ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሜታ በአውስትራሊያ የማኅበራዊ ሚዲያ ክልከላ ምክንያት 550,000 አካውንቶችን አገደ
አውስትራሊያ በልጆች ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ክልከላ የሚጥለውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረች የመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ ሜታ ወደ 550,000 የሚጠጉ አካውንቶች አገደ።
ከታኅሣሥ 10 2025 ጀምሮ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በአውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ የተደነገገው ሕግ ሥራ ላይ መዋል ጀምሯል።
የተለያዩ የዓለም አገራት እገዳውን በቅርበት በሚከታተሉበት በዚህ ወቅት የአውስትራሊያ መንግሥት እና ጉዳዩን ደግፈው የሚከራከሩ ወገኖች ልጆችን ከጎጂ ይዘቶች እና አልጎሪዝም ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ይከራከራሉ።
ሜታ እና ሌሎች ተመሳሳይ ኩባንያዎች የታዳጊዎችን የኦንላይን ደህንነት ለመጠበቅ መሰራት ያለባቸው ተጨማሪ ጉዳዮች መኖራቸውን መስማማታቸው ተገልጿል።
ሆኖም ግን ኩባንያዎቹ አንዳንድ ባለሙያዎች አሁንም ጥያቄዎች የሚያነሱባቸውን ሌሎች እርምጃዎችን መሞከራቸውን ቀጥለዋል።
ሜታ "የአውስትራሊያ መንግሥት ለወደፊት የተሻለ መንገድ ለመፈለግ ከኢንዱስትሪው ጋር ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲሳተፍ ጥሪ እናቀርባለን፤ ለምሳሌ በጅምላ እገዳዎችን ከመጣል ይልቅ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ግላዊነትን የሚጠብቁ፣ እና ለዕድሜ ተስማሚ የሆኑ የኦንላየን ላይ ተሞክሮዎችን በማቅረብ ረገድ ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ማበረታታት" ሲል በብሎጉ ላይ ጽፏል።
ኩባንያው አዲሱን ሕግ በማክበር በመጀመሪያው ሳምንት ብቻ ኢንስታግራም ላይ 330,639፣ በፌስቡክ 173,497 እና በትሬድስ ደግሞ 39,916 አካውንቶችን ማገዱን አስታውቋል።
ኩባንያዎቹ የዕድሜ ማረጋገጫ በመተግበሪያው ላይ መከናወን አለበት የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።
ይህም በተቆጣጣሪዎችም ሆነ በመተግበሪያዎቹ ላይ የሚኖር የሕግ ጫናን ይቀንሳል ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች ፈቃድ መስጠት የሚችሉበት አማራጭ መፈጠር አለበት የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
"ወጣቶች የትኛውንም መተግበሪያ ቢጠቀሙ ወጥ የሆነ እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ጥበቃዎችን ለማረጋገጥ ይህ ብቸኛው መንገድ ነው። ይህም ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳ ሕግን ለማለፍ ወደሚጎርፉባቸው አዳዲስ መተግበሪያዎች መድረስ የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት ለማስወገድ ይረዳል።"
ከአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት እስከ አውሮፓ ኅብረት ድረስ ያሉ የተለያዩ መንግሥታት የሕፃናትን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ለመገደብ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ነገር ግን ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች ጋር ተያይዞ አውስትራሊያ ወላጆች ፈቃድ መስጠት እንደማይችሉ የከለከለች ብቸኛዋ አገር ነች።
ይህም አገሪቱን በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ረገድ በዓለም ላይ እጅግ ጥብቅ ሕጎች ካሏቸው አገራት መካከል አንዷ አድርጎታል።
በዚህም የተነሳ ሕጉ በብዙ ወላጆች ዘንድ የተደገፈ እና በዓለም ላይ የመጀመሪያው ሆኗል።
መንግሥት እንደሚለው ከሆነ እገዳው ልጆች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሏቸውን "ግፊቶች እና አደጋዎች" ለመቀነስ ያለመ ነው።
አንዳንድ ባለሙያዎች ግን የአውስትራሊያ ልጆች የእድሜ ፍተሻውን የሚያካሂደውን ቴክኖሎጂ በማታለል ወይም ሌሎች፣ ምናልባትም ደህንነታቸው ወዳልተጠበቀ መተግበሪያዎች ሊፈልሱ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
አንዳንድ የአእምሮ ጤና ተሟጋቾች ደግሞ ይህ ሕግ የወጣቶችን መስተጋብር የበለጠ ይጎዳል ሲሉ ይከራከራሉ።