ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን በተፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ገለፁ

የቤንሻንጉል ክልል የሚያሳይ ካርታ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል ገለፁ።

ቢቢሲ በተጨማሪ በጥቃቱ አካባቢ የነበሩ የዓይን እማኞችንና በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን በማናገር ለመረዳት እንደቻለው 120 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በጥቃቱ በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ለመግለጽ ባይችሉም ቁጥሩ "በጣም ከፍተኛ" እንደሆ ለቢቢሲ አረጋገጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ዛሬ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ በመተከል ስለደረሰው ግድያ "እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ ሆኗል። በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ" ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት ችግሩን ከሥሩ ለመፍታት " አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል" ብለዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ይህ ጥቃት በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገደሉትን ሰዎች አስመልክቶ ባወጣው መለግጫ "እጅግ አሰቃቂው ግድያ በክልሉ የሚኖሩ አማራዎች፣ ኦሮሞዎችና ሺናሻዎች ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ መንግሥት ብሔር ተኮር የሆነ ግድያን ለማስቆም በፍጥነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው" ብሏል።

ኮሚሽኑ ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የታጠቁ ኃይሎች በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ በተባለው ቀበሌ ውስጥ ጥቃቱን ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ መሆኑንና ጠቅሷል።

ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት የተፈጸመው የጥቃቱ ሰለባዎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩበት ወቅት ቤቶችን በማቃጠልና በተኩስ መሆኑም ተገልጿል።

አምንስቲ ከጥቃቱ ከተረፉ መካከል አምስት ሰዎች እንዳነጋገረና ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የቡለት ዞን ነዋሪ እንደሆኑ አሳውቋል። በተጨማሪም ሁሉም ድርጅቱ ያነጋገራቸው ሰዎች የታጠቁ የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች የአማራ፣ ኦሮሞና ሺናሻ ብሔር ተወላጆችን ቤት እየነጠሉ ጥቃት እንዳደረሱ ተናግረዋል።

ጥፋተኞች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ መንግስት በመተከል ዞን ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አምስት አመራሮችን በህግ ቁጥጥር ሥር ማዋሉን ትናንት ምሽት በክልሉ የመገናኛ ብዙኀን ላይ ይፋ አድርጓል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የኢፌዴሪ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ቶማስ ኩዊ፣ የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ፣ የቀድሞ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር፣ የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባንዲንግ ማራ፣እንዲሁም አቶ አረጋ ባልቢድ የመተከል ዞን የቀድሞ አመራር የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።

ኢሰመኮ ጥቃቱን በተመለከተ ተጎጂዎችንና ሌሎችንም በማነጋገር ባደረገው ማጣራት ጥቃቱ ለተፈጸመበት ቀበሌ የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን መረዳቱን አመልክቷል።

ጥቃቱ የተፈጸመባት በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ቡለን ከተማ 90 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ መሆኗን ጠቅሶ፤ በቀበሌው የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል።

አምነስቲ እንዳነጋገራቸው አምስት ሰዎች ምስክርነት ከሆነ ደግሞ ጥቃት አድራሾቹ ቤቶችን አቃጥለዋል፤ ሰዎችን በስለትና በጥይት ገድለዋል። እስካሁን ድረስ ቢያንስ 100 ሰዎች እንደተገደሉ ተዘግቧል።

የሞት ቁጥሩ አሁንም ሊጨምር እንደሚችል አምነስቲ ያሳስባል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚከታተለው ድርጅት መንግሥት ይህን 'አሰቃቂ ግድያ' እንዲመረምር ጥሪ አቅርቧል።"ጥቃት አድራሾቹ ለፍትህ መቅረብ አለባቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት መሰል ድርጊቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ሊከላከል ይገባል" ብለዋል የድርጅቱ ኃላፊ።

"አምነስቲ ኢንተርናሽናል በግሉ የአጥቂዎችን ማንነት ማረጋገጥ ባይችልም፤ ጥቃቱ በሥፍራው የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ይገመታል። ከመስከረም ወር ጀምሮ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ አማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሺናሻዎችና አገዎች ላይ ያነጣጠረ ተከታታይ ጥቃት እየተፈፀመ ነው።"

