በምዕራብ ኦሮሚያ ባለፉት 12 ወራት ቢያንስ 8 የአካባቢው ባለስልጣናት ተገድለዋል

ባለፈው አንድ ዓመት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች ውስጥ በመንግሥት እና በተቋማት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እየተጠናከሩ መጥተዋል።
የመንግሥት ኃላፊዎች የጥቃቱ ዋነኛ ዒላማ ይደረጉ እንጂ፤ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች፣ ሰላማዊ ሰዎችና የውጪ አገራት ዜጎች ጭምር የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
የክልሉም ሆነ የየአካባቢዎቹ የመንግሥት ባለስልጣናት ለግድያዎቹ ተጠያቂ የሚያደርጉት "ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ኃይሎችን" ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ከኦነግ ተነጥሎ የወጣውን 'ኦነግ ሸኔ' የተባለውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
በምዕራብ ኦሮሚያ ከኅዳር 2011 እስከ ኅዳር 2012 ባሉት 12 ወራት ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጥቃቶቹ ሰለባ የሆኑትን ሰላማዊ ሰዎችን ሳይጨምር በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው በታጣቂዎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ10 በላይ እንደሚሆን የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ኅዳር 2012 ዓ.ም
ባለንበት ዓመት በዚህ የኅዳር ወር ብቻ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 5 የመንግሥት ባለስልጣናት ተገድለዋል።
ከእነዚህም መካከል በምዕራብ ኦሮሚያ የጀልዱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ረጋኔ ከበበ እና የጎጆ ከተማ የፖለቲካ ዘረፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገረመው በተመሳሰይ ቀን ተገድለዋል።
ሁለቱ የአካባቢው ባለስልጣናት በጎጆ ከተማ ማክሰኞ ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ላይ ነበር በጥይት ተመትተው የተገደሉት።
የሁለቱን ባለስልጣናት መገደል ለቢቢሲ ያረጋገጡት የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ ሲሆኑ፤ የመንግሥት ኃላፊዎቹ የተገደሉት "ባልታወቁ ታጣቂዎች" ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ሳምንት አንድ የምዕራብ ሸዋ ዞን ባለስልጣን በጥይት ሲገደሉ፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያም ማንነታቸው በውል ያልተገለፀ ታጣቂዎች ደግሞ የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ጫላ ደጋጋ መግደላቸውም ተነግሯል።
ቀደም ብሎ ረቡዕ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጠዋት ላይ የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር የመንገዶች ባለስልጣን ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ቶላ ገዳ ለሥራ ወደ ምዕራብ ወለጋ ቄለም ወለጋ ዞን እየተጓዙ ሳሉ ላሎ አሳቢ ተብሎ በሚታወቀው ወረዳ ውስጥ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ኡመታ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ጥቅምት 2012 ዓ.ም
ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ዕሁድ አመሻሽ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ዞን ኃላፊ የነበሩት አቶ ገመቺስ ታደሰ በታጠቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።
የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳምጠው አቶ ገመቺስ ቢያንስ በአራት ጥይት መመታታቸውን እና አንድ ጊዜ በስለት መወጋታቸውን ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
ግለሰቡ ቀደም ሲልም ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ዛቻ ይሰነዘርባቸው እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን በወቅቱ ፖሊስ በአቶ ገመቺስ ግድያ ተጠርጣሪ እንዳልያዘ የነቀምቴ ፖሊስን በመጥቀስ ዘግበን ነበር።
መስከረም 2012 ዓ.ም
የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አበበ ተካልኝ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የተገደሉት መስከረም 7 ቀን 2012 ነበር።
አቶ አበበ በታጣቂዎች መገደላቸውን የጉሊሶ ወረዳ የአስተዳደር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ሊካሳ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። "ደጃፋቸው ላይ በሁለት ጥይት ግንባራቸውን ተመትተው ነው የተገደሉት" ሲሉ የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ከንቲባውን ቤታቸው በር ላይ ከገደሉ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ዘልቀው በመግባት "ለስብሰባ የተዘጋጀ ጽሑፍ እና የአካባቢውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝርን የያዘ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ይዘው ሄዱ'' ሲሉ አቶ ተስፋ ጨምረው ተናግረዋል።
