ፊሊፒንስ፡ ሳይፈለጉ የተረገዙ 200ሺህ ልጆች በኮቪድ ቤት መዋል ምክንያት የተጸነሱ ይሆን?

ፊሊፒንስ ጎዳናዎች ነፍሰጡር ይበዛቸዋል። ሆስፒታል የአዋላጅ እጥረት አጋጥሞ ይሆናል፤ የዳይፐርና ጡጦ ገበያው ደርቷል። ለምን?
ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንዱ ግን ኮቪድ-19 ነው። የእንቅስቃሴ ገደቡ ሰዎች ቤት እንዲውሉ አስገደዳቸው።
ቤት ከዋሉ ደግሞ በድንገት የሚፈጥጠሩ ውልብታዎችና ብልጭታዎች ወደ አልጋ የሚያመሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
ከዚያ እርግዝና ይከተላል።
ሌላው ትልቁ ችግር የእንቅስቃሴ ገደቡ ሴቶች የእርግዝና መከላከያ አቅርቦት እንዳያገኙ ማድረጉ ነው።
ይሄን ነገር ለማሳየት ለምን የአጌዋን ተወላጅ የሮቬሊ ዛባላን ታሪክ አንጋራም?
ዛባላ ወፍራለች፤ ነፍሰጡር ናት። አሁን እንዲያውም ደርሳለች። የመጀመርያዋ እንዳይመስላችሁ።
ይህ 10ኛ እርግዛናዋ ነው።
አሁን 41 ዓመት ሆናት። ስታወራን ወገቧን ማዞር እንኳ አይሆንላትም። እርግዝናዋ ገፍቷል።
10ኛ ልጇ ሆዷ ውስጥ ሆኖ ይራገጣል። 9ኛው እቅፏ ላይ ይንፈራገጣል። እግሮቿ ሥር የሚርመሰመሱ "ለቁጥር የሚከብዱ" በሚል የሚጋነኑ ልጆች አሉ።
ልጅ አይቆጠርም ይባላል። እውነት ነው፤ አንዳንዱ ግን ብዙ ስለሆነ ነው የማይቆጠረው።
ዛባላን ባገኛናት ጊዜ ከእግሯ ሥር "ምድርን የሞሉትን" የአብራኳን ክፋዮች ልታስተዋውቀን ሞከረች።
"…ይሄኛው ካርል፣ ያኛው ጄውል፣ ይቺ ጆይሲ…" ልጆቿን ቆጥራ ሳትጨርስ ደከማት። በመሀሉ 6 ዓመት የሞላው ልጇ ጎሸም አደረጋት። ስሙን ተሳስታ ነው ለካስ። ማኩረፉ ነው። ተቃውሞውን መግለጹ ነው በሱ ቤት። እናቴ ሆነሽ ስሜን እንኳ በትክክል አታውቂውም እንደማለት…
"ውይ የኔ ነገር፣ ይሄ ጄዌል ሳይሆን ቻርሊ ነው። ተምታቱብኝ እኮ" ብላ ፈገግ አለች፤ በእናትነት፤ በቅንነት፣ እንዲሁም በቀናነት።
ዛባላ ስለቤተሰብ ምጣኔ የሰማቸው 7 ከወለደች በኋላ ነው።
10ኛ ልጅ የመውለድ ሐሳብ በጭራሽ አልነበራትም። ድንገት ላልተፈለገ እርግዝና ተጋለጠች። ኮቪድ-19 ነው ጉድ የሰራት።
በዚህ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት ፖሊሶች መንገድ ላይ ያገኙትን ሰው ተኩሰው እስከመምታት ደርሰው ነበር።
ምግብ ለመግዛት ከቤት መውጣት የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ነው።
በዚህ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የእርግዝና መቆጣጠርያ እንክብልም ሆነ ሌላ ዘዴን ለማግኘት ሳይቻላቸው ቀረ።
በዚህ ሁኔታ 200 ሺህ ልጆች ፊሊፒንስን ሊቀላቀሉ ተዘጋጅተዋል ይላሉ ጥናቶች።
የፊሊፒንስ የሥነ ሕዝብ ጥናት ኢንስቲትዩት በሠራው አንድ የዳሰሳ ጥናት 214 ሺህ ያልተፈለጉ ሕጻናት ተረግዘዋል። ይሄ ጥናት በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ተቋም የተደገፈ ነው።
ፊሊፒንስ ከኮቪድ-19 በፊትም ብዙ ልጆች እየተወለዱባት መፈናፈኛ እያጣች ያለች አገር ናት። ሆስፒታሎች ሁልጊዜም በደረሱ ሴቶች የተሞሉ ናቸው። የጨቅላ ሕጻናት ለቅሶ ብሔራዊ መዝሙሯ የሆነ ይመስላል።
በየዓመቱ ለ2 ሚሊዮን 300 ሺህ ብቻ የጎደላቸው ሕጻናት በፊሊፒንስ ምድር ይወለዳሉ።
የሚገርመው አብዛኞቹ ልጆችን ለመውለድ የሚገደዱት የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ቤተሰቦች መሆናቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሕዝብ ሞልቶ የተትረፈባት ማኒላ
የፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ ሕዝብ አሸዋ ነው። 13 ሚሊዮን ሰዎች ይርመሰመሳሉ።
በእያንዳንዱ ስኩዌር ኪሎ ሜትር 70 ሺህ ዜጎች ታጭቀዋል።
አየሩ የተበከለ ነው። መንገዶች በእግረኛና በተሸከርካሪ ጭንቅ ቁና ቁና ይተነፍሳሉ። ሰዎች ማደርያ ሞልቶባቸው ጎዳና ተጋድመዋል።
እስር ቤቶች እንኳ ሞልተው በሰው ላይ ሰው ይጋደማል። የአንዱ እስረኛ ጭንቅላት ለሌላው መከዳ ነው።
የፊሊፒንስ እስር ቤቶች ከሚችሉት በላይ በ300 እጥፍ ታሳሪ ታጉሮባቸዋል። የአገሪቱ አወዛጋቢው መሪ ዱቴርቴ የሚገድሉትን ገድለው የተረፈውን እስር ቤት ነው የሚወረውሩት።
በአደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች ጉዳይ ላይ ቀልድ አያውቁም። ለፖሊሶቻቸው 'ድፏቸው' ብለው በይፋ እስከመናገር የደረሱ ሰውዬ ናቸው።
ጭንቅ ጥብብ በሚሉት ሰፈሮች ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ዜጎች ናቸው የሚኖሩት።
በእነዚህ ሰፈሮች ብዙ ነዋሪዎች ከቆሻሻ ገንዳ የተገኘ የተጣለ ሥጋ ሳይቀር ለቅመው ይመገባሉ። በዚህ ሁሉ ድህነት ውስጥ ደግሞ ልጅ በላይ በላዩ ይወልዳሉ፤ ይዋለዳሉ።
አንዳንድ አጥኚዎች ድህነቱ የልቅ ሕዝብ ብዛት ውጤት ነው ብለው ያምናሉ። የወሊድ ምጣኔው ከፍተኛ ነው።
ከ1960ዎቹ ጀምሮ መንግሥት የወሊድ ምጣኔን ለመቀነስ ሞክሯል። አልተሳካለትም እንጂ። ያን ጊዜ 35 ሚሊዮን ብቻ የነበረው የፊሊፒንስ ሕዝብ አሁን ከ110 ሚሊዮን አልፎ ፈሷል።
ይህ ለምን ሆነ?
አንዱ ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ከሚከተለው እምነት ጋር ይተሳሰራል።
ፊሊፒንሶች በብዛት የጥብቅ ካቶሊክ እምነት ተከታዮች ናቸው። ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በእርግዝና መከላከያ አጠቃቀም ዙርያ ያላት አቋም ነገሩን እምብዛምም የሚያበረታታ አይደለም።
እንክብል ወስዶ ከማደር ይልቅ "ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሏት" የሚለውን መንፈሳዊ መርህ አንብቦ የሚተኛ ዜጋ ይበልጣል።
"እውነት ነው፤ የእርግዝና መቆጣጠሪያን አንደግፈውም" ይላሉ ቄስ ጀሮሜ ሲላኖ። ቄስ ጀሮሜ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አባት ናቸው።

'የልጅ መፈልፈያ ፋብሪካ"
የዶ/ር ጆስ ፋቤላ መታሰቢያ ሆስፒታል ሠራተኞች እረፍት የላቸውም። ለነገሩ በቀን 120 እናቶችን እያዋለዱ እንዴት እረፍት ይኖራቸዋል? ያውም ይህ አሐዝ የ2012 ነው።
ይህ ልዩ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ብዙ ልጆች ከማዋለዱ የተነሳ "የልጆች መፈልፈያ ፋብሪካ" የሚል ቅጽል ተሰጥቶታል።
በዚህ ሆስፒታል ማዋለጃ ክፍሎች ውስጥ በተዘዋወርን ጊዜ በአራስ ልጆች ወጀብ የተመታን ያህል ነበር የተሰማን።
ክፍሉ ግማሽ የእግር ኳስ ሜዳ ያክላል። ከብረት የተሰሩ አልጋዎች ተደርድረዋል። በአልጋና አልጋ መሀል ክፍተት እንኳን የለም። ሁለት አልጋ ተጋጥሟል። መሀሉ አንድ ተጨማሪ ሰው እንዲያስተኛ።
ጣሪያው ላይ የተንጠለጠሉት የሙቀት ማስተንፈሻ እርግብግቢቶች አርጅተው ሥራ አቁመዋል።
ክፍሉ የሰው ትንፋሽ ተጨንቋል። በጣም ብዙ እናቶች የማዋለጃ ቀሚስ ለብሰው ባለፉት ጥቂት ደቂቃዎች ወደዚህ ዓለም ያመጧቸውን ሕጻናት ታቅፈው ተቀምጠዋል።
ደግነቱ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብላቸው እንዳጠለቁ ናቸው።
