የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ወደ ምዕራብ ኦሮሚያም ይሄዳሉ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የሐይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መስተዳደር መካከል ያለውን አለመግባባት በሽምግልና መፍትሔ እንዲያገኝ ለማገዝ ዛሬ ወደ መቀለ እንደሚሄዱ ተነግሯል።
የሽምግልና ቡድኑ ከመቀለ ጉዞው ባሻገር ለረጅም ጊዜ ግጭቶችና የሰላም መደፍረስ እንዳጋጠመው ወደሚነገርልት የምዕራብ ኦሮሚያ እካባቢዎች በመንቀሳቀስ ሰላም እንዲወርድ እንደሚጥር የቡድኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለቢቢሲ ጨምረው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ከጊዜ እየተካረረ በመሄድ ከኢህአዴግ መክሰም በኋላ የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ይሰማል።
ይህ አለመግባባት ያሳሰባቸው የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ ወደ ትግራይ ዛሬ ማክሰኞ እንደሚያቀኑ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መስኡድ አደም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የሽምግልና ቡድኑ ወደ መቀለ የሚሄድበት ዋና ዓላማ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው አለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መሄዱ እና ችግሩ እንዲፈታ ደግሞ መቀራረብና መነጋገር አስስፈካጊ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
አቶ መስኡድ እንዳሉት የሽምግልና ቡድኑ በሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ አመለካከት የሚያነሳው ነገር እንደሌለ ጠቅሰው፤ መግባባትን በመፍጠር አገራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እንደሚጥሩ አመልክተዋል።
"እንደ ሐይማኖት አባትም እንደ አገር ሽማግሌም በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋገሩ እንላለን። ከዚያም በሚያደረጉ ውይይቶች ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ መፍትሄዎች ይመጣሉ ብለን እናስባለን" ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ሽምግልና ቡድኑ እምነት ለሚታየው አለመግባባት ዋነኛው ችግር ያጋጠሙ ቅራኔዎችን ተቀራርቦ መነጋገር አለመቻል ነው።
ስለዚህም እነዚህ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ይህንን ሚና በመውሰድ ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ እንዲነጋገሩና ለገጠማቸው ችግር በእራሳቸው መንገድ መፍትሔ እንዲኣገኙ መርዳት የቡድኑ ቀዳሚ ሐሳብ ነው ተብሏል።
"የመጀመሪያውን እርምጃ በመውሰድ አገራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ። እናቀራርባቸው፤ እነሱ ይነጋገሩ" የሚል መነሻ በሽማግሌዎቹ መኖሩ ተገልጿል።
አቶ መስኡድ እንዳሉት ይህንን የሽምግልን ለማከናወን ተነሳሽነቱ ከማንም ግፊት የመጣ እንዳልሆነ ጠቅሰው ይህ ተግባር "እንደ ሐይማኖት መሪም ሐይማኖታዊ ግዴታ ነው። የተጣሉን ማስታረቅ ሰዎችን ማቀራረብ ሐይማኖታዊ የተቀደሰ ምግባር ነው። እንደ አገር ሽማግሌም ትልቅ የሞራል ግዴታም ጭምር ነው" ሲሉ በእራስ ተነሳሽነት የተጀመረ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል።
የሽምግልና ቡድኑ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት መፍትሔ እንዲያገኝ "እንደ አማኝ ፈጣሪ ያግዘናል ብለን ነው የምናስበው። ሐይማኖት መሪዎች በፀሎት ያግዛሉ፣ የአገር ሽማግሌዎች ያነጋግራሉ፣ ያደራድራሉ፥ ያቀራርባሉ" በማለት ጥረታቸው በስኬት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋ አመልክተዋል።
የሽምግልና ቡድኑ በሁለቱ ወጎች መካከል ያለው ትልቁ ችግር ያለመነጋገር ነው ብሎ እንደሚያምንና ለዚህ ደግሞ ቁልፉ መነጋገር በመሆኑ በመነጋገር መፍትሔ ይገኛል ብሎ እንደሚያምን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ላለመግባባትም እኮ መግባባት ያስፈልጋል። በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ አንግባባም፤ በዚህ በዚህ ጉዳይ ተግባብተን አብረን እንቀጥላለን ማለትም አንድ ነገር ነው። ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ካደረግን ከዚያ በኋላ ችግሮቻቸውን በመነጋገር፣ በውይይት ይፈታሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።"
የሽምግልና ቡድኑ የዛሬ ወደ ትግራይ የሚደረገው ጉዞ የመጀመሪያው እንደሆነና በዚህ ጉዞ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር የተናገሩት አቶ መስኡድ ሌሎች መቀራረብና መግባባት ይኖርባቸዋል በሚባሉ ወገኖች መካከል ተመሳሳይ ሥራዎች እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በዚህም "ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ወደ አማራም፣ ወደ ሶማሌም፣ ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎችም በመሄድ በአጠቃላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል። የዛሬው የመቀሌ ጉዞ የእዚያ ጥረት ማስጀመሪያ ነው የሚሆነው" ብለዋል።
በአገሪቱ የለውጥ እርምጃዎች መወሰድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ህወሓት በአንድ ግንባር ስር ለ25 ዓመታት በአንድ ላይ ሲሰሩ ከነበሩት ድርጅቶች ጋር የነበረው ትስስር ላልቶ ቅራኔ በአደባባይ ሲነገሩ ቆይተዋል።
በተለይም የአራት ክልላዊ ፓርቲዎች ጥምረት የነበረው ኢህአዴግ ከስሞ በብልጽንና ፓርቲ ሲተካና ህወሓት እራሱን ሲያገል ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተካረው አሁን ካለበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይታወሳል።
















