የኢትዮጵያ መንግሥት እና ኦነግ አብሮ ለመሥራት ከስምምነት ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel
የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ እና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) አመራሮች በአሥመራ ተገናኘተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።
የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ''ከውይይቱ በኋላ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦነግ መካከል የነበረው ጦርነት እንዲያበቃ እና ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ሃገር ውስጥ ገብቶ እንዲሠራ ከስምምነት ላይ ደርሰናል'' ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ኤርትራ ባቀኑበት ወቅት ከኦነግ አመራሮች ጋር መገናኘታቸውን ያስታወሱት አቶ ቶሌራ ''ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የተካሄደውን ሰፊ ውይይት ተከትሎ በተናጠል የተኩስ አቁም አውጀን ነበር፣ ይህም አሁን ለደረስንበት ስምምነት አስተወሰጽኦ አበርክቷል'' ብለዋል።
አቶ ቶሌራ እንደሚሉት ከሆነ ዛሬ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ የተካሄደው ውይይት በስኬት በመጠናቀቁ የኦነግ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የተቀሩት የግንባሩ አባላት ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ ያመቻቻል።
መቀመጫውን ኤርትራ ባደረገው እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ለመደራደር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ መሄዱ ይታወሳል።
የኤርትራ የኮሚኒኬሽን ሚንስትር የሆኑት አቶ የማነህ ገ/መስቀልም በትዊትር ገጻቸው ላይ ሁለቱ አካላት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።