"አልጋ እንዲጋሩ እያደረግን ነው፤ ቦታ የለንም። ገና ብዙ በሽተኞች ይመጣሉ። ሆስፒታሉ ከሚችለው በላይ ነው እየተሠራ ያለው። አንዳንድ ጊዜ ጥቂት አልጋዎችን ለ7 ሰዎች እንዲጋሩ ሁሉ እናደርጋለን" ይላሉ ዶ/ር ዲያና ካጂፔ።
ይህ ወረርሽኝ ደግሞ ነገሮችን አባብሷቸዋል። በቅርቡ ሰባት ሐኪሞችና ነርሶች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታሉ ለመዘጋት ተቃርቦ ነበር።
ዞሮ ዞሮ ፊሊፒንስ ልጆችን ወደ ምድር በስፋት እያመጣች ነው።
የቤተሰብ ምጣኔ አዋቂዎች እንደሚሉት የዚህ ልጆችን በላይ በላዩ የመውለድ ጣጣ ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድም ድህነትን የማውረስ ተግባር ነው።
እርግጥ ነው ፕሬዝዳንት ዶቴርቴ የቤተሰብ ምጣኔ አቀንቃኝ ናቸው። ነገር ግን አሁን በአደገኛ እጽና በጸረ ሙስና ዘመቻዎች ተጠምደዋል።

ፊሊፒንስ በደቡብ ምሥራቅ እሲያ አገሮች ሁሉ በወጣት ሴቶች እርግዝና መጠን የሚያህላት የለም።
አሁን ደግሞ የእንቅስቃሴ ገደቡ ቤት መዋልን በማስከተሉና የወሊድ መቆጣጠርያ ማግኘትን ከባድ በማድረጉ የፊሊፒንስ ወጣት ሴቶች የእርግዝና መጠን በ20 እጅ ተመንድጓል።
እስኪ በዛባላ ታሪክ እንደጀመርነው በእሷው ታሪክ እንጨርስ።
የ10 ልጆች እናት ዛባላ የምትኖረው በባሴኮ፣ ቶንዶ ውስጥ ነው። ባሴኮ፣ ቶንዶ በዓለም ላይ እጅግ ከተጨናነቁ ጭርንቁስ ሰፈሮች አንዱ ነው።
ዛባላ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በእርግዝና መከላከያ ዙሪያ ያለውን አቋም አሳምራ ታውቃለች።
"ገና የአንድ ወር እርጉዝ እንደነበርኩ ሳውቅ ባሌን ጽንሱን ማቋረጥ እንደምፈልግ ነገርኩት። ምክንያቱም ሕይወት ከብዶን ነበር። እሱ ግን ግዴለሽም እንወጣዋለን አለኝ። እኔም ሐጥያት ከምሠራ በቃ ይቅር ብዬ ጽንሱን ሳላቋርጥ ቀረሁ" ትላለች።
አሁን እሷና ባሏን ድህነት አለያይቷቸዋል።
ዛባላ እንባዎቿ ዱብ ዱብ እያሉ በሐዘንና በጭንቀት ስለ ነገ ታስባለች። የልጆቿ ነገር ያሳስባታል። ምን ላበላቸው ነው ግን እያለች ትቆዝማለች።
ይህን ታሪክ እየነገረችን በነበረበት ጊዜ ትንሽ ከሕዝብ ጭንቅንቅ ወጣ ባለ አካባቢ ድንገት ፖሊስ መጣ። ሰዎች መሸሽ ጀመሩ። ሁሉም እግሬ አውጪኝ…
ፖሊሶቹ አደገኛ እጽ ቸርቻሪዎችን እያደኑ ነበር። ዛባላ ስትናገር አሁን አደገኛ እጽ ከመሸጥ የተሻለ አማራጭ በአገሪቱ የለም።
አሁን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፊሊፒንስን ምጣኔ ሀብት አሽመድምዶታል።
አንዳንድ ጊዜ ግራ ሲገባኝ ለልጆቼ፣ "ለምን ለሆኑ ሀብታሞች አልሸጣችሁም። በጉደፈቻ ያሳድጓችኋል" እላቸዋለሁ።
"ከዚያ ግን በሐሳቡ እጸጸታለው። ነገም ሌላ ቀን ነው ብዬ ተስፋ ማድረግን እመርጣለሁ" ትላለች።
አሁን በፊሊፒንስ የዛባላ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች አሉ። ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ።
ዓለም ፊቷን ያዞረችባቸው። አደገኛ እጽ ለመቸርቸር የሚገደዱ። በችግር ምክንያት ልጃቸውን ለሀብታም 'በመሸጥ' የተሻለ ህይወት ይገጥማቸዋል ብለው የሚያስቡ ደጋግ እናቶች።
በዚህ ሁኔታ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጉድ አፈላ። ሌላ የወሊድ ወረርሽኝ አስከተለ።
ፊሊፒንስ እንዴት አድርጋ ነው የኮቪድ-19 እቀባ በፈጠረው ቤት የመዋል ግዴታ ውስጥ ሳይፈለጉ ወደ ምድር ያመጣቻቸውን ተጨማሪ 200 ሺህ ልጆቿን የምታሳድገው?
















