አዲስ አበባ፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለምን ተስፋፋ?

አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, AA Press Secretary

በኢትዮጵያ ያለውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለሚከታተል ሰው ባለፉት ጥቂት ቀናት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል። አብዛኛው ቁጥር እየተመዘገበ የሚገኘው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ነው።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በትናንትናው ዕለት ካወጣው መግለጫ መረዳት እንደተቻለው በመዲናዋ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1205 ደርሷል።

በዚሁ ሪፖርት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡባቸው ክፍለ ከተሞች አዲስ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች ናቸው። ሁለቱ ክፍለ ከተሞች ባለፉት ጥቂት ቀናት በከተማው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን በፈረቃ ሲመሩ ቆይተዋል።

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በአዲስ ከተማ እንብርት አካባቢ በልደታ፣ አራዳ፣ ጉለሌ እና ኮልፌ-ቀራንዮ ክፍለ ከተማዎች ይዋሰናል። ክፍለ ከተማው በአፍሪካ ጭምር ትልቅ ነው የሚባልለትን ገበያ መርካቶን ጨምሮ ትልቁ የአገሪቱ የአውቶብስ መናኃሪያም በዚሁ አካባቢ ይገኛል። "የአገር አቋራጭ አውቶብስ ተራ በክፍለ ከተማው አለ። ጠዋት ብቻ 4 ሺህ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይሳፈሩበታል" ሲሉ የክፍለ ከተማው የበሽታው መከላከል እና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ለበን ጸጋዬ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ስርጭት

ለቫይረሱ በክፍለ ከተማው በፍጥነት መሰራጨት የተለያዩ መላምቶች ከዚህም ከዚያም ይወረወራሉ። ቀዳሚው አካባቢው የንግድ ማዕከል በመሆኑ የውጭ ሃር ጉዞዎች ሳይቋረጡ በፊት ብዙዎች ለንግድ ወደ ቻይና እና መካከለኛው ምስራቅ መመላለሳቸው ነው።

ኑሯቸውን ለማሸነፍ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በቤት ሠራተኛነት ሄደው የሚመለሱ ሰዎችም ቁጥር ቀላል አይደለም።

በክፍለ ከተማው ወረዳ ሁለት የሚኖረው መስፍን ቀደም ሲል በልደታ ክፍለ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ የተመዘገበበት አካባቢ "ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጋር የሚዋሰን እና ያለው የነዋሪው አኗኗር እና ትስስር ጥብቅ" መሆኑን ያነሳል።

አቶ ለበን በበኩላቸው ኮሮናቫይረስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ባለበት እና የሰዎች ንክኪ በሚበዛበት አካባቢ የመስፋፋት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ ክፍለ ከተማው ቀደም ሲል እንደ ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በተደጋጋሚ መከሰቱን በምሳሌነት ያስታውሳሉ።

ወደ አራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ለመሄድ ወደ ትልቁ አውቶብስ መናኃሪያ የሚያቀናው ህዝብ ቁጥር መጠን ከፍተኛ መሆን፤ በመርካቶ ያለው የሰዎች እንቅስቃሴ እና የንግድ ልውውጥ እንዲሁም በትንሽ ቆዳ ስፋት ብዙ ሰው የሚኖርበት አካባቢ መሆኑን በተጨማሪም በምክንያትነት ያነሳሉ።

"ምንም የጉዞ ታሪክ እና ከታማሚ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች እንዲሁም በቫይረሱ ስለመያዛቸው ምንም ምልክት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን" ስርጭቱ እንዲስፋፋ ያደርጋል ያለን የአካባቢው ነዋሪ ፍቃዱ ደረጀ ነው።

መሳለሚያ፣ መርካቶ፣ እና አውቶብስ ተራን የመሳሰሉ ሰዎች በብዛት በሚጎበኟቸው ቦታዎች እና ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የንግድ ልውውጡ በጥሬ ገንዘብ መሆኑንም ለስርጭቱ በምክንያትነት የሚያስቀምጡ አሉ።

ጥንቃቄ

"አሁን አሁን 99.9 በመቶው" የአዲስ አበባ ነዋሪ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርጎ ከቤት ይወጣል ያለን መስፍን በሌላ በኩል "አንዳንዴ [ኮሮና] ያለም አይመስልም። ለወረርሽኙ መስፋፋት ስጋት ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ መርካቶ ነው። ሁሉም ነገር ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ዓይነት ከመሆኑ የተነሳ ኮሮና ያለ አይመስልም" ብሏል።

