ኮሮናቫይረስ፡ አገራትን ጭምብል እስከመሰራረቅ ያደረሳቸው የኮሮናቫይረስ ዲፕሎማሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአንዳንደ አገራትን እውነተኛ ባህሪ አውጥቶታል ኮቪድ-19። ጭምብል እስከመሰራረቅ የደረሰ።
ወረርሽኙን ተከትሎ በአገራት መካከል ቬንትሌተር ለማግኘት የሚደረገው ሽሚያ ለጉድ ነው። ሁሉም ቅድሚያ ለዜጋዬ ስለሚል ማለት ነው።
ክትባቱን ቀድሞ ለማግኘትም ፉክክሩ ጦፏል። ሁሉም አገር በሳይንስ የበላይነቱን ለማስጠበቅ።
የአውሮፓ ኅብረት ከኮቪድ-19 በኋላ ዕድሜ ይኖረዋል? ሲሉ መጠየቅ የጀመሩም አልጠፉም። ምክንያታቸው ደግሞ በሰሜንና በደቡብ የአውሮፓ አገራት መካከል የታየው መቃቃር ነው።
ጣሊያንና ስፔን እንዴት በችግራችን አትደርሱልንም ሲሉ በእነ ጀርመን ላይ ጥርስ ነክሰዋል።
ተንታኞች 'የኮቪድ ዲፕሎማሲ' ሲሉ ስም አውጥተውለታል ይህን ምስቅልቅል። አንዳንዶቹን ቀጥለን እንመለከታለን።
ቱርክና ስፔን
ስፔን እጅግ በወረርሽኙ ከተጎዱ አገራት ተርታ ትመደባለች። 166 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ በበሽታው ተይዞባታል፤ ከ17 ሺህ በላይ ደግሞ ሞቶባታል።
ባለፉት ሦስት ወራት የመድኃኒት እጥረት ቁምስቅሏን እንድታይ አድርጓታል። ሐኪሞቿ የመከላከያ ያለህ ይላሉ፤ ታማሚዎቿ ቬንትሌተር ይሻሉ።፡ ብዙዎቹ የህክምና ተቋማቶቿ እጅግ አስፈላጊ የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶችን በበቂ አልቀረቡም፤ ለሐኪምም ለታማሚም።
ከሰሞኑ ደግሞ ከቱርክ ጋር መቃቃር ውስጥ ገብታለች፤ ስፔን። ምክንያቱ ደግሞ በስፔን ሦስት ግዛቶች የሚገኙ የጤና ኤጀንሲዎች የገዟቸው ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ የሕክምና ቁሳቁሶችን የጫነ መርከብ በቱርክ መታገቱ ነው።
የስፔን መገናኛ ብዙኀን ነገሩን "አይን ያወጣ ሌብነት" ሲል ነው የዘገበው።
የማድሪድ ባለሥልጣናት አንካራ የህክምና መሣሪያዎቻችንን ወስዳ የራሷን በሽተኞች እያከመች ነው እስከማለት ደርሰው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን ጋዜጣ 'ኤል ሙንዶ' በበኩሉ የሕክምና መሣሪዎቹ በስፔን ትዕዛዝ ቻይና እንድታመርታቸው የተከፈለባቸው ናቸው። ሆኖም ቁሳቁሶቹ የሚመጡት ከቻይና በመሆኑና አምራቹ በቱርክ ውስጥ የሚገኝ የስፔን ኩባንያ መሆኑ ነው ነገሩን ያወሳሰበው ብሏል።
በዚህ መካከል አንካራ አገሯ የተመረቱ ቬንትሌተሮች ከአገር እንዳይወጡ ከውሳኔ ላይ ደርሳ ነበር።
ሳምንት ከፈጀ እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ጥረት በኋላ የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህክምና መሣሪያ የጫነችውን መርከብ ከቱርክ ለማስለቀቅ ችሏል።
ይህ ክስተት ኮሮናቫይረስ በአገራት መካከል የፈጠረውንና እየፈጠረ የለውን ውጥረት የሚያሳይ ነው።
ቻይናና አሜሪካ፣ ዶ/ር ቴድሮስና ትራምፕ
