በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ከ100 በላይ የኦነግ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈቱ

የቀድሞ የኦነግ ጦር አባላት

የፎቶው ባለመብት, Daniel Areri

የምስሉ መግለጫ, ወደ ሕዝብ ከተቀላቀሉት የቀድሞ የኦነግ ጦር አባላት መካከል ጥቂቶቹ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ከ100 በላይ የኦነግ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማሕበረሱ መቀላቀላቸው ተገለፀ።

የምዕራብ ጎጂ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አበራ ቡኖ ታጣቂዎቹ ወደ ማሕበረሰቡ የተቀላቀሉት በባህላዊ ሥርዓት መሠረት መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አክለውም የተያዙት ወደ 500 የሚጠጉ ታጣቂዎች መሆናቸውን ተናግረው "113 የሚሆኑት ወደ ማሕበረሰቡ ተቀላቅለዋል። አብዛኞቹ በሰላማዊ መንገድ ነው የተመለሱት" ብለዋል።

ቀሪዎቹ የቀድሞ ኦነግ አባላት በሕዝብ መያዛቸውን የገለፁት ኃላፊ "አንዳንዶቹ የኦነግ አባላት ትጥቅ ሳይኖራቸው" ወደ ጫካ መግባታቸውን ተናግረዋል።

"ከ500 ታጣቂዎች መካከል በወንጀል የተጠረጠሩት ወደ ሕግ ይላካሉ" ያሉት አቶ አበራ ቀሪዎቹ ደግሞ ሥልጠና እንደሚገቡ አስረድተዋል።

ሥልጠናው ታጥቀው ለነበሩት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ይሰጣል ያሉት አስተዳዳሪው፤ ሕዝቡ ሰላሙን የሚያደፈርሱትን አጋልጦ የሰጣቸው ሰዎች ስለሆኑ 'እንደ እስረኞች አናያቸውም' ብለዋል።

ትጥቅ ባይኖራቸውም ግን በዝርፊያ፣ ግድያ፣ በመድፈር፣ የተጠረጠሩ ሰዎች ተጣርተው ለሕግ ይቀርባሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰኔ 5 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት ላይ በእስር የሚገኙ አባሎቹ እንደሚፈቱ ተገልጦ እንደነበር አስታውሷል።

ሆኖም ግን ይላል መግለጫው የታሰሩ አባላቶቹም አለመፈታታቸውን አስታውሶ እንደ አዲስ በደጋፊዎቹና በአባላቶቹ ላይም እስር መቀጠሉን በመጥቀስ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።

በወቅቱ መንግሥት ደጋፊ ወይንም አባል ስለሆነ ብቻ የታሰረ አንድም ሰው የለም ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የኦነግ አመራሮች ከዚህ በኋላ የምናዘው ጦር የለም ማለታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የቀድሞ የኦነግ ወታደሮችና የመንግሥት ወታደሮች መካከል በደቡብና ምዕራብ ኦሮሚያ በተደጋጋሚ በሚከሰት ውጊያ ሰዎች መሞታቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።