ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፡ በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት ሰበብ 12 ሰዎች ተገደሉ

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ዱሃዝባጉና ቀበሌ በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ እሁድ ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ መከሰቱን አረጋግጠዋል።
እንደ ኃላፊው ከሆነ ማንዱራ ወረዳ ዱሃዝባጉና ቀበሌ አካባቢ ሦስት ሰዎች የአንድ ግለሰብን መሣሪያ ከመንጠቅ ባለፈ በስለት ጉዳት አድረሰውበት ከአካባቢው ተሰውረዋል።
ይህንንም ተከትሎ በስለት የተወጋው ግለሰብ ዘመድ በስሜት በመነሳሳት በጦር መሳሪያ በፈጸመው ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን አስረድተዋል።
ይህን ተከትሎም መሳሪያ የተነጠቀበት ግለሰብ ወንድም በፈጸመው ጥቃት የ12 የሰዎች ህይወት አልፏል ያሉት አቶ ጋሹ ከሟቾቹ በተጨማሪ አንድ ግለሰብ ጉዳት ደርሶበት የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል ብለዋል።
ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄ እንደሆነም አመልክተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ግጭቱ እንዳይስፋፋ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልሉ ጸረ ሽምቅ እና የፖሊስ አባላት አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ናቸው።
ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ የነበሩ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ እኩለ ሌሊት ገደማ ጥቃቱ መፈጸሙን አመልክተው "12 ሬሳ የወጣበት ቦታ ነው የምኖረው" በማለት ጥቃቱ ሲፈጸም ወደ ጫካ መሸሻቸውን ተናግረዋል።
"ትናንት ገበያ ስለነበር በቦታው ነበርኩ። በሰዓቱ ባጃጅም መኪናም አልነበረም። ዓይናችን እያየ፣ እየሰማን በየጫካው ተበትነን አደርን" በማለት በድንጋጤ ሌሊቱን ከቤታቸው ውጪ መሳለፋቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ ስናነጋግራቸው "አሁን አንድ ቤት ታሽገን፣ ታግደን ነው ያለነው" ብለዋል።
ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የክልሉ፣ የዞኑም ይሁን የቀበሌ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደማይወጡ አያይዘው ተናግረዋል።
"አመራሩ ደሞዙን እየበላ ሰላም በሚሆንበት ቀን መጥቶ ተከታትሎ ይሄዳል እንጂ ረብሻ በሚነሳ ቀን ሁሉም እዛው ይቀራሉ" ሲሉም ምሬታቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ ለቢቢሲ እንደገለጹት የተፈጠረው ግጭት በግለሰቦች መካከል ብቻ መሆኑን አመልክተው፤ የአካባቢው አመራር የነዋሪውን ደኅንነትና ሰላም ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ ግድያው የተፈጸመበት አካባቢ "በአንጻረዊ ሁኔታ ሠላም ነው" ያሉት አቶ መለሰ የአካባቢው አመራር ማኅበረሰቡን በማነጋገር ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የዓይን እማኙ "ስለዚህ እኛ ምንም ማድረግ አንችልም። እንወጣለን ስንል ደግሞ አናስወጣም ይላሉ። ታግደን ነው ያለነው" ሱሉም ስላሉበት ሁኔታ አስረድተዋል።
የክልሉ ባለስልጣናት እንዳሉት እሁድ ሌሊት የተፈጸመው ጥቃት ከዚህ ቀደም በክልሉ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር የማይገናኝ የግለሰቦች ግጭት ነው።
ካለፈው ዓመት ዓመት ማብቂያ አንስቶ በተጠናቀቀው የመስከረም ወር ጭምር በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ውስጥ ማንነታቸው ውል ያለተገለጸ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በፈጸሙ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ከክልሉ ጸጥታ ኃይል በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ የተሰማራ ሲሆን አካባቢዎቹ በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆኑ መደረጉ ይታወሳል።