በአሜሪካና በቻይና መሀል የተፈጠረው ዲፕለማሲያዊ ውጥረት ከቃላት ይጀምራል። አንድ የቻይና ባለሥልጣን ቫይረሱ ዉሃን ከተማን በጥቅምት ወር ጎብኝተው በተመለሱ የአሜሪካ ወታደሮች ሳይቀመም እንዳልቀረ እንደሚጠረጥር ተናገረ።
የባለስልጣኑን ክስ ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ የሚፈልጉት ያገኙ መሰሉ። ቫይረሱንም "ቻይና ቫይረስ" አሉት። ይህ ደግሞ የቻይና ባለሥልጣናትን ጨጓራ የላጠ ጉዳይ ነበር።
የኋላ ኋላ ቻይና ነገሩን ባናከረው፣ ሰዎችን በማዳን ላይ ብንጠመድ ይሻላል በማለቷ፤ ትራምፕም ቫይረሱን "የቻይና ቫይረስ" ብለው መጥራቱን እርግፍ አድርገው ተዉት። ትራምፕን በዚህ ረገድ እስከወዲያኛው ማመን ቢከብድምድ።
መጪውን ምርጫ ለማሸነፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም የሚባሉት ትራምፕ፤ ባለፉት ዓመታት ያመጡትን የምጣኔ ሀብት ስኬት ኮቪድ-19 ጠራርጎ በልቶታል። ይህ ደግሞ አስቆጥቷቸዋል። የተቆጡት በቫይረሱ አይደለም። በአገራቸው በተቋማት ነው።
ከዚህ በኋላ እርሳቸው ዋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ ስንት ሚሊዮን ሥራ እንደፈጠሩ መናገር ብዙም ስሜት የሚሰጥ አይሆንም። በወረርሽኙ ምክንያት ሥራ ያጣው 7 ሚሊዮን ተጠግቷልና።
'ተራ ጉንፋን ነው በቅርቡ ይጠፋል' ያሉት ቫይረስ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝባቸውን አዳርሶ፣ 20 ሺህ ዜጎችን ቀጥፎ አገራዊ ቀውስ ፈጥሯል። ይህም አናዷቸዋል።
ትራምፕ ይህን ችግር በተቻለ መጠን ከራሳቸው ማራቅ ነበረባቸው። መጀመርያ ዲሞክራቶች ከቫይረሱ ጀርባ ተደብቀው የፈጠሩት ሴራ አለ ብለው ቫይረሱን ወደ ዲሞክራቶች አጠጋጉት። ቀጥለው ወደ ቻይና ወሰዱት። በመጨረሻም ዶ/ር ቴድሮስ ወደሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ገፉት።
የዓለም ጤና ድርጅት ሥራው ሁሉ 'ቻይናን ማዕከል ያደረገ ነው' ሲሉ ተችተዋል፤ ትራመፕ። በየዓመቱ ለድርጅቱ የሚሰጡትን የአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር ድጎማም በድጋሚ ሊያጤኑት እንደወሰኑ አስታውቀዋል።
ይህ ክስተት ቻይና እንደግዛቷ በምትመለከታት ታይዋን፣ የዓለም ጤና ድርጅትን በሚመሩት ዶ/ር ቴድሮስና የታይዋን የምንጊዜም አጋር በሆነችው አሜሪካ መሀል ፍጥጫን ፈጥሯል።
አሜሪካ ቻይናን "ትክክለኛውን የቫይረሱን ተጠቂዎች ቁጥር ደብቃለች" ስትል መክሰስ የጀመረችው ቀደም ብላ ነው።
የቻይና፣ የዶ/ር ቴድሮስና የታይዋን የዲፕሎማሲ ምስቅልቅ የኮሮናቫይረስ ዘመን የዲፕሎማሲ ችግር ሌላ ማሳያ ሆኖ ተወስዷል።
"በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በዓለም እንዲህ ዓይነት የጋራ ጠላት ሲከሰት አገራት ይበልጥ ተቀራርበው፤ ሊሰሩ ነበር የሚገባው" ትላለች በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመራማሪ ሶፊያ ጋስተን ለቢቢሲ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ይህ ወረርሽኝ ግን በተቃራኒው አገራት ወደራሳቸው ብቻ እንዲመለከቱና እርስበርስ እንዲፎካከሩ ነው እንጂ እንዲተባበሩ አላደረጋቸውም።"