ኮሚሽኑ በበኩሉ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑና ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን አረጋግጧል።

"በተጨማሪም ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ሰዎች ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ደርሰውኛል" ሲል ገልጿል።

በጥቃቱ በሰው ሕይወትና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱና የተሰበሰቡ ሰብሎች በእሳት እንዲወድሙ መደረጋቸውን ኢሰመኮ አመልክቶ፤ ቢያንስ 18 ያህል የእህል ክምሮች ሲቃጠሉ የተመለከቱ አንድ ተጎጂን በእማኝነት ጠቅሷል።

ጥቃቱ ከበኩጂ ቀበሌ በተጨማሪ በጨላንቆና ዶሼ ቀበሌዎችም ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች እንዳሉ በመግለጽ፤ በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከጥቃቱ በኋላ ቀያቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆናቸው መረዳቱን አመልክቷል።

ኢሰመኮ እንዳለው አካባቢው የተመደበው የመከላከያ ሠራዊት ከጥቃቱ ቀደም ብሎ የፌዴራልና የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ ስፍራውን ለቆ መሄዱ ተከትሎ ጥቃት መፈጸሙናን እስከ እኩለ ቀን መቆየቱ ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ታህሳስ 13/2013 በመተከል በመገኘት ከነዋሪዎች ጋር በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ተነጋግረው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ታህሳስ 13/2013 በመተከል በመገኘት ከነዋሪዎች ጋር በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ተነጋግረው ነበር

ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የሺናሻ ተወላጆች ናቸው። ነዋሪዎቹ ጨምረውም በጥቃቱ በስምና በመልክ የሚያውቋቸው የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል።

ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን በተመለከተ የፌዴራሉና የክልሉን መንግሥታት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንዲያደርጉ ሲያሳስብ መቆየቱን ጠቅሶ "ይሁንና ጥቃቶቹ በመልክና በስፋት እየተባባሱ መጥተዋል" ብሏል።

ኮሚሽኑ በጥቃቱ ላይ ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረብ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር አሳስቧል።

ጨምሮም በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል።

የአካባቢው ባለስልጣናት ጥቃቱን የሚፈጽሙት ኃይሎችን "ጸረ ሠላም" ከማለት ውጪ ማንነታቸውና የጥቃቱ አላማ በግልጽ አይታወቅም። በተለያዩ ጊዜዎች በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች የተለያየ ቁጥር ያላቸው በጥቃቶቹ ተሳትፈዋል የተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

የግድያውን እውነተኛ መንስዔ የሚያጣራ ኮሚቴ ይቋቋም

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ፣ ኢዜማ በመተከል የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ ክልሉ የዜጎች መሰረታዊ መብት የሆነውን በሕይወት የመቆየት መብት ማስከበር ባለመቻሉ እና ድርጊቱ እየተደጋገመ በመምጣቱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካሁን የተፈጸሙት አሰቃቂ ወንጀሎችን ክልሉ ለምን ማስቆም እንዳልቻለ እውነተኛ መንስዔ የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቁሞ በአፋጣኝ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ጠይቋል።

አክሎም የፌደራል መንግሥት በሕግ አግባብ ጣልቃ በመግባት የዜጎቹን ሕይወት የመጠበቅ እና ሕግ የማስከበር ሥራውን ከማስጠበቅ በተጨማሪ አጥፊዎችን እና በክልሉ ያሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮችን ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስቧል።

በአካባቢው ለወራት በዘለቀው ጥቃት ሳቢያ ጸጥታውን ለመቆጠጠርና በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች ለማስቆም ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ የፌደራል መንግሥት ጦር ሠራዊትና የክልሉ የጸጥታ አካላት የተካተቱበት ኮማንድ ፖስት ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች መዋቀሩ ይታወሳል።

ነገር ግን አሁንም ድረስ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው። አሁን የተፈጸመውና ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት በአካባቢው ከተፈጸሙት ሁሉ የከፋው እንደሆነ ይነገራል።