ዶናልድ ትራምፕ የዋጡት መድኃኒት ኮሮናን "አይፈውስም" ተባለ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ትራምፕ ሲዘምሩለት የነበረው "የኮሮና መድኃኒት" አይረባም ተባለ

ለወባ እጅግ ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ የሚነገርለት ሀይድሮክሲክሎሮኪን ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝት ተከትሎ ዝነኛ ለመሆን የተገደደ መድኃኒት ነው ማለት ይቻላል፡፡

መድኃኒቱ ዝናው ከፍ እያለ በመምጣቱ ትልቋ የመድኃኒቱ አምራች ሕንድ ይህን መድኃኒት ወደ ውጭ መላክን በአዋጅ እስከማስከልከል ደርሳ ነበር፡፡

ሀይድሮክሲክሎሮኪን በተለይም ዶናልድ ትራምፕ "ተአምራዊ ፈውስ ይሰጣል" ብለው በሚያስገርም እርግጠኛነት ሲያሞካሹት የነበረ መድኃኒት ነው፡፡

"እኔን ስሙኝ፤ ሀይድሮክሲክሎሮኪን ፈውስ ነው፤ የኮሮና ጸር ነው፤ ይህን መድኃኒት በመውሰድ ምን ትጎዳላችሁ? ሲሉ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር በተደጋጋሚ ዘምረውለታል ዶናልድ ትራምፕ፤ ለዚህ መድኃኒት፡፡

በመጨረሻ ግን ይህ የርሳቸው እርግጠኝነት በሳይንቲስቶች ሊደገፍ አልቻለም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ሀይድሮክሲክሎሮኪውን ሞት ያፋጥናል የሚሉ ጥናቶች መውጣት ጀምረው ነበር፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም መድኃኒቱ ለኮሮና ፈዋሽነቱ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ፍሬ አልባ እንደሆኑ ገልጾ ነበር፣ ከዚህ ቀደም፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ግን እጅ አልሰጡም፡፡ ከሳይንቲስቶችም፣ ከመድኃኒት ቀማሚዎችም፣ ከመድኃኒት አስተዳደርም ሆነ ከዓለም ጤና ድርጅት በተቃራኒው ቆመው ለዚህ መድኃኒት ፈዋሽነት ሽንጣቸውን ገትረው እየተከራከሩ ነው፡፡

በመድኃኒት ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት አስተተዳደር ትናንት ሰኞ ይህ የወባ መድኃኒት ሕመማቸው ለጸናባቸው እንኳ ቢሆን ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች እንዳይሰጥ አዟል፡፡

የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር እንደሚለው በቅርብ በተደረጉ የክሊኒካል ሙከራዎች የመድኃኒቱን ፈዋሽነት የሚያሳይ ምንም ነገር አልተገኘም፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ግን እኔን ስሙኝ መድኃኒቱ አንደኛ ነው እያሉ ነው፡፡

ሀይድሮክሲክሎሮኪን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ይህ መድኃኒት እጅግ ለከፋባቸው የኮሮና በሽተኞች ቢሰጥ ችግር የለውም ብሎ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

ነገር ግን ሰኞ ለት ባወጣው ውሳኔ ሀይድሮክሲክሎሮኪውን ለኮሮናቫይረስ የሚረባ መድኃኒት እንዳልሆነና የጎንዮሽ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በሙከራዎች ተደርሶበታል ብሏል፡፡

ይህ ውሳኔ ያበሳጫቸው ዶናልድ ትራምፕ መድኃኒቱን እኔ ራሴ ወስጄዋለሁ፤ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት አላመጣብኝም ብለዋል፡፡

"ወሰድኩት በጣም ጥሩ ስሜት ነው የሰጠኝ፤ ምንም ቅር ያለኝ ነገር የለም፤ ለሁለት ሳምንታት ነው የወሰድኩት፤ ይኸው እንደምታዩት ደህና ነኝ" ብለዋል ለጋዜጠኞች፡፡

የ74 ዓመቱ አወዛጋቢ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ብዙ ወዳጆቼ ወስደውት ከኮሮና ቫይረስ መፈወሳቸውን ነግረውኛል፤ ይህ መድኃኒት ሕይወታቸውን ታድጎታል" ብለዋል፡፡

በርካታ ጋዜጠኞች ግን ዶናልድ ትራምፕ ይህን መድኃኒት ውጬዋለሁ ማለታቸውን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት፡፡