ትራምፕ ጦርነት ከተጀመረ ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች ሲሉ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, IRIBNEWS
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነት እንደማይፈልጉ ነገር ግን በሁለቱ ሃገራት መካከል ግጭት ከተጀመረ "ውድመት " እንደሚከሰት ተናገሩ።
አርብ ዕለት ለኤንቢሲ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመነጋገር በሯ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል። ነገር ግን ኢራን የኒውክለር ጦር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈልጉ አልሸሸጉም።
በዚህ ሳምንት ኢራን የአሜሪካን ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ መጣሏን ተከትሎ አሜሪካ የአፀፋ እርምጃ ልትወስድ ወስና በመጨረሻ ሰዓት ውሳኔያቸውን መቀልበሳቸውንም ተናግረዋል።
150 ኢራናያውያን ሕይወታቸውን ያጣሉ በሚል ውሳኔያቸውን እንዳጠፉት ጨምረው ተናግረዋል።
"አልወደድኩትም፤ የአፀፋ እርምጃው ተመጣጣኝ ነው ብዬ አላሰብኩም" ብለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ኢራን ማክሰኞ ዕለት የአየር ክልሏን ጥሶ የገባውን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ መጣሏን ተናግራለች።
አሜሪካ ግን አውሮፕላኑ ዓለም አቀፉ የአየር ክልል ውስጥ ነበር ስትል ተከራክራለች።
በሁለቱ ሃገራት መካከል ውጥረቱ እየተጋጋለና እየተካረረ ሲሆን አሜሪካ በቅርቡ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የደረሰውን አደጋ ኢራን ፈፅማዋለች ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
ኢራን ደግሞ በምላሹ አቋርጣው የነበረውን የኒውክሌር ማብላላት እንደምትቀጥልበትና ከተቀመጠላት መጠንም ከፍ እንደምታደርግ ገልፃለች።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በ2015 ከኢራን ጋር የተፈራረሙትን ስምምነት አሜሪካ አልፈልግም ብላ መውጣቷ ይታወሳል።
አሜሪካ፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሰኞ ዕለት ተገናኝቶ በኢራን ጉዳይ ላይ እንዲመክር ጥሪ አቅርባለች።
















