ምዕራብ ኦሮሚያ፡ "መንግሥት ጠንከርና መረር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል" ጄነራል ብርሃኑ ጁላ

የፎቶው ባለመብት, OBN
በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ መንግሥት የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ የጸጥታ ኃይል ወደ ስፍራው ማሰማራቱን መግለፁ ይታወሳል።
መንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል ወደ ስፍራው ያሰማራሁት ታጥቆ የሚንቀሳቀሱና የአካባቢው ነዋሪ ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ነው ቢልም፤ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በንጹሃን ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ላይ እጁ አለበት ሲሉ ይኮንናሉ።
ቢቢሲ በዚህ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከምክትል ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ጋር ቆይታ አድርጓል።
"እኔ የምመራው ወታደር ሕዝብ አይነካም"
የአገር መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፤ አካባቢውም ያለ ስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ሥር ይገኛል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ከተሰማራ በኋላ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው መባሉን ምክትል ኢታማዦር ሹሙ አጥብቀው ይቃወማሉ።
"ይህ ስህተት ነው" የሚሉት ምክትል ኢታማዦር ሹሙ፤ በአካባቢው ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኃይል ሁለት ዓመት እንዳስቆጠረ አስታውሰው፤ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እርምጃ ለመውሰድ ሠራዊት ወደ ሥፍራው ማዝመቱን ተናግረዋል።
"የሠራዊት ሥራ ሕዝብን ከሽፍታ መለየት ነው። ለሕዝብ ከለላ መስጠት፣ ሽፍቶች ላይ ደግሞ እርምጃ መውሰድ ነው። በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚባለው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ምን እንደሚባል እናውቃለን። የመከላከያ ሠራዊት አባላት 'ፕሮፌሽናል' ናቸው። ሕዝብን ከሽፍታ ይለያሉ። . . . የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝብ ላይ ጉዳት አያደርስም። ሕዝቡም 'ሽፍታን አስወግዱልን' ነው እያለ ያለው እንጂ መከላከያ ይህን ጉዳት አደረሰብኝ አይደለም ያለው።" ይላሉ።
ምክትል ኢታማዦር ሹሙ መከላከያ ሠራዊት በሕዝብ ላይ ገዳት አደረሰ እየተባለ ያለው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሆኑን ተናግረው፤ ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት መጠየቅ ያለበት የአካባቢው ሕዝብ ነው ባይ ናቸው። "እናንት ራሳችሁ ስትጠይቁ ስለሚያስፈሯሯቸው በሚስጥር ጠይቋቸው ከዛ እውነቱን ትረዳላችሁ"
"እኔ ያደራጀሁት እና እኔ የምመራው ወታደር ሕዝብ አይነካም። የመንግሥት ወታደር ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሶ ከሆነ ግን መንግሥት ይጠየቃል። እኔም በግሌ ሕዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ እክሳለሁ።"
"የተለየ ኦፕሬሽን"
የአገር መከላከያ ምክትል ኢታማዦር ሹሙ እንደሚሉት ከሆነ፤ ጦሩ በአሁኑ ወቅት "የተለየ" ነው ያለውን ኦፕሬሽን በምዕራብ ኦሮሚያ እያካሄደ ይገኛል።
"ከዚህ ቀደም ወደ ሰላም እንዲመጡ ይለመኑ ሁሉ ነበር። ልመናው ሲበዛባቸው ይልቁን መጠናከር ጀመሩ፤ ሕዝቡ ላይ የሚደርሰው በደል ተጠናክሮ ቀጠለ። ሕዝብ ያስፈራራሉ፣ ሕዝብ ይዘርፋሉ፣ ያስቃያሉ፣ አፍነው 70 እና 60 ኪሎ ሜትር ይዘው ሄደው ለሁለት ሳምንት ደብድበው ይለቃሉ። በዚህ መሰል ዘግናኛ ተግባር የሚታወቀው አል-ሸባብ ነበር። አል ሸባብ ራሱ አሁን እንዲህ አይነት ተግባር አይፈጽምም" በማለት መንግሥት "ጠንከር እና መረር" ያለ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ያስረዳሉ።
"ይህ ቡድን ሊድን የማይችል፤ አዕምሮው የተበላሸ መሆኑ በመንግሥት ታምኖበታል። የደፈጣ ተዋጊ ስነ-ምግባር እንኳ የሌላቸው ናቸው እኮ" በማለት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የሚዋግዋቸውን ኃይሎች ባህሪ ይገልጻሉ።
