ትራምፕ ጦርነት ከተጀመረ ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች ሲሉ አስጠነቀቁ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነት እንደማይፈልጉ ነገር ግን በሁለቱ ሃገራት መካከል ግጭት ከተጀመረ "ውድመት " እንደሚከሰት ተናገሩ።

አርብ ዕለት ለኤንቢሲ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመነጋገር በሯ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል። ነገር ግን ኢራን የኒውክለር ጦር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈልጉ አልሸሸጉም።

በዚህ ሳምንት ኢራን የአሜሪካን ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ መጣሏን ተከትሎ አሜሪካ የአፀፋ እርምጃ ልትወስድ ወስና በመጨረሻ ሰዓት ውሳኔያቸውን መቀልበሳቸውንም ተናግረዋል።

150 ኢራናያውያን ሕይወታቸውን ያጣሉ በሚል ውሳኔያቸውን እንዳጠፉት ጨምረው ተናግረዋል።

"አልወደድኩትም፤ የአፀፋ እርምጃው ተመጣጣኝ ነው ብዬ አላሰብኩም" ብለዋል።

ኢራን ማክሰኞ ዕለት የአየር ክልሏን ጥሶ የገባውን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ መጣሏን ተናግራለች።

አሜሪካ ግን አውሮፕላኑ ዓለም አቀፉ የአየር ክልል ውስጥ ነበር ስትል ተከራክራለች።

ኢራን ደግሞ በምላሹ አቋርጣው የነበረውን የኒውክሌር ማብላላት እንደምትቀጥልበትና ከተቀመጠላት መጠንም ከፍ እንደምታደርግ ገልፃለች።

ባለፈው ዓመት አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በ2015 ከኢራን ጋር የተፈራረሙትን ስምምነት አሜሪካ አልፈልግም ብላ መውጣቷ ይታወሳል።

አሜሪካ፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሰኞ ዕለት ተገናኝቶ በኢራን ጉዳይ ላይ እንዲመክር ጥሪ አቅርባለች።