የአሜሪካ ምርጫ፡ ዶናልድ ትራምፕ ምርጫው ይጭበረበራል እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ "ዲሞክራቶች ኮሮጆ ሊገለብጡ ይችላሉ" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናገሩ።
ይህን ያሉት በርካታ ሕዝብ በታደመበት በታላቁ የሪፐብሊካን ጉባኤ ነው።
ፓርቲያቸው ለኅዳሩ ምርጫ ዳግም እንዲወዳደሩለት በዕጩነት ያቀረባቸው ሲሆን እሳቸውም ይህንን በይፋ ተቀብለዋል።
በዚሁ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ አወዛጋቢ ንግግር አድርገዋል።
"የአሜሪካንን ሕዝብ ለማጭበርበር ዲሞክራቶች ኮቪድ-19ን ሊጠቀሙ ይችላሉ" ሲሉ ተቀናቃኞቻቸውን ከሰዋል።
የሪፐብሊካን ፓርቲ ታላቁ ጉባኤ እየተካሄደ ያለው በኖርዝ ኮሮላይና ግዛት፣ ሻርለት ከተማ ነው።
ጉባኤው ዛሬ የመጀመሪያ ቀኑ ሲሆን ለቀጣይ ሦስት ቀናት ይዘልቃል።
ትራምፕ ሰዎች በፖስታ ቤት በኩል ድምጽ የሚሰጡበት አሰራር ለመጭበርበር የተመቸ እንደሆነ ጠቆም አድርገው አልፈዋል።
የሕዝብ ቅድመ አስተያየት ቅኝቶች እንደሚያሳዩት ትራምፕ በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ሕዝብ ዘንድ ያላቸው ቅቡልነት ከጆ ባይደን በትንሹ ያነሰ ነው።
የዛሬ አራት ዓመት በዚህ ጊዜ በተመሳሳይ ከምርጫው በፊት በተሰፈሩ የሕዝብ የቅቡልነት ቅኝቶች መለኪያ በሒላሪ ክሊንተን እየተመሩ እንደሆነ ያመላክቱ ነበር።
"ዲሞክራቶች ይህንን ምርጫ ሊያሸንፉን የሚችሉት ሲያጭበረብሩ ብቻ ነው" በማለት የምርጫው ተአማኒነት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖር በር የሚከፍት ሐሳብ ሰንዝረዋል፤ ትራምፕ።
ትራምፕ ከአራት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ሒላሪ ክንሊንተን ምርጫውን ልታጭበረብር እንደምትችል ይናገሩ ነበር።
ትራምፕ ሪፐብሊካንን ወክለው እንዲወዳደሩ በይፋ የተመረጡት ትናንት ሰኞ በነበረው የሻርለት ከተማ ጉባኤ ላይ ነው።
ምንም እንኳ በጉባኤ አካሄድ መሰረት ዕጩ ፕሬዝዳንት ንግግር የሚያደርገው ዕጩነቱን በይፋ ከተቀበለ በኋላ ቢሆንም፤ ትራምፕ ግን ይህን ደንብ ጥሰው መነጋገሪያውን ጨብጠው ዘለግ ያለ ንግግር ማድረግ ጀምረዋል።
ደጋፊዎቻቸው በንግግራቸው መሀል "አራት ተጨማሪ ዓመታት፤ ለእርስዎ!" እያሉ ለፕሬዝዳንቱ ሞቅ ያለ ድጋፍ ሲያሰሙ ነበር፡፡
ደጋፊዎቻቸው ይህንን ሲሉ ትራምፕ ቀበል አድርገው የሚከተለውን ተናግረዋል።
"እንዲያውም ዲሞክራቶችን ለማሳበድ ከፈለጋችሁ መዘመር ያለባችሁ 'አራት ተጨማሪ ዓመታት እያላችሁ ሳይሆን 12 ተጨማሪ ዓመታት' በማለት መሆን ይኖርበታል።"
ትራምፕ ይህን ያሉት እንዲያው ለቀልድ ጨዋታ ይሁን ወይስ ከልባቸው 12 ዓመታት በሥልጣን መቆየት ወደው ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።
በአሜሪካ ሕገ መንግሥት በ1951 የጸደቀው 22ኛው ማሻሻያ ላይ አንድ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሁለት የአስተዳደር ዘመኖች ብቻ ይኖሩታል። በዚህም በሥልጣን ላይ መቆየት የሚችለው ቢበዛ ለ8 ዓመት ይሆናል ሲል ይደነግጋል።
ትራምፕ ቢሆንላቸው ረዥም ዘመን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የመቆየት ፍላጎት እንዳላቸው በአንዳንድ አጋጣሚዎች ጥቁምታን ሰጥተው ያውቃሉ።














