ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ተያዙ

ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊ እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊ እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

ቀደም ብሎ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ረዳት በኮሮናቫይረሱ መያዟን ተከትሎ እርሳቸው እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገው ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አሳውቀው ነበር።

ለሁለተኛ ዙር የምርጫ ዘመን ፉክክር እተዘጋጁ ያሉት የ74ቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ በሆነው የዕድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ፤ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከታወቀ በኋላ "በጋራ እናልፈዋለን" ሲሉ ትዊተር ላይ አስፍረዋል።

የምርመራውን ውጤቱን ተከትሎ እርሳቸው እና ባለቤታቸው በኮቪድ-19 መያዛቸውን ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል።

በኮሮናቫይስ መያዟ የተነገረው የትራምፕ የቅርብ ረዳት የ31 ዓመቷ ሆፕ ሂክስ ናት።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ "እኔ እና ቀዳማዊት እመቤት በቫይረሱ ተይዘናል። እራሳችንን ለይቶ የማቆየት እና ወደማገገም ሂደት በፍጥነት እናመራለን" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ የምርጫ ክርክር ለማድረግ ወደ ኦሃዮ ባቀኑበት ወቅት ሆፕ ሂክስ አብራቸው በኤር ፎርስ ዋን የፕሬዝዳንቱ አውሮፕላን ተጉዛለች።

ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ማሪን ዋን በተሰኘው የፕሬዝደንቱ ሄሊኮፕተር ውስጥ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በቅርበት ሆና መጓዟ ተገልጿል።

የትራምፕ ሐኪም ሾን ኮንሌይ ባወጡት መግለጫ፤ ፕሬዝዳንቱም ሆኑ ቀዳማዊቷ ዕመቤት በአሁኑ ጊዜ "ሁለቱም ለማገገም ዋይት ሐውስ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያቸው የህክምና ክትትል እተደረገላቸው ለመቆት አቅደዋል" ሲሉ አመልክተዋል።

"ፕሬዝዳንቱ ከበሽታው ለማገገም የሚያስፈልገውን እያደረጉ የሚተበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚቀጥሉ ላረጋግጥላቸሁ እወዳለሁ" ያሉት ሐኪሙ በቀጣይ የትራምፕን ጤና በተመለከተ የሚኖሩ ለውጦችን በሂደት እንደሚያሳውቁም ገልጸዋል።

የትራምፕ በቫይረሱ መያዝ ሁለተኛውን ፕሬዝደንታዊ ክርክር እንዴት ሊያውክ እንደሚችል ግልጽ አይደለም። ሁለተኛው የፊት ለፊት ክርክር በፍሎሪዳ ማያሚ ውስጥ ጥቅምት 15 ለማካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።

ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ "ሆፕ ሁልጊዜም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ታደርግ ነበር። ውጤቷ ግን ፖዘቲቭ ሆኗል” ብለዋል። በሽታው ከ7.2 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያንን ያጠቃ ሲሆን ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች ሞት ደግሞ ምክንያት ሆኗል።

ሆፕ ሂክስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሆፕ ሂክስ

ዋይት ሐሃውስ ለሁሉም የፕሬዝደንቱ አማካሪዎች እና ከፕሬዝደንቱ ጋር በየዕለቱ ለሚገናኙ ሰዎች በሙሉ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ብዙ ጊዜ የአፍ እና አፍንጫ ጭምብል ማድረግን የሚያጣጥሉት ፕሬዝደንት ትራምፕ ከአማካሪዎቻቸው ጋር ሲገናኙ ርቀታቸውን ሲጠብቁ አይታዩም።

ብሉምበርግ እንደዘገበው ከሆነ በኮቪድ-19 መያዟ የተረጋገጠው የትራምፕ አማካሪ የበሽታውን ምልክት አሳይታለች።

ግንቦት ወር ላይ የምክትል ፕሬዝደንቱ አማካሪ ኬቲ ሚለር በቫይረሱ ተይዘው ማገገማቸው ይታወሳል።

ሆፕ ሂክስ የትራምፕን ቡድን የተቀላቀለችው እአአ 2014 ላይ ነበር። በወቅቱ የፖለቲካ ልምድ ያልነበራት ሆፕ ከአንድ ዓመት በኋላ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አካል እንድትሆን ተደርጓል።

ትራምፕ "ሆፕስተር" እያሉ የሚጠሯት ሆፕ ሂክስ ትራምፕ ከሚያምኗቸው አማካሪዎች መካከል አንዷ ስትሆን፤ የፕሬዝደንቱን አመለካከት ማስቀየር ከሚችሉ ጥቂት አማካሪዎች መካከል ሆፕ አንዷ ነች ይባላል።