ለዚህ የሶፊያ ነጥብ ሁነኛ ማሳያው የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ናቸው።
መጀመሪያ ጣሊያን ወረርሽኙን መቆጣጠር ሲያቅታት አባል አገራት እንዲያግዟት ጠይቃ ነበር። ሆኖም ጀመርንና ፈረንሳይ ጣሊያን የጠየቀቻቸው የህክምና መሣሪያዎች ወደ ውጭ እንዳይወጡ እግድ ጥለዋል።
"ይህ ለአውሮፓ ኅብረት ትብብርና ወንድማማችነት መልካም ምልክት አይደለም ሲሉ ጽፈዋል" በብራስልስ የጣሊያን አምባሳደር ማሪዚዮ ማሳሪ።
ጣሊያኖች በበኩላቸው ጀርመን እነሱን ለመርዳት ዳተኛ መሆኗ አስቀይሟቸዋል። በርሊን በወረርሽኙ ምጣኔ ሀብታቸው እጅግ የተጎዱ አገራትን በመደገፉ ሐሳብ ብዙም ያመነችበት አይመስልም።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላደቀቀው ኢኮኖሚ የሚሆን የብድር ቦንድ መኖር የለበትም፤ የተጎዱ አገራትንም ጭምር ወደ ችግር ይከታል ትላለች ጀርመን።
የተጎጂ አገራትን ምጣኔ ሐብት በምን ሁኔታ እንደግፍ በሚለው ዙርያ ግልጽ ልዩነት አለ። ኔዘርላንድስ፣ ኦስትሪያ እና ፊንላንድም እንደ ጀርመን ሁሉ የኮሮናቫይረስ ትብብር ቦንድን በጋራ ማተሙን አይደግፉትም።
ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ግሪክ፣ አየርላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ስሎቬኒያና ሉክዘምበርግ ግን ለነጣሊያን በኅብረቱ ደረጃ ድጋፍ ሊሰጥ ይገባ ነበር ይላሉ። ይህም የሚያሳየው በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ዘንድ የዋዛ የማይባል ክፍፍል መኖሩን ነው።
እጅግ እልህ አስጨራሽ ከሆነ ድርድር በኋላ 27 አባል አገራቱ የጋራ የብድር ማዕቀፍ አሰናድተው 500 ቢሊዮን ዶላር አጽድቀዋል።
ይህ ቁርሾና የአባል አገራት ክፍፍል ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ እንደ ወረርሽኙ ብን ብሎ ይጠፋል ተብሎ አይጠበቅም።
አክራሪ ነጭ ብሔርተኞች ኅብረቱ ከንቱ እንደሆነና ከኅብረቱ ለመውጣትም ሕዝቡን ለማነሳሳት ይጠቀሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቻይናና አዲሱ ዓለም አቀፋዊ ሚናዋ
ቻይና ወረርሽኙን በአስተማማኝ ሁኔታ መቆጣጠሯን ካረጋገጠች ወዲህ ሌሎች አገራትን ወደ መርዳቱ ተሸጋግራለች። መጀመሪያ እጇን የዘረጋቸውም ለጣሊያን ነው።
ሮም ከቻይና የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎችን እርዳታ ብቻ ሳይሆን የቻይና ሐኪሞችን ጭምር በእርዳታ አግኝታለች።
በዚህም ቻይና በጣሊያዊያኑ ዘንድ ክብርና ሞገስን አግኝታለች። #grazieCina (እናመሰግናለን ቻይና) የሚሉ የማኅበራዊ ሚዲያ የምስጋና ዘመቻዎችም ተከፍተው ነበር።
