ኢትዮጵያ የአሜሪካን የፕላስቲክ ቆሻሻዎች እንደማትቀበል ገለፀች

የቻይና የፕላስቲክ ቆሻሻዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከጥቂት ቀናት በፊት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ፕላስቲክ ተረፈ ምርት (ቆሻሻ) ከሚላክባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ዘ ጋርዲያን የተባለው ጋዜጣ ባወጣው የምርመራ ዘገባ ላይ ተጠቅሶ ነበር።

ጋዜጣው የአሜሪካንን የቆሻሻ አወጋገድ ምስጢር ባጋለጠበት በዚህ ዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባው የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ወደየት ነው የሚሄዱት በሚልም ለዘመናት የአሜሪካ የፕላስቲክ ቆሻሻ መጣያ የነበሩት ቻይናን የመሳሰሉ ሃገራት ፖሊሲያቸውን በመቀየራቸው ሌሎች ደሃ ሃገራት እንደተመረጡ ያትታል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ባንግላዴሽ፣ ላኦስ፣ ሴኔጋል ቀጣዮቹ የአሜሪካ የፕላስቲክ ቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች መሆናቸውን በጠቀሰው በዚህ ዘገባ፤ የአገራቱ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ የላላ መሆኑ እንዲሁም፤ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም የማዋል ሥራ (ሪሳይክል) ኃይል አባካኝ በመሆናቸው እነዚህም ሃገራት ደግሞ ርካሽ የሰው ጉልበት ስላላቸው ተመራጭ እንዳደረጋቸው ጠቅሷል።

ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ብዙ ኢትዮጵያዊያን "እንዴት የሃብታም ሃገራት ቆሻሻ ማራገፊያ እንሆናለን?" በማለት ጠንካራ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ነገር ግን ወደ ኢትዮጵያ እንዲወገድ ይመጣል ስለተባለው ቆሻሻ የወጣው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ የፌደራል የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ለቢቢሲ ገልጿል።

የፕላስቲክ ቆሻሻ የሃገሪቱ ከፍተኛ ችግር በሆነበት ወቅት ኢትዮጵያ ከውጭ የምትቀበልበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ነው በፌደራል አካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የአየር ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ መሰረት አብዲሳ የገለጹት።

"የፕላስቲክ ቆሻሻ ከፍተኛ የብክለት ምንጭ ነው፤ ይህንንም ለመከላከልም በሃገር ደረጃ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ነው፤ ፍቃድ የሚሰጠውም አካል ፍቃድ የሚሰጥ አይመስለኝም፤ አይሰጥምም" በማለት መንግሥት በከተሞች አካባቢ ያለውን ብክለት ችግር ከመቆጣጠር ከፍተኛ ትኩረት በተሰጠበት ወቅት ከሌላ ሃገር ቆሻሻ ለማስገባት ፈቃደኛ አይሆንም ብለዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው ሥራ በእርሳቸው መስሪያ ቤት በኩል ከመሰራቱ አንፃር ክትትል እንደሚያደርጉ የተናገሩት አቶ መሰረት በጋርዲያን ላይ የወጣው መረጃ ስህተት እንደሆነ ገልፀዋል። የተባለውን ቆሻሻ "ሃገሪቷ በፕላስቲክ ምርቶችና አወጋገዱ እየተቸገረች ባለችበት ሁኔታ እንደማትቀበል" ገልፀዋል።

"ይሄ መሆን አይችልም፤ እንዴትስ እናስገባለን?" በማለት አቶ መሰረት ፈርጠም ብለው በጉዳዩ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች ይግባ ቢባል ፈቃድ ሰጭው አካል የትኛው ነው ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ባለሙያው ሲመልሱ "የፕላስቲክ ጉዳዮችን የሚመለከት በፌደራል አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ውስጥ ደረቅ ቆሻሻና አደገኛ ኬሚካሎች የሚባል ዲፓርትመንት አለ" ብለዋል።

ግን ከዚህ በተጨማሪ እንደተባለው በሚዲያ ብቻ ዝም ብሎ ይፋ እንደማይደረግና የእርሳቸውም ቢሮ እንዲሁም ጉምሩክም ሆነ ሌሎች አካለት በሃገር አቀፍ ደረጃ መታወቅ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

"ይህ አካባቢንም ሆነ ሰውን የሚጎዳ ከመሆኑ አንፃር ዝም ብሎ በሚዲያ ብቻ ስለተነገረ የሚገባ አይደለም፤ በሃገር ደረጃ ይፋ ሊደረግ ይገባል። ከዚህ አንጻር ለቆሻሻው ፍቃድ የሚሰጥ አካል ይኖራል ብዬ አላስብም" ብለዋል።

አንዳንድ የግል ድርጅቶች የፕላስቲክ ግብአቶችን በግላቸው ለመጠቀም ሊያስገቡ እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ መሰረት "የሚያስገቡም ከሆን ቀድመው ከሚመለከተው አካል ፍቃድ መውሰድ አለባቸው፤ ብዙ ሂደትም አለው" ብለዋል።

አቶ መሰረት ሃገሪቷ በፕላስቲክ ምርቶች ላይ ጠንካራ አቋም እንዳላት ገልፀው፤ በአዋጁ መሰረት የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገና የተለያዩ ፋብሪካዎች እየተስፋፉ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪም የፕላስቲክ ምርቶችን ፈጭቶ ወደ ውጭም እየተላከ ነው ብለዋል።

ለወደፊትም እንደሌሎች ጎረቤት ሃገራት ከፕላስቲክ ነፃ የሆነ ከተማም ሆነ አገር መፍጠር እንደሚቻልም ባለሙሉ ተስፋ ናቸው።