በአዲስ አበባ ኮሮናቫይረስን የመቆጣጠር እድል አምልጦ ይሆን?

ጭምብል ያደረገች ወጣት መኪና ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየዕለቱ ኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሕብረተሰብ ጤና ተቋም የሚወጣው ዕለታዊ መረጃ ያመለክታል።

የጤና ሚኒስትሯ፣ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩትም በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

በተለይ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር በተከታታይ እየጨመረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተገኙ ናቸው።

አርብ ግንቦት 14 ቀን 34 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ፣ ቅዳሜ 61 ሰዎች፣ ዕሁድ ግንቦት 16 ደግሞ ሰማንያ ስምንት ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸው ሲነገር ከእነዚህም መካከል 73ቱ የተገኙት አዲስ አበባ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ ባለሙያዎችን ያሳሰበው አብዛኞቹ በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች የውጭ አገር የጉዞ ታሪክና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆኑ ነው።

ለ40 ዓመታት በሕብረተሰብ ጤና ዘርፍ የሰሩት አቶ ኃይሌ ውብነህ፤ "አሁን እየተመዘገቡ ያሉት ህሙማን የጉዞ ታሪክና ንክኪ የሌላቸው መሆናቸው ያለጥርጥር ወረርሽኙ ሕብረተሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ በመሆኑ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም" ይላሉ።

ሕብረተሰቡ ውስጥ ገብቷል ሲባል የሚያዘው ሰው በሽታው የተላለፈበት ዋነኛው ምንጭ በአገር ወይም በዙሪያው ካለ ሰው ነው ማለት እንደሆነ በማብራራት፤ ይህም ወረርሽኙ በሕብረተሰቡ ውስጥ እየተዛመተ መሆኑን እንደሚያመለክት ይጠቁማሉ።

በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ የሚገኙትና የማይክሮባዮሎጂና የዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶክተር አበባየሁ ንጉሤም "ወረርሽኙ ሕብረተሰቡ ውስጥ ወደ ጎን በቀላሉ የመስፋፋት ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ ፍጥነቱም ይጨምራል" ብለዋል።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች በምርመራ እስኪታወቁ ወይም ጎልቶ ወጥቶ እስኪደረስበት ድረስም በርካታ ንክኪ ስለሚኖረው የበሽታው መስፋፋት አሳሳቢ ከመሆኑ በተጨማሪ ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ እንደሆነ ዶክተር አበባየሁ ጨምረው ያስረዳሉ።

አቶ ኃይሌ እንደሚሉት በሽታው በአገሪቱ ውስጥ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ጎን ለጎን ከአምስት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ሕብረተሰቡ በፍላጎቱ በየቦታው ያደርጋቸው የነበሩት የጥንቃቄ እርምጃዎች ከፍ ያለ ነበር።

ነገር ግን ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየላላ በተለይ በፋሲካ በዓል ሰሞን መዘናጋቱ ጎልቶ ይታይ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃይሌ፤ ከዚያ በኋላ የትራንስፖርት ገደቡ መላላት፣ እንቅስቃሴዎች እንዳበበረታታቸው ጠቅሰው "ያኔ የላላው የመከላከያ ዘዴ ነው አሁን ዋጋ እያስከፈለን ያለው" ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

ዶክተር አበባየሁም እንደሚሉት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥሩ ለሳምንታት ዝቅ ብሎ መቆየቱ በሕብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋትን ፈጥሯል። ጨምረውም እሳቸው በሚኖሩበት ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥም በተመሳሳይ ቀስ በቀስ መስፋፋቱን ያስታውሳሉ፤ "የአንድ ሳምንት መዘናጋት ከብዙ አገራት ተሞክሮ እንደታየው ብዙ ዋጋ ያስከፍላል።"

ጭምብል ያደረጉ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሽታው በሕብረተሰቡ ውስጥ በመግባቱ ቁጥሩ ከዚህም እየጨመረ እንደሚሄድ የሚናገሩት ዶክተር አበባየሁ፤ በሽታው ያለባቸው ሰዎች ሳይታወቅ ወደ ሌሎች ስለሚያስተላልፉ ከፍተኛ መጠን ላይ ሊደርስ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

ስለዚህም "መጀመሪያ ላይ ይገኝ የነበረው ቁጥር ትንሽ መሆኑና አሁን እየጨመረ መምጣቱ፤ ከፍ እያለ ሊሄድ እንደሚችል ስለሚያመለክት አሁኑኑ መወሰድ ያለባቸው እርምጃ መውሰድ ይገባል" ሲሉ ሳይረፍድ ሁሉም የሚችለውን እንዲያደርግ ይመክራሉ።

አቶ ኃይሌም በህሙማን ቁጥሩ እየጨመረ መሄድ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው አይመስሉም። በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ባለፉት ሳምንታት ከታየው አጠቃላይ የሕዝብ እንቅስቃሴ አንጻር በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄድ "የሚጠበቅ እንደሆነና በቅርብ ጊዜም ይቀንሳል የሚል ግምት የለኝም" ይላሉ።

የጤና ባለስልጣናት በአገሪቱ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 582 ሰዎች ውስጥ 377ቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን አመልክተው፤ በተለይ በልደታና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከሌሎች ቦታዎች ከፍ ባለሁኔታ መስፋፋቱን ገልጸዋል።

