ምርጫ 2013፡ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ይጠበቃሉ ተባለ

ምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ
የምስሉ መግለጫ, ምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀ።

ቦርዱ ይህን ያለው ዛሬ 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫን አስመልክቶ እያደረጋቸው ያሉ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ሥራን ባስታወቀበት ወቅት ነው።

ቦርዱ እድሜያቸው ለመምረጥ ደርሶ በምርጫው ይሳተፋሉ ያላቸው ዜጎች ከአገሪቱ ሕብ ቁጥር ወደ ግማሽ የሚተጉ ሲሆኑ፤ በመላው አገሪቱ በምርጫው ድምጽ የሚሰጡባቸው 50 ሺህ 900 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩም አስታውቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር የቤት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቀረበለትን በአገሪቱ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግምገማና ምክረ ሐሳብ ተመልክቶ ከባለፈው ዓመት የተሸጋገረውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት ከድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ 152 ሺህ 700 ሰዎችን እንዲሁም ለድምጽ መስጫ ቀን 254 ሺህ 500 ምርጫ አስፈጻሚዎችን እንደሚያሰማራም አስታውቋል።

በዚህ ዓመት ሊካሄድ እንደሚችል ለተጠቆመው አገራዊ ምርጫ በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመራጮች መዝገቦች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል አስታውቋል።

የምርጫውን ተአማኒነት ለማረጋገጥም መራጮችም የሚወስዱት ለማባዛት እና አስመስሎ ለማተም የማይቻል የደኅንነት መጠበቂያ ያለው የመራጮች መታወቂያ ካርድ መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

ቦርዱ እንደ ድምጽ መስጫ ሳጥኖች፣ የሚስጥር ድምጽ መስጫ መከለያዎች፣ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች የያዙ ቦርሳዎች፣ የጠረጴዛ ባትሪ የመሳሰሉ ለምርጫ ቀን የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

አገራዊ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ የሚያመለክተው የጊዜ ሰሌዳ ያልወጣ ቢሆንም፤ ቦርዱ ከወዲሁ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ መርጫ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት እንዲተላለፍ መወሰኑ ይታወሳል።