ዶናልድ ትራምፕ ፡ "ኮሮናቫይረስን የሚያጣጥሉት ሆነ ብለው ነው" አሜሪካዊው ጋዜጠኛ በመፅሃፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቦብ ውድዋርድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ነው። በዋሽንግተን ፖስት በሪፖርተርነት አሁን ደግሞ በተባባሪ አርታኢነት እየሰራ ይገኛል።
ውድዋርድ በአገሪቱ እጅግ የተከበረ ጋዜጠኛ ነው። ዶናልድ ትራምፕን ከታኅሳስ እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት ብቻ 18 ጊዜ ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል።
ታዲያ ጋዜጠኛው ከቀናት በኋላ ለንባብ በሚያበቃው 'ሬጅ' በተሰኘውና በዶናልድ ትራምፕ ላይ በሚያተኩረው መፅሐፉ "ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ኮቪድ -19 አሜሪካን ክፉኛ ከመምታቱ አስቀድሞ ከጉንፋን በላይ ገዳይ በሽታ መሆኑን ያውቁ ነበር፤ ይሁን እንጅ ይህን የጤና ቀውስ ማጣጣል ይፈልጋሉ" ብሏል።
ትራምፕ በአሜሪካ አንድም ሰው በቫይረሱ ሕይወቱ ሳያልፍ በፊት 'ቫይረሱ ገዳይ ነው' ሲሉ እንደነገሩት ውድዋርድ እርሳቸውን ጠቅሶ ፅፏል።
ፕሬዚደንቱ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ፤ ሕዝባቸውን ልክ ካጣ ጭንቀት ለማላቀቅ ስለሚፈልጉ እንደሆነ ነግረውታል።
ረቡዕ ዕለትም የተወሰኑ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በፕሬዚደንቱ እና በጋዜጠኛው መካከል የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን የተወሰነ ክፍል የለቀቁ ሲሆን፤ ሪፖርቱ በወረርሽኙ፣ ዘር እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
በአገሪቱ ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ እስካሁን ከ190 ሺህ በላይ አሜሪካዊያን ሕይወታቸው አልፏል።
መፅሐፉ ስለ ትራምፕና ስለቫይረሱ ምን ይላል?
በመፅሐፉ ውስጥ ፕሬዚደንት ትራምፕ በአደባባይ ይናገሩት ከነበረው በላይ ስለ በሽታው አስከፊነት ያውቁ እንደነበር ተጠቅሷል።
የካቲት ወር ላይም ኮሮናቫይረስ ከጉንፋን የከፋና ገዳይ እንደሆነ ለጋዜጠኛው ውድዋርድ ነግረውታል።
ትራምፕ በሽታው በአየር ላይ እንደሚተላለፍም ለፀሐፊው የነገሩት በፈረንጆቹ የካቲት የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ነበር።
"ይህም ከመንካት በላይ አደገኛ ነው። ነገሮችን መንካት የለብንም። አይደል? ነገር ግን አየሩን ትተነፍሳለህ፤ በዚያ ነው የሚያልፈው፤ ያ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው፤ እንዲህ ነው ልትለው አትችልም። ከአስቸጋሪ ጉንፋን በላይ ገዳይ ነው" ነበር ያሉት።
ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ትራምፕ ቫይረሱ በቁጥጥር ሥር እንደሚውል ቃል ገብተው ነበር። በቅርብም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ ዜሮ እንደሚወርድ ተናግረዋል። በአደባባይም "ጉንፋን ከኮቪድ -19 በላይ አደገኛ" እንደሆነ አመላክተው ነበር።
በፈረንጆቹ መጋቢት 10 ላይም በካፒቶል ሂል [የአሜሪካ ምክር ቤት] "ተረጋጉ፤ በሽታው ይጠፋል" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ማለትም ዋይት ሐውስ ወረርሽኙ ብሔራዊ አደጋ መሆኑን ካወጀ ከቀናት በኋላ ደግሞ ፕሬዚደንቱ "ሁልጊዜም ቫይረሱን ማጣጣል እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም በሕዝቤ ዘንድ ጭንቀት መፍጠር አልፈልግም" ሲሉ ለውድዋርድ ነግረውታል።
ዋይት ሐውስ ያለው ምን ነበር?
ረቡዕ ዕለት ፕሬዚደንት ትራምፕ "ሰዎች ላይ ፍርሃት መልቀቅ አልፈልግም፤ ጭንቀት መፍጠርም እንደዚያው፤ እንዳላችሁት ይህችን አገርም ሆነ ዓለምን እብደት ውስጥ አልከትም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ አክለውም "በራስ መተማመን እና ጥንካሬን ማሳየት እንፈልጋለን" ብለዋል።
በመጪው ህዳር ወር ላይ ዳግም ለፕሬዚደንትነት የሚወዳደሩት ትራምፕ፤ የጋዜጠኛው ውድዋርድ መፅሐፍ "ፖለቲካዊ ማጠልሸት ነው" ብለዋል።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካይሊ ማክናኒ መፅሐፉን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ "ፕሬዚደንቱ ቫይረሱን አጣጥለው አያውቁም፤ ፕሬዚደንቱ መረጋጋትን ነው የገለፁት እዚህ ላይ ቀልድ ያውቁም" ሲሉ ተናግረዋል።
የትራምፕ ተቀናቃኝ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ላይ "ገዳይ የሆነው በሽታ አገራችንን ክፉኛ ሲያጠቃ ፕሬዚደንቱ ሆነ ብለው ሥራቸውን አልሰሩም። ወረርሽኙ የሞት ወይም የሽረት ጉዳይ ነበር፤ ይህም የአሜሪካን ሕዝብ መካድ ነው" ብለዋል።















