ፍርድ ቤት በጣሊያን ኤምባሲ ላሉት የቀድሞ ባለስልጣናት አመክሮ ፈቀደ

ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ

የፎቶው ባለመብት, ADDIS FORTUNE

የምስሉ መግለጫ, ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ

ለሠላሳ ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ በጥገኝነት የቆዩት ሁለት የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከኤምባሲው እንዲወጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአብላጫ ድምጽ ወሰነ።

ሠላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ በጥገኝነት የቆዩት እነዚህ ከፍተኛ ባለስልጣናት ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ ናቸው።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ሁለቱን ግለሰቦች በተመለከተ የቀረበውን የአመክሮ አቤቱታ ከመረመረ በኋላ በኤምባሲው ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የቆዩት የቀድሞ ባለስልጣናት ካሉበት ቦታ ነጻ ሊወጡ ይገባል ሲል በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።

ጉዳዩን ለመመልከት ከተሰየሙት ዳኞች መካከል አንደኛው ግለሰቦቹ ፍርድ አግኝተው ቅጣታቸውን በማረሚያ ቤት ያልተቀበሉ በመሆናቸው "ከመደበኛው የአመክሮ ሥርዓት ውጪ የአመክሮ ጊዜያቸው እንደደረሰ በመቁጠር እንዲለቀቁ ከውሳኔ መደረሱ" ላይ ልዩነት እንደላቸው ማሳወቃቸውን ፋና ዘግቧል።

በደርግ የስልጣን ዘመን ተፈጽመዋል በተባሉ ከፍተኛ ወንጀሎች ከሌሎች የወቅቱ ከፍተኛ ባለስልጠናት ጋር በሌሉበት ተከሰው የነበሩት ሁለቱ ግለሰቦች የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው ነበር።

የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባን ከመያዙ አንድ ቀን ቀደም ብለው በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ከተጠለሉት አራት የወቅቱ ከፍተኛ ባለስልጣንት መካከል የነበሩት ብርሃኑ ባይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ሌፍተናንት ጀነራል አዲስ ተድላ የሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ነበሩ።

ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ ከእስር ቤት ውጪ ለ30 ዓመታት ያህል በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ከቆዩ በኋላ፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በግለሰቦቹ ላይ የተላለፈው የሞት ቅጣት ውሳኔ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየር ለአገሪቱ ፕሬዝደንት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር የዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪ ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሞት ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲሻሻል መፍቀዳቸው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ይፋ ተደርጓል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለቢቢሲ እንደገለጹት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩት ሁለቱ የቀድሞ ባለስልጣናት፤ የሞት ፍርዳቸው ወደ እድሜ ልክ እስራት በርዕሰ ብሔሯ ተቀንሶላቸዋል።

ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በደርግ መንግሥት ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ የተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው ነው የሞት ቅጣት የተበየነባቸው።

ዐቃቤ ሕግም በተመሳሳይ የተላለፈባቸው የሞት ፍርድ ወደ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀነስ በይቅርታ እና የምህርት ቦርድ በኩል ለርዕሰ ብሔሯ ጥያቄ ማቅረቡ ተነግሯል።

ሁለቱ የቀድሞ ባለስልጠናት ለዓመታት ተጠግተውበት ከነበረው ኤምባሲ እንዲወጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሰጠው በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሠረት ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የሞት ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀነስ ካደረጉ በኋላ በዐቃቤ ሕግ በአመክሮ እንዲለቀቁ በቀረበ ጥያቄ ነው።

የኢህአዴግ ኃይሎች አዲስ አበባን ለመያዝ አንድ ሳምንት ሲቀራቸው የወቅቱ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ስልጣናቸውንና አገራቸውን ለቀው አስካሁን ድረስ በጥገኝነት ወደሚገኙባት ዚምባብዌ ካቀኑ ከሳምንት በኋላ ነበር ባለስልጣናቱ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ የገቡት።

ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እንዲሁም ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ በውቅቱ ተይዘው ከነበሩ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በስልጣን ዘመናቸው ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው በሌሉበት የሞት ቅጣት ተወስኖባቸው ነበር።

መንግሥትም የጣሊያን መንግሥት ተፈላጊዎቹን አሳልፎ እንዲሰጠው በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ጣሊያን ጥያቄውን ሳትቀበለው ግለሰቦቹን አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲዋ ውስጥ አስጠግታ 30 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ለቀሩት ጊዜ አቆይታቸዋለች።

በወቅቱ በኤምባሲው ውስጥ ጥገኝነት በመጠየቅ ገብተው የነበሩት ከፍተኛ ባለስልጣናት ስምንት የነበሩ ሲሆን አራቱ በእራሳቸው ፈቃድ ኤምባሲውን ለቀው መውጣታቸው ይነገራል።

አሁን ኤምባሲው ውስጥ ከሚገኙት ከኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጀነራል አዲስ ተድላ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም አገር ለቀው ሲሄዱ ለቀናት የመሪነት ቦታውን ይዘው የነበሩት ሌ/ጀኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይሉ ይመኑ ይገኙ ነበር።

እነዚህ ከፍተኛ የቀድሞ ባለስልጣናት በኤምባሲው ውስጥ ጥገኝነት አግኝተው ለተለያዩ ጊዜያት ከቆዩ በኋላ እዚያው እንዳሉ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸው እንዳለፈ ይታወቃል።

ዚምባብዌ የሚገኙትንና በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በወቅቱ እጃቸውን ሰጥተው በነበሩ የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ በስልጣን ዘመናቸው ተፈጽመዋል በተባሉ ጥፋቶች የከባድ ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሂደቱ ለዓመታት ከተካሄደ በኋላ አብዛኞቹ የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ነገር ግን በእስር ላይ ሳሉ ህይወታቸው ካለፈው ውጪ ያሉት ባለስልጣናት ከ20 ዓመታት እስር በኋላ በምህረት ነጻ መውጣታቸው ይታወቃል።