አቶ ኃይሌ እነዚህ የከተማዋ ከፍሎች ጎልተው ለመታየት የበቁት "ምርመራ የሚደረግባቸው ቦታዎች የበሽታው ክስተት በታየባቸውና በሚጠረጠሩ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ስለሚያደርግ ነው፤ ሁለቱ አካባቢዎች በተለይ ጎልተው የታዩት" ብለው ያስባሉ።

አክለውም በከተማዋ ከእነዚህ አካባቢዎች ውጪ ያሉ ቦታዎች ነጻ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የምርመራው ቦታ እየሰፋ ሲሄድ በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ወይም የከፋ ውጤት ሊገኝ ይችላል ይላሉ ብለው ይሰጋሉ።

በብዙ ቦታዎችም ከተጠቀሱት ክፍለ ከተሞች በበሽታው የተያዙ ብዙ ሰዎች ባይገኙ እንኳን፤ ተመሳሳይ መጠን ያለው ቁጥር ሊኖሩ እንደሚችል ያምናሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ጎልቶ በታየባቸው አካባቢዎች የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎች ለመውሰድ መንግሥት እያሰበ መሆኑን እየተነገረ ነው።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክትር ሊያ ታደሰ እንዳሉት ቫይረሱ እየተስፋፋ መሆኑን በምርመራ እየተገኙ ያሉ ውጤቶች እንደሚያመለክቱ ጠቅሰው፣ በሽታውን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴን በመገደብ የልየታ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሚኒስትሯ ጨምረው እንዳሉት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪም በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪም ሆነ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ይህም ሁለቱ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ዶክተር አበባየሁና አቶ ኃይሌ እንዳሉት ወረርሽኙ በሕብረተሰቡ ውስጥ መግባቱንና የመዛመት እድሉ ከፍ እንደሚል የሚያመለክት ነው።

በክፍለ ከተማም ሆነ በሌላ መልኩ ለይቶ እንቅስቃሴን መገደብ ብዙም እንደማይዋጥላቸው የሚናገሩት ዶክተር አበባየሁ "በከተማዋም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ቦታዎችን መለየት ሳያስፈልግ መወሰድ ያላበቸው የመከላከል እርምጃዎች በቶሎ መወሰድ አለባቸው" ይላሉ።

ነገር ግን እርምጃው የራሱ የሆነ ችግር ቢኖረውም "በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመሩ ከሄደ ሌሎችን ለመጠበቅ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣልና ሌሎች ጠንከር ያሉ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል" ብለው ይመክራሉ።

"አሁን እንደሚታየው የበሽተኞች ቁጥር ከመጨመር ወደኋላ ስለማይል የበለጠ የጥንቃቄ እርመጃዎች በመንግሥት በኩል ይወሰዳሉ ብዬ እጠብቃለሁ" የሚሉት ደግሞ አቶ ኃይሌ ውብነህ ናቸው።

በተለይ ደግሞ የበሽታው ክስተት በስፋት በታየባቸው አካባቢዎች ለየት ያለ እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሕዝብ የሚጠቅምና የበሽታውን በከተማዋ መስፋፋት ለመግታት የሚያስችል ይሆናልም ይላሉ።

በሽታው ወደ ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢና ከከተማዋ ውጪ ወዳሉ የገጠር ክፍሎች እንዳይዛመት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ ኃይሌ "የእንቅስቃሴ ገደብን በተመለከተ ያለውን የበሽታ መስፋፋት በመከታተልና ጥናት ላይ በመመርኮዝ መሆን አለበት" ይላሉ።

በተጨማሪም "አማራጭ ወደሌለው አቅጣጫ እየሄድን ነው። በየቀበሌው የቅኝት ቡድን በማሰማራት በየቀኑ ያለውን የጤና ችግርን በማሰባሰብና መረጃውን እየተከተሉ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።"

ዶክተር አበባየሁ ንጉሤም በሽታውን ለመቆጣጠር መጀመሪያ ላይ በሁሉም በኩል ሲወሰዱ የነበሩት የጥንቃቄ እርምጃዎች አሁንም ተጠናክረው በስፋት ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው አጽንኦት ይሰጣሉ።

እያንዳንዱ ሰውም "መረበሽ ሳይሆን ጥንቃቄ ላይ ትኩረት በማድረግ ራሱንና በዙሪያው ያሉ ሰዎችን ከበሽታው መጠበቅ ይኖርበታል" የሚሉት ዶክተር አበባየሁ፤ ወጪ የሌለባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውስድ የበሽታውን ስጋት መቀነስ ይቻላል ይላሉ።

"በሸታውን ለመቆጣጠር የሚያስችለንን እድል ከእጃችን እየወጣ ነው" የሚሉት አቶ ኃይሌ "ነገር ግን አሁንም የበሽታውን መስፋፋት ማዘግየት ይቻላል" ብለው ያምናሉ።

ለዚህ ደግሞ በጤና ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የተመከሩትን በሽታውን የመከላከያ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ኃይሌ "እያስተማሩ ካልሆነ ደግሞ በሕግም ቢሆን ተግባራዊ እንዲሆኑ ማደረግ" በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ ሊያቀለው ይችላል ይላሉ።

ኮሮና
Banner