"መሮ አንድም ቀን መሳሪያ ሳይቱኩስ . . . ታዳጊዎችን እያስጨረሰ ነው"
ምዕራብ ኦሮሚያ በኮማንድ ፖስት ሥር መተዳደር ከጀመረ ወዲህ በርካቶች ሰዎች በተዳጋጋሚ ለእስር እየታደረግን ነው እያሉ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማል። ምክትል ኢታማዦሩ ግን ይህ ፍጹም ስህተት ነው ይላሉ።
"ይህ ሐሰት ነው። የስነ-ልቦና ጦርነት የሚባል ነገር አለ። አንድ ወታደር ሳይገድሉ 80 ወታደር ገደልን 100 ማረክን ይላሉ፣ መልሰው ደግሞ እንዲህ በሚባል ቀበሌ ውስጥ መከላከያ ገብቶ ሰው ገደለ ብለው ሐሰት ይነዛሉ። ገንዘብ እያወጡ የሚልኩላቸውን ደጋፊዎቻቸውን ለማስደሰት በማሰብ ያላገኙትን ድል አገኘን እያሉ ያወራሉ። እውነቱ ግን አንድም ቀን ከእኛ ጋር ፊት ለፊት ተዋግተው አያውቁም። ሁሌም ሲሸሹ ነው የሚመቱት። እየሸሹ ነው የሚያዙት። ከእኛ ጋር ፊት ለፊት እንኳ ተገናኘቶ የመዋጋት አቅም የላቸውም። ስለዚህ በእነሱ በኩል የሚመጣው ሁሉ እውነት ብሎ መቀበል ስህተት ነው" ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በትግል ስሙ 'መሮ' ተብሎ በሚታወቀው ኩምሳ ድሪባ ከሚመራው ኃይል ውጪ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ሌላ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለመኖሩን የሚናገሩት ምክትል ኢታማዦር ሹሙ፤ መሮ የሚመራው ኃይልም ቢሆን መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ የታጣቂዎቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ይላሉ።
"ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄዷል። ባለፉት ሶስት ሳምንታት ሰላም ሆኗል። ለምለም በረሃ በሚባለው ቦታ እንጂ ሌላው አካባቢ ሠላም ነው። ሁሉም አካባቢ እሰኪጸዳ የሰላም ማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ ይካሄዳል። አሁን የቀሩት ስፖንሰር ያላቸው ህይወታቸውን በዚህ መልክ ለመምራት የፈለጉት ዋነኛዎቹ ብቻ ናቸው። እነሱም ተደብቀው ነው የሚገኙት። መሮ ራሱ ተደብቆ ነው የሚገኘው። ሠራዊት እሱ ያለበት ቦታ መድረሱን ሲሰማ ቦታ ይቀይራል። እሱ አንድም ቀን መሳሪያ ሳይተኩስ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ፤ ታዳጊዎችን ከቀያቸው ሰብስቦ እያስጨረሳቸው ነው" ይላሉ።
"ስልክ ማቋረጡ ኦፕሬሽኑን ስኬታማ አድርጎታል"
በምዕራብ ኦሮሚያ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
ምክትል ኢታማዦር ሹሙ የስልክ አገልግሎት የተቋረጠው በአካባቢው የአገር መከላከያ ሠራዊት እየወሰደው ካለው ኦፕሬሽን ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የስልክ አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ በአካባቢው በታጣቂዎቹ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ስኬታማ ማድረጉን ተናግረዋል።
የስልክ አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ "በጣም ነው የጠቀመን" የሚሉት ጀነራል ብርሃኑ፤ "እኚህ ሰዎች እኮ የመገናኛ ሬዲዮ እንኳን የላቸውም፤ ሞባይል ስልክ በመጠቀም ነው የመንግሥትን እንቅስቃሴ ለሁለት ዓመት ሲያከሽፉ የቆዩት" ብለዋል።
ደቡብ ኦሮሚያ
ከምዕራብ ኦሮሚያ በተጨማሪ በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል እንዳለ ይታመናል።
ጄነራል ብርሃኑ እንደሚሉት በቅርቡ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በአካባቢ የነበሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
"በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ህዝቡን እያስገደዱ ቡና እያስመጡ ወደ ኬንያ አሻግረው ይሸጡ ነበር። ሕዝብ ሲንገላታ ቆይቷል። ይህ የሆነው ደግሞ መንግሥት ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት የኃይል እርምጃ ሳይወስድ በመቅረቱ ነበር። ኦፕሬሽን ካካሄድን በኋላ ሁለቱም ጉጂዎች ነጻ ወጥተዋል። አሁን መደበቂያ ሲያጡ ወደ ሶሎሎ [ኬንያ እና ኢትዮጵያ ድንበር አዋሳኝ] ሸሽተዋል።" በማለት እያካሄዱት የሚገኘው ወታደራዊ እርምጃ ውጤት ማምጣቱን ይናገራሉ።