በዚህ ሃሳብ በንግድ ሥራ የተሠማራው ፍቃዱም ይስማማል። "እኔ መርካቶ ፖሊስ እየመታ ማስክ ያስደርጋል እንጂ ግፊያው እንደዚያው ነው። እንደውም ባለፈው [ቫይረሱ] መጣ የተባለ ጊዜ ማለት ነው። ሰዉ መንገዱ ሁላ ጭር እያለልን ነበር፤ አሁን አሁን ግን ኮሮና ምን ያመጣል እንየው እያሉ ነው። [. . .] ብዙም ሰው ኢትዮጵያዊያንን እየገደለ አይደለም በማለት ሰዉ ተዘናግቷል"

ቫይረሱ ወደ አትዮጵያ በገባበት ሰሞን ህብረተሰቡ የነበረው ጥንቃቄ አሁን የለም። በየአካባቢው በበጎ ፈቃድ እጅ በማስታጠብ እና ትምህርት በመስጠት ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች አሁን አይታዩም።

በታክሲ ሰልፍ፣ በንግድ ማዕከላት፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በሌሎች አካባቢዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እየተቀዛቀዘ ይገኛል።

መላመድ እና ሥራቸውን አቋርጠው የነበሩ ሰዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው እየተመለሱ መሆኑን ፍቃዱ አጫውቶናል።

ኮሮና
Banner

ስጋት

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ተገኘ ሲባል ዝግ የነበሩ ሱቆች መከፈት፤ ሰዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለስ መጀመራቸው ስጋት እንደጫረበትም ፍቃዱ ይናገራል።

ይህ ግን በአካባቢው የቫይረሱ ስርጭት ይጨምራል በሚል ብቻ አይደለም። ለሌሎች አካባቢዎችም ይተርፋል በሚል እንጂ።

ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ጉዞ ለማድረግ አውቶብስ ተራን በየዕለቱ የሚረግጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እና ለመዲናዋ አዲስ አበባም ሆነ ለአገሪቱ የንግድ ማዕከል ወደ ሆነቸው መርካቶ የሚመላለሱ ሰዎች ስርጭቱን እንዳይጨምሩት ይሰጋል።

"[በክፍለ ከተማው ቫይረሱ መጨመሩ] ስጋት አለው። አንደኛ መርካቶ ለሃገሪቱ የንግድ ማዕከል ናት ማለት ይቻላል። ወደ ተለያዩ ክልሎች ለመሄድም አውቶብስ ተራን መርገጥ ሊኖር ይችላል" ይላል ለበን።

የእለት ገቢያቸውን በአካባቢው አግኝተው ወደ ሌሎች የከተማዋ ክፍሎች የሚያመሩትንም ቤቱ ይቁጠራቸው።

ስለዚህ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ያለው የኮሮናቫይረስ መስፋፋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎችም ሆነ ለመላው አገሪቱ ስጋት መሆኑን ያነጋገርናቸው ሰዎች በሙሉ የሚስማሙበት ነው።

እርምጃዎች

ካለው ስጋት ጎን ለጎን በአካባቢው በተደጋጋሚ ከሚሰማው አምቡላንስ ደምጽ በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች ትምህርትም በስፋት እየተካሄደ ነው ብሎናል መስፍን።

እያነጋገርነው ባለንበት ወቅት እንኳን በአካባቢው ህይወት ቢያልፍ ሳይመረመር ግብዓተ መሬቱ እንዳይፈጸም ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ነግሮናል፤ እኛም ትምህርቱ ሲሰጥ በስልክ እየሰማን ነበር።

"ሰፈር ይደብራል። ፈጣሪ ይጠብቀን ትላለህ እንጂ ምንም አታደርግም። አሁን እናቶች [የምንነግራቸውን] እየሰሙ ነው። እኛም እያስተባበርን ነው። ፈጣሪ ይጠብቀን" ያለን መኖሪያው አብነት የሆነውና በአካበቢው ያሉ ሰዎችን እያስተባረ የሚገኘው ፍቃዱ ነው።

በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ቫይረሱ በዝቶባቸዋል የሚባሉ አራት አካባቢዎች ተለይተዋል። ወረዳ 1 (በተለምዶ አብነት የሚባለው አካባቢ)፣ ወረዳ 2 (በተለምዶ መርካቶ የሚባለው አካባቢ በከፊል)፣ ወረዳ 7 (በተለምዶ አውቶብስ ተራ የሚባለው አካባቢ) እና ወረዳ 8 (በተለምዶ መርካቶ የሚባለው አካባቢ በከፊል) ናቸው። [መርካቶ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ያርፋል።]