ከንቲባውን ገድለው ላፕቶፕ ዘርፈው ሄዱ የተባሉት ታጣቂዎች በቁጥር ወደ ስድስት እንደሚጠጉ የሟች የቤተሰብ አባላት ለመንግሥት የጸጥታ አካል መናገራቸውም ተገልጿል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ በሚገኝ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ላይ ቦምብ ተወርውሮ አንድ ሰው የተገደለው እና በርካቶች የቆሰሉት መስከረም 2012 ነበር።
የመንዲ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለሙ ጉዲና ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተወረወረው ቦምብ የአንድ ሰው ህይወት ከመቅጠፉም በላይ በርካቶችን አቁስሏል።
ሰኔ 2011 ዓ.ም
ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ሌላኛው የታጣቂዎች ኢላማ የነበሩት ባለስልጣን ደግሞ የደምቢዶሎ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ገመቹ ነበሩ። ከንቲባው በጥቃቱ በጥይት ተመትተው ቆስለው በህይወት ተርፈዋል።
ከንቲባው አቶ ታደለ በጥይት ተመትተው የቆሰሉት ከቢሯቸው ወጥተው መኪናቸው ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ነበር። "ከንቲባው ከሥራ በሚወጡበት ሰዓት ነበር በር ላይ ጥቃቱን ያደረሱባቸው" ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣን ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከንቲባውን በሁለት ጥይት እንደመቷቸውና አንደኛው ጥይት እጃቸውን ሌላኛው ደግሞ በጎን በኩል ኩላሊታቸው አካባቢ እንደመታቸውም ለማወቅ ተችሏል።
ታኅሳስ 2011 ዓ.ም
ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ መነ ቤኛ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ላይ በጥይት ተመተው የተገደሉት ታኅሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር።
የዞኑ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተረፈ፤ ሁለቱ የፌደራል ፖሊስ አባላት የፊንጫአ ኃይል ማመንጫ እና ጌዶ ከተማ ላይ የሚገኝ የኃይል ማከማቻ ጣቢያዎችን የሚጠብቁ የጸጥታ ኃይል አባላት ነበሩ ብለዋል።
''መኪና ላይ ሆነው ወደ ፊንጫአ እየተጓዙ ሳሉ ባልታወቁ ታጣቂዎች ተኩስ ተከፈተባቸው'' በማለት አቶ ደሳለኝ የነበረውን ሁኔታ ተናግረው ነበር።
መጋቢት 2011 ዓ.ም
የውጪ አገር ዜጎችን ጭምር ዒላማ ያደረገው እና ለአምስት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት የተሰነዘረው ሌላኛው ጥቃት መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር የተፈጸመው።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ ሁምነ ዋቀዮ በተባለ ቀበሌ ሦስት ኢትዮጵያዊያን፣ አንድ ጃፓናዊ እና አንድ የህንድ ዜግነት ያላቸው ሰንራይዝ ለሚባል የማዕድን አውጪ ተቋም ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው በጥቃቱ የተገደሉት።
ክስተቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሰዎቹ የተገደሉት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ነው ብሎ ነበር።
ከተገደሉት ሰዎች አራቱ ወንዶች ሲሆኑ አንንደኛዋ የውጪ ዜጋ ሴት ናት።
እነዚህ የጥቃቱ ሰለባዎች ከማዕድን ኩባንያው ጋር ይሰሩ የነበሩ ሲሆን አቶ አለማየሁ በቀለ የተባሉት ግለሰብ የኩባንያው ባለቤት እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።
አቶ አለማየሁ ይህንን የማዕድን ማውጣት ሥራ ለመጀመር ሦስት ዓመታትን የፈጀ ጥናት ማከናወናቸውንና የምርት ሥራውን ለመጀመር በተቃረበበት ወቅት ከአራት ባልደረቦቻቸው ጋር በታጣቂዎቹ መገደላቸውን የቅርብ ጓደኛው በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ተጠያቂ ያልተገኘላቸው ጥቃቶች
በምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በተለይ የመንግሥት ባለስልጣናትንና የጸጥታ አካላትን ኢላማ በመድረግ ሲፈጸም የቆየው የታጣቂዎች ጥቃትን በተመለከተ ከግምት ባለፈ ተጠያቂ የሆነ አካል አልተገኘም።
በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂዎች በተፈጸሙት በእነዚህ ጥቃቶች በመንግሥት ሥራ ላይ ከተሰማሩት ሰዎች በተጨማሪ ሰላማዊ ነዋሪዎችም ሰለባ ሆነዋል።
እስካሁን በተለይ የመንግሥት ኃላፊዎችንና የጸጥታ አካላትን ኢላማ አድርገው የተፈጸሙት የታጣቂዎች ጥቃቶች ምክንያቱ ምን እንደሆነና ለድርጊቱም ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።
ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት የጸጥታና ከተለያዩ የመንግሥት አካላትን ያካተተ የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ይታወሳል።