መቀመጫውን ለንደን ባደረገ አማካሪ ድርጅት የሚሰሩት የዲፕሎማሲ አዋቂ ሚስተር አንቶኒ እንደሚሉት፤ የቻይና ተግባር አሜሪካ ቸል ብላ የቆየችውንና በቅድመ ትራመፕ ዘመን የነበራትን ዓለም አቀፋዊ የተጽእኖ ፈጣሪነት ሚና የሚሞላ ነው ይላሉ።
ትራምፕ ሁሉ ነገር በቅድሚያ ለአሜሪካዊያን የሚለው ፖሊሲያቸው ብዙ አገራት የሚወዱላቸው አይደለም።
ከ2016 ወዲህ አሜሪካ ሁሉን ለእኔ ብቻ የሚለውን አተያይ በተለያየ መንገድ አንጸባርቃለች።
ይህ ከተገለጸበት መንገድ አንዱ ትራምፕ በክትባት ምርምራ ላይ የነበሩ የጀመርን ሳይንቲስቶችን በገንዘብ ሊያባብሉ የሞከሩበት መንገድ ነው።
በቅርቡ ደግሞ የህንዱ ወዳጃቸውን ፕሬዝዳንት ሞዲን ጭምር ሀይድሮክሲክሎሮኪን የወባ መድኃኒትን ለአሜሪካ ካልሰጡ እበቀልዎታለው ብለው ማስፈራራታቸው ሌላው ነው።
ህንድ የአሜሪካንን ቅጣት ፈርታ በሚመስል ሁኔታ የወባ መድኃኒቱ ወደየትም አገር እንዳይላክ የጣለችውን ዕቅድ ወዲያዉኑ አንስታዋለች።
የዲፕሎማሲ አዋቂው አንቶኒ እንደሚሉት አሜሪካ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ትጫወተው የነበረው ሚና በትራምፕ ዘመን አክትሟል፤ በምትኩ ቻይና ወደ መድረኩ ብቅ እያለች ነው።
የቻይናና ብራዚል መቋሰል
አሜሪካ ቻይናን የቫይረሱን ጉዳት መጠን ቀንሰሽ ታቀርቢያለሽ ስትል ትወቅሳለች። በወቀሳው ብራዚላዊያንም ተደምረዋል። ነገሮች እየተካረሩ ሄደው የቻይናና የብራዚል ሹሞች በማኅበራዊ ሚዲያ አንድ ሁለት መባባል ጀምረው ነበር።
በቅርቡ የቦልሶኒሮ የትምህርት ሚኒስትር አብረሃም ዌንትሮብ "ቻይና ይሄን ቫይረስ የፈጠረችው ዓለምን ለመቆጣጠር ካላት ፍላጎት ነው" ብለዋል። ይህን የጻፉበት መንገድ ደግሞ ቻይናዎችን በሚያስቆጣ መልኩ ነው።
ይህን ተከትሎ ቻይና ጨርቋን እስክትጥል ነው የተቆጣችው። ማብራሪያም ጠይቃለች።
ከጤናማ አነጋገር የራቁት የትምህርት ሚኒስትሩ እንደ ብራዚሉ ቦልሶኒሮ መዘባረቅ የሚያበዙ ናቸው። የእሲያ ሰዎች የሰውየውን ንግግር ዘረኛ ሲሉ ኮንነውታል።
"እንዲህ አይነቱ አነጋገር አስቀያሚና የዘረኛ መርዝ የተሸከመ ነው" ብለውታል በብራዚል የቻይና ኤምባሲ ተወካይ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢጠየቁም በጄ አላሉም። "ቻይና አንድ ሺህ ቬንትሌተር ከሰጠችን ግን ኤምባሲዋ ድረስ በእምብርክኬ ሄጄ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ሲሉ አፊዘዋል።
የሚገርመው የብራዚል ትልቋ የንግድ አጋር ቻይና ናት። 80 ከመቶ የሶያ አተር ብራዚል የምትሸጠው ለቻይና ነው።
የብራዚል የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት ከቻይና ቬንትሌተርና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ለማግኘት በዝግጀት ላይ ነበሩ፤ ይህ የዲፕሎማሲ ቁርሾ እስኪፈጠር ድረስ።

የፎቶው ባለመብት, Handout
ቬንዝዌላና ኮሎምቢያ
በዚህ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ዲፕሎማሲ ከመድኃኒት ባልተናነሰ አስፈላጊ ነው የሚሉ አልጠፉም።
ይህ ቫይረስ ቀድሞ የነበሩ የዲፕሎማሲ ቁርሾዎች ደግመው እንዲያንሰራሩም አድርጓል። ለምሳሌ ኮሎምቢያና ቬኒዝዌላን ማየት ይቻላል።
