በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከ85 ወደ 59 ቀነሰ

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አርማ

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB

በኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ተብለው በቁጥር ከሚታወቁት 85 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 26ቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመሰረዛቸው ብዛታቸው ወደ 59 ቀነሰ።

በቦርድ መሰረዛቸው የተገለጸው በተለያዩ ጊዜያት ተመስርተው በብሔርና በአገር አቀፍ ፓርቲነት በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከሚገኙት ውስጥ በፓርቲነት ለመቀጠል የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ሳያሟሉ የቀሩት 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት ተመዝግበው ከነበሩት ከአንድ መቶ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የተወሰኑት በተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቅባቸውን ባለማሟላታቸው በመሰረዛቸው፤ በአሁኑ ወቅት በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡና በተለያዩ የምዝገባ ሂደት ላይ የሚገኙት 59 ፓርቲዎች ናቸው።

የምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በምዝገባው ማጣራት ሲደረግባቸው የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 85 የነበሩ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 26ቱ ተሰርዘዋል።

ከተሰረዙት መካከልም የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ይገኙባቸዋል።

ከተሰረዙት ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም የሚጠበቅባቸውን አሟልተው እንዲያቀርቡ የተወሰነ እና የማጣራት ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ ፓርቲዎች ያሉ ሲሆን የሚሰረዙት ቁጥር ሊጨምር ይችላል።

በዚህም መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም የሚጠበቅባቸውን አሟልተው እንዲያቀርቡ የተወሰነና የማጣራት ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ 12 ፓርቲዎች እንዳሉ የምርጫ ቦርድ መግለጫ አመልክቷል። ከእነዚህ ውስጥም የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት ( መኢአድ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ይገኙበታል።

በተጨማሪም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ነገር ግን የቴክኒክ መስፈርቶች ማሟላት ይቀራቸዋል ያላቸውን ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ ራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ፣ አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይን ጨምሮ ሰባት ፓርቲዎች መሆናቸውን ገልጿል።

ከዚህ በሻገር በምዝገባው ሂደት የሚጠበቅባቸውን በማሟላት የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ፓርቲዎች 40 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥም ገዢው ፓርቲ ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እና ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት (አረና) ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳለው በተሻሻለው አዋጅና ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸውን ግዴታዎች በሚደነግገው መመሪያ መሰረት የተመዘገቡና በሂደት ላይ ያሉ ፓርቲዎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን ሲያጣራ ቆይቷል።

በዚህም መሰረት ፓርቲዎቹ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ነገሮች በማጣራት ከ35 በመቶ በላይ የመስራች አባላት ፊርማ ትክክል የሆኑ ፓርቲዎችን ምዝገባ ያጸደቀ መሆኑን ቦርዱ አመልክቶ ከ35 በመቶ በታች የሆኑትን 26 ፓርቲዎችን እንዲሰረዙ ወስኗል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድጋሚ ለመመዝገብ የሚጠበቅባቸውን መመዘኛዎች አላሟሉም ያላቸውን 27 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ መሰረዙ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከወሰዷቸው የማሻሻያ እርምጃዎች መካከል የምርጫ ቦርድ በገለልተኝነት እንዲመራ ማድረግ አንዱ መሆኑ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ቦርዱ እንደ አዲስ ተዋቅሮ የሕግ ማሻሻያዎች ከተደረጉ በኋላ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ተመስርተው በአገሪቱ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ ሕግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ በማድረግ በድጋሚ እንዲመዘገቡ ሲደረግ ቆይቷል።

እስካለፈው ዓመት ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚታወቁ ከ106 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን በድጋሚ ምዝገባ በማድረግ አውቅናቸውን እንዲያድሱ ባለፈው ዓመት ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር።

በዚህም መሠረት ቦርዱ ባደረገው ማጣራት የሚጠበቅባቸውን ሳያሟሉ የቀሩ 53 አገራዊና የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሰረዙ መወሰኑን ባለፈው ዓመት ግንቦት 07/2012 ዓ.ም እና በዚህ ዓመት ታኅሳስ 13/2013 ዓ.ም ወስኗል።