ቫይረሱ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለበት ከመጋቢት 5/2012 ጀምሮ ማህበረሰቡን እያስተማሩ እንደሚገኙ የሚገልጹት አቶ ለበን "ቤት ለቤት የሙቀት ልኬታ አሁን ሁለተኛ ዙር ጀምረናል። ሳል እና ሙቀት ያለባቸው እየተመረመሩ ነው። ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱ እና ሳል እና ትኩሳት ያላቸው ሰዎችም በተመሳሳይ ምርመራ እየተደረገላቸው ይገኛል" ብሎናል።

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ጤና ቢሮ

ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳር የጤና ቢሮ ኃላፊ ናቸው። ". . .ከመላ አገሪቱ ከ60 እስከ 70 በመቶ ኬዝ አዲስ አበባ ይሆናል ተብሎ ነው" በማለት በከተማው ሊኖር የሚችለውን የቫይረሱ ስርጭት መጠን ግምት ያስቀምጣሉ።

በኢትዮጵያ እስካሁን ከተመዘገቡት 1636 የኮሮናቫይረስ ህሙማን 74 በመቶ ወይንም 1205 ያህሉ ከአዲስ አበባ ናቸው።

ግን ይህ ቁጥር የቫይረሱ ስርጭት ትልቁ መጠን ነው ተብሎ እንደማይገመት ዶክተር ዮሀንስ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ቁጥሩ ገና የመስፋፋቱ ጫፍ ላይ አልደረሰም። ገና ነው ብለን ነው የምንጠብቀው። ጫፍ ይደርሳል የሚባልበትን ወቅት ለመለየት የተሰሩ ሞዴሎች አሉ። ይሄን ወር [ግንቦት] ጨርሰን ሰኔ መጨረሻ አካባቢ ዕድገቱ ጫፍ ላይ ሊደርስ ይችላል" ብለዋል።

መጀመሪያ አካባቢ የነበረው እጅን መታጠብ እና መጠንቀቅን የመሳሰሉ ነገሮች ቢቀዛቀዙም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ደግሞ ጨምሯል ብለዋል።

". . . እንደዚህ አይነት ወረርሽኝ ሲመጣ ረዥም ጊዜ ስለሚቆይ ማህበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖውን በማጤን ብዙ ነገሮች እንደስርጭቱ የሚቀየሩ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሁሉም መጠንቀቅ እና ሌሎችንም መጠበቅ ያስፈልጋል" ይላሉ።

አንዳንዶች በአዲስ አበባ የእንቅስቃሴ ገደብ ለምን አይጣልም ሲሉ ይጠይቃሉ። ዶክተር ዮሐንስ "በርካታ የአዲስ አበባ ህዝብ የዕለት ጉርሱን ሰርቶ የሚገባ ነው። የበለጸጉት ሃገራት ሞክረውት ያቃታቸው ነገር ነው። . . . የከተማውን እንቅስቃሴ ማቆም ማለት ሌላ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ነው የሚከተው።" በማለት እንደዚህ አይነት ነገር በእኛ አገር ሁኔታ የማይቻል መሆኑን ያብራራሉ።

ከዚህ ይልቅ እንደአማራጭ የተያዘው ቫይረሱ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች በወረዳ ወይንም በቀጠና ጠበብ ያለ ቦታ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል ስርጭቱን መቆጣጠር መሆኑን ኃላፊው ይገልጻሉ።

"በሚከሰቱበት ብሎክ እና ቀጠና እንቅስቃሴዎችን በመግታት የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የዕለት ጉርስ የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ብሎክ ቤዝድ የምግብ ባንክ እያቀረብን ልየታ እያደረግን ነው። አሁንም በዚያ እንቀጥላለን።" ሲሉ በልደታ ክፍለከተማ ለሁለት ሳምንት የተደረገውን የእንቅስቃሴ ገደብ ዓይነት እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

አሁን ቫይረሱ እየተስፋፋባቸው በሚገኝባቸው አካባቢዎች ካላቸው ባህሪ አንጻር ሊስፋፋ እንደሚችል ግምት እንደነበር ተናግረው "በአካባቢዎቹ በርካታ ናሙና እየወሰድን እንመረምራለን" ሲሉ ሃሳባቸውን ይደመድማሉ።