የኮሎምቢያ ባለሥልጣናት ለፕሬዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እውቅና አይሰጡም።
ሁለቱ ተጎራባች አገራት በዚህ የተነሳ እንደተቋሰሉ ነበሩ፡፡ በሚሊዮኖን የሚቆጠሩ የቬንዝዌላ ነዋሪዎችም በስደት ወደ ኮሎምቢያ አቅንተዋል። ለዚህ የሁለቱ ጎረቤት አገራት ጸብ ኮሮናቫይረስ አዲስ መልክ ሰጥቶታል።
በዚህ ወር መጀመርያ ኒኮላስ ማዱሮ ለኮሎምቢያው አቻቸው ኢቫን ዱኮ 2 የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማሽኖችን በስጦታ ያቀርባሉ።
ከዚያ ቀደም ብሎ የአካባቢው ሚዲያዎች "ኮሎምቢያ ቫይረሱን መመርመሪያ አንድ ማሽን ብቻ ነበራት፤ እሱም ተሰበረባት" ሲሉ ጽፈው ነበር። ይህን ተከትሎ ነበር ማዱሮ ስጦታ ያቀረቡት።
የስጦታው ጥያቄ ከኮሎምቢያ በኩል እሺም እምቢም አልተባለም። እንዲያውም እንደ ነገር ፍለጋ ሳይታይ አልቀረም።
የኮሎምቢያ ዝምታ ያናደዳቸው የቬንዝዌላ ባለሥልጣናት ነገሩን አባባሱት። የቬኒዝዌላው ምክትል ፕሬዝዳንት ደልሲ ሮድሪጎዝ የሚከተለውን በትዊተር ሰሌዳቸው ጻፉ።
"የኮሎምቢያ ባለሥልጣናት ስጦታችንን ለመቀበል አልፈቀዱም። ለኮሎምቢያ ሕዝብ ግድ እንደሌላቸው ያሳያል።"
ይህ ደግሞ በምላሹ ኮሎምቢያን አስቆጣ። አንድ የኮሎምቢያ ባለሥልጣን በራዲዮ በሰጡት ምላሽ "የቬንዝዌላ ስጦታ እጀ ሳባራ ነው፤ አሰራሩ ከእኛ ጋር አይገጥምም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግብጽና ኳታር
የኮሮናቫይረስ ዲፕሎማሲ በመካከለኛው ምሥራቅም ጥላውን አጥልቶ ቆይቷል። ምክንያቱ ደግሞ ግብጻዊያን ዜጎች በኳታር መውጣት ሳይችሉ መቆየታቸው ነበር።
ኳታር ለአልጀዚራ እንዳለችው ግብጻዊየኑ በቻርተርድ አውሮፕላን ከጉልበት ሰራተኞች ጋር ሆነው ከአገር ለመውጣት አለመፍቀዳቸው ነው ችግሩ።
ግብጽ ወትሮም ከኳታር በተቃራኒው ከቆመው የአረብ አገራት ጥምረት ጋር ነው የምትወግነው። የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ሳኡዲና ሌሎች ሆነው በትንሽዋ ኳታር ላይ ካደሙ ሦስት ዓመታት አልፏል።
ኳታር መንግሥታችንን ለመገልበጥ አክራሪ ታጣቂዎችን ትደግፋለች ሲሉ ይከሳሉ፥።
ኮሮና ይህንኑ የቆየ የዲፕሎማሲ ቁርሾን አባብሶታል።
አውሮፓና ሩሲያ
ከነዚህ ለየት የሚለው የዲፕሎማሲ ቁርሾ በአውሮፓ አገራትና በሩሲያ መካከል የተከሰተው ነው። ለሩሲያ የሚቀርብ ሚዲያ በኮቪድ19 ጉዳይ ሆን ብሎ ሐሰተኛ ዜና ለአውሮፓዊያን ይነዛል ሲሉ አውሮፓዊያኑ ይከሳሉ።
የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ይህንን ክስ "መሰረተ ቢስ" ብለውታል።
የዲፕሎማሲ ተንታኟ ሶፊያ እንደምትለው ከዚህ በኋላ በመላው ዓለም ቀኝ አክራሪዎች ኅብረት እንደማይሰራ ማስረጃ አግኝተዋል።
"ኮሮናቫይረስ ለአውሮፓዊያንና ከዚያ ባለፈም ላሉ አገራት መልካም የትብብር መመስረቻ ሊሆን በተገባ ነበር። የሆነው ግን በተቃራኒው ነው።"
አንድ የጋራ ጠላት ካላስማማ ምን ሊያስማማ ይችላል?













