የዛሬ 30 ዓመት ተጠንስሶ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ሥዕላዊ መግለጫ

ጥቂት ጄኔራሎችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ኮ/ል መንግሥቱን ወደ ምሥራቅ ጀርመን (GDR) ለመሸኘት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኙ፡፡

በተቀራራቢ ሰዓት ሜ/ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ አሥመራ ለጄ/ል ደምሴ ቡልቶ የሚሰጥ ደብዳቤ ይዘው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ አቀኑ።


ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ቤተ መንግሥት ከሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ቢሯቸው በመሄድ ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ማድረግ ጀመሩ።


ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ከባለቤታቸውና ከሴት ልጃቸው ጋር በመሆን ወደ ምሥራቅ ጀርመን ለመብረር አውሮፕላን ተሳፈሩ።


ለሰባት ሩብ ጉዳይ ላይ የጓድ መንግሥቱ ሽኝትን ተከትሎ፣ 11 የሚሆኑ ጄኔራሎች ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ በሚገኘው መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ መፈንቅለ መንግሥቱን ለማቀነባበር በኅቡዕ ስብሰባ ተቀመጡ።
የጄኔራሎቹ ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። የፕሬዝዳንቱ አውሮፕላን ይመታ ወይም ተገዶ አሥመራ ይረፍ በሚለው ነጥብ ላይ አለመግባባት ተፈጠረ።


የዘመቻ መምሪያ ኃላፊውና የመፈንቅለ መንግሥቱ የዘመቻ አሰናጅ ጄ/ል አበራ አበበ የመከላከያ ሚኒስትሩን ጄ/ል ኃይለጊዮርጊስን ገድለው ከሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ተሰወሩ።

አየር ወለድ ኮማንዶ ስለነበሩ ምናልባት በአጥር ዘለው እንዳመለጡ ግምት ተያዘ።


‹‹ስፓርታ›› በሚባል የሚታወቀውና በሰሜን ኮሪያዎች የሰለጠነው ልዩ የአየር ወለድ ጦር 150 የሚሆኑ ኮማንዶዎች ከጦላይ አዲስ አበባ መገናኛ ሚኒስቴር አቅራቢያ ደረሱ።
በኋላም ወደ 4ኛ ክፍለ ጦር ተንቀሳቀሱ።


በጄ/ል ቁምላቸው ደጀኔና በሌ/ኮ/ል ካሳዬ ታደሰ የሚመራ በቁጥር ከአራት መቶ በላይ የሚሆኑ የልዩ ኮማንዶ አባላት በአራት አንቶኖቭ አውሮፕላን ተከታትለው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደረሱ።

ዓላማቸውም ለመፈንቅለ መንግሥቱ ሴረኞች ሽፋን መስጠትና ቁልፍ ተቋማትን መቆጣጠር ነበር።

የመከላከያ ሚኒስትሩን መገደል ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎችና አክሻፊዎች መካከል ንግግር ተጀመረ።
መልዕክተኞች የነበሩት ሌ/ጄ አዲስ ተድላና ሌ/ኮ ደበላ ዲንሳ ነበሩ።
ድርድሩ ፍሬ ባለማፍራቱ የጓድ መንግሥቱ ቀኝ እጅ የነበሩት ሻምበል መንግሥቱ ገመቹ እና የደህንነት ኃላፊው ኮ/ል ተስፋዬ ወ/ሥላሴ የሃገር መከላከያ ሚኒስትርን በልዩ ጥበቃ ብርጌድ ጦር በታንክና በብረት ለበስ አስከበቡ።

ምሽት አካባቢ ነገሩ ያበቃለት መሆኑን የተረዱት ጄ/ል መርዕድ ንጉሤና ጄ/ል አመሀ ደስታ ራሳቸውን በየተራ አጠፉ።


መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉን፣ ከሴረኞቹ መካከል ጄ/ል ፋንታ፣ ኮማንደር ኃይሌ እና ጄ/ል አበራ ለጊዜው መሰወራቸው በመገናኛ ብዙኃን ተነገረ።
ከሦስት ቀናት በኋላ ጄ/ል ፋንታ ከተደበቁበት የመከላከያ ሚኒስቴር ኮንቴይነር ወጥተው እጅ ሰጡ። ከጥቂት ወራት በኋላ ከማዕከላዊ ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ ተባለ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጄኔራል አበራ ጉለሌ አካባቢ ከተደበቁበት የዘመድ ቤት ተከበው ሳለ በጣሪያ ወጥተው ሊያመልጡ ሲሉ በአንድ ወጣት ፖሊስ ግንባራቸው ላይ ተመትተው ወደቁ።

ግንቦት 13፣ 1982 ለድፍን አንድ ዓመት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩት 12 ጄኔራሎች በስዒረ መንግሥቱ ተሳትፋችኋል በሚል በሞት እንዲቀጡ ተወስኖ ያንኑ ምሽት ይኸው ተፈጻሚ ተደረገ።














