ከትናንት በስቲያ ሁለት የምዕራብ ሸዋ ባለስልጣናት በጥይት ተትመተው ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, የምዕራብ ሸዋ ኮሚኒኬሽን
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የጀልዱ ወረዳ አመራር የሆኑ ሁለት የአካባቢው ባለስልጣናት ከትናንት በስቲያ ማንነታቸው አልታወቀም በተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸው ተነገረ።
የጀልዱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ረጋኔ ከበበ እና የጎጆ ከተማ የፖለቲካ ዘረፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገረመው በጎጆ ከተማ ማክሰኞ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ በጥይት ተመትተው መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ይህን መሰል በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ባለፈው ሳምንት እንኳ አንድ የምዕራብ ሸዋ ዞን ባለስልጣን በተመሳሳይ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያም ማንነታቸው በውል ያልተገለጹ ታጣቂዎች የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ የነበሩትን ኮማንደር ጫላ ደጋጋን መግደላቸው ተነግሯል።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ግድያዎች በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ ቆይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከመንግሥት ባለስልጣናቱ ባሻገር ሰላማዊ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎችና የውጪ ዜጎችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ማንነታቸው በውል ባልተገለጹ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በክልሉ በሚገኙ ባለስልጣናት ላይ ኢላማ እያደረገ የመጣውን ይህን ግድያ ለማስቆም በቅርቡ የተቋቋመው እና 'ጋዲሳ ሆገንሰ ኦሮሞ' የሚሰኘው አካል ከመንግሥት ጋር በመሆን መፍትሄ እያፈላለገ እንደሆነ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ፓርቲዎች ስብስብ መድረክ የሆነው 'ጋዲሳ ሆግንሰ ኦሮሞ' የኦሮሞ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ፓርቲዎች አብረው ለመስረት ከስምምነት ደርሰው ከሁለት ወራት በፊት ያቋቋሙት አካል ነው።
በ'ጋዲስ ሆግንሰ ኦሮሞ' ምስረታ ላይ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዳውድ ኢብሳ፣ መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ እና በቀለ ገርባ ፓርቲዎቻቸውን ወክለው ፊርማቸውን ካኖሩ አመራሮች መካከል ይገኙበታል።
አቶ ዴሬሳ "ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ አካላት ትግላቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን ነው የመንግሥት ፍላጎት" ይላሉ። አክለውም "አለመረዳዳት ነው እንጂ ኦሮሞ ኦሮሞን ገድሎ የሚገኝ ጥቅም የለም፤ ኪሳራ ነው ማለት ነው" ብለዋል አቶ ዴሬሳ።
በተለይ በምዕራባዊ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ላጋጠመው ባለስልጣናትን ኢላማ ላደረገው ግድያ ተጠያቂውን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዴሬሳ፤ "ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ባለበት ሁኔታ እከሌ ነው ማለት አይቻልም፤ እርስ በእርስ መጠቋቆም ነው የሚሆነው" ብለዋል።
ይህንን ጥቃት ለማስቆም በአጠቃላይ "እንደ መንግሥት ያለን አቋም የጦር መሳሪያ አያስፈልግም የሚል ነው" በማለት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ወደ ሰላማዊው መድረክ እንዲመጡ እንደሚፈለግ አመልክተዋል።
በተጨማሪም አቶ ዴሬሳ "ሰላም በሌለበት እና ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አካል ባለበት ሁኔታ ለወንጀሉ ተጠያቂው እገሌ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው" ያሉ ሲሆን፤ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን መቆጣጠር እና የህግ የበላይነትን ማስከበር መሰል ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
በምዕራቡ የአገሪቱ አካባቢ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን ባይኖርም ድርጊቱ በተለይ ኢላማ ከሚያደርጋቸው የመንግሥት ባለስልጣናት አንጻር ምናልባት ፖለቲካዊ ዓላማ ሊኖረው ይችላል ተብሎ ይገመታል።
ቀደም ሲል አንዳንድ ባለስልጣንትና የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እንደሚገምቱት ከኦነግ አፈንግጦ የወጣና በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ቡድን ጥቃቱን እየፈጸመ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) የተቋቋመ ቢሆንም ስለጥቃቱ ፈጻሚዎችም ሆነ ከጥቃቶቹ በኋላ ስለተወሰዱ እርምጃዎች እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።












