ነበር። የቤቱን ስምም በልጆች ዝነኛ የተረት ተረት ታሪክ ፒተር ፓን ውስጥ ባለው ደሴት ስም ሰይሞት ነበር።

በተረቱ ዓለም ውስጥ ይህ ደሴት ልጆች የማያድጉበት ዓለምን የሚወክል ነው።

ማይክል ይህንን ቤት የገዛው እንደነሱ አቆጣጠር በ1987 ነበር። በዚያ ጊዜ ትሪለር የተሰኘውን ሙዚቃ ያወጣበት እና በዝና ማማ ላይ የወጣበት ዘመን ነበር።

ይህንን ቤቱን ወደኋላ ላይ የመዝናኛ ስፍራ አድርጎት ቆይቷል።

ግቢው ከስፋቱ የተነሳ እጅግ ግዙፍ የእንሰሳት መጠበቂያ (zoo)፣ የአእዋፋት መናኸሪያ፣ የዲዝኒላንድ ሁሉም ዓይነት መጫወቻና መዝናኛዎች፣ በርካታ ሲኒማ ቤቶች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ መለስተኛ ባቡር መጓጓዣዎችና በናቱ ስም የተሰየመ የባቡር ጣቢያ ያሉት ምናልባትም አንድ አነስተኛ የገጠር ቀበሌን የሚያህል ስፋት ያለው ነው።

በዚህ ስፍራ ሕጻናትና ቤተሰቦቻቸው እንዲዝናኑበት በማሰብ አካባቢውን በከፊል የመዝናኛ ማዕከል አድርጎትም ነበር ማይክል ጃክሰን።

ኔቨርላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኔቨርላንድ መኖርያ ቤቱ ተከፍተው የማያውቁ፣ አንድም ቀን አንድም ሰው አድሮባቸው የማያውቁ በርካታ ክፍሎች ያሉ ሲሆን በግቢው ውስጥ የመኖርያ ቤት ሕንጻዎች ቁጥር ግን 22 እንደሆነ ይታወቃል።

በጊዜው ከ120 በላይ የቤት ሰራተኞች የነበሩት ማይክል ለደመወዝ ብቻ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ዶላር ያላነሳ የወጣ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ማይክል በዚህ ስፍራ ይኖር የነበረው በርካታ ሕጻናት ጋር ሲሆን ፖሊስ ይህንን ግቢ ድንገት በመውረር ማይክል ይታማበት የነበረውን ከልጆች ጋር ጾታዊ ፍላጎት አለው በሚል ክስ መስርቶበት ነበር።

ፖሊስ ማይክልን በዚህ ግቢ ውስጥ ሕጻናትን ያባልጋል፣ ምናባዊ ዓለም ሊፈጥር ፈልጓል በሚል ከሶት ነበር። ማይክል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ክዶ ተከራክሯል።

በ2005 ማይክል የ13 ዓመት ልጅን አባልገሀል በሚል ክስ ቀርቦበት ፍርድ ቤት ነጻ አድርጎት ነበር። ከዚህ በኋላ ይህንን ኔቨርላንድ ግቢ ጠልቼዋለሁ አልመስም ብሎ ስፍራውን ትቶት ኖሯል።

እንዳለውም ማይክል ጃክሰን ወደ ኔቨርላንድ የተጠንጣለለ ቤቱ ሳይመለስ ነው የኖረው።

ከአራት ዓመታት በኋላ በ2009 ማይክል ጃክሰን ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ሌላ መኖርያ ቤቱ ውስጥ ከልብ ጋር በተያያዘ በሽታ፣ ከመጠን ያለፈ ብዙ መድኃኒት በመውሰዱ ለሞት መዳረጉ አይዘነጋም።

ሞቱን ተከትሎ በርካታ የምርመራ ዘጋቢ ፊልሞች በዚህ ኔቨርላንድ መኖርያ ቤቱ ዙርያ ተሰርተዋል። ማይክል ጃክሰን በዚህ ግዙፍ ቤቱ ውስጥ ያልተገቡ ምናባዊ የሚመስሉ ድርጊቶችን ይፈጽም እንደነበረ የሚገምቱ ፊልም ሰሪዎች ጥርጣሪያቸውን የሚያንጸባርቁ መረጃዎችን አሰራጭተዋል።

ኔቨርላንድ ግቢ የማይክል ጃክሰንን ሞት ተከትሎ ስሙን ወደ ሲካሞር ቫሊ በመቀየር እድሳት ተደርጎለት ነበር።

አሁን ይህንን ታሪካዊና ግዙፍ ንብረት የግሉ ያደረጉት ቢሊየነሩ ሚስተር በርክል አካባቢውን ምን ሊሰሩበት እንደሆነ ይፋ አላደረጉም።

ሆኖም ግን ይህንን ቤት ለመግዛት ሐሳቡ እንዳልነበራቸውና በዚያ ስፍራ በሄሊኮፕተር ሲንሸራሸሩ ከሰማይ ላይ ካዩት በኋላ ፍላጎት እንዳደረባቸው አብራርተዋል።

የ68 ዓመቱ በርክል የዩዋኪፓ ኩባንያ መሥራችና ባለቤት ሲሆኑ ፎርብስ በያዝነው ወርና ዓመት ጠቅላላ ሀብታቸውን 1 ቢሊዮን ተኩል ገምቶታል።