ጆ ባይደን ‹‹ከጨለማው ዘመን አወጣችሁ ዘንድ ምረጡኝ›› አሉ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አራተኛ ቀኑን በያዘው የዲሞክራቶች ታላቅ ጉባኤ የማሳረግያ ንግግር ያደረጉት ጆ ባይደን፣ የድቅድቅ ጨለማ ዘመን ሊያበቃ ይገባል አሉ።

እጩው ፕሬዝዳንት ጆ በይፋ የዲሞክራቲክ እጩነቱን ተቀብለዋል።

ጆ ባይደን በፖለቲካ ውስጥ ብቻ 47 ዓመታትን አሳልፈዋል። አሁን 77 ዓመታቸው ሲሆን በኅዳር 3 ምርጫ ቢመረጡ ወደ ዋይትሀውስ ሲገቡ 78 ይሆናቸዋል።

ያን ጊዜ በታሪክ ሽማግሌው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ። ዶናልድ ትራምፕ የጆ ታናሽ ናቸው። ገና 74 ላይ ነው ያሉት።

ጆ ባይደን ከትውልድ ግዛታቸው ዊልሚንግተን፣ ዴሌዌር በቀጥታ ባደረጉት መራር ንግግር ራሳቸውን ብርሃን፣ ዶናልድ ትራምፕን ደግሞ በጨለማ መስለዋል።

ሰውዬው አሜሪካንን ለረዥም ጊዜ ጨለማ ውስጥ አቆይቷታል ብለዋል። ሆኖም ዘለግ፣ መረር ባለው ንግግራቸውን አንድም ጊዜ ትራምፕን በስም አልጠቀሱም፣ አመላከቱ እንጂ።

‹‹አሁን ያለን ፕሬዝዳንት ብዙ ቁጣ ቀስቅሷል፣ ብዙ ፍርሃት ፈጥሮብናል፣ ብዙ ከፋፍሎናል›› ሲሉ የትራምፕ ዘመን ለአሜሪካ ምጥ ሆኖባት እንደቆየ አመላክተዋል።

አሁን የሕዝብ ስሜቶችና አስተያየቶችን በሚተነብዩ የዳሰሳ ዘዴዎች የአሜሪካ ሕዝብ ልቡ በተወሰነ መልኩ ወደ ባይደን እንደዞረ ይነገራል።

ነገር ግን ለምርጫው ገና 75 ቀናት ስለሚቀሩ ውጤት ይህን ይመስላል ብሎ ከወዲሁ መተንበይ ከባድ ይሆናል። ጆ በትውልድ ግዛታቸው ደለዌር በሚገኝ ባዶ አዳራሽ ሆነው ባደረጉት የማሳረጊያ ንግግር ከጨለማ ወደ ብርሃን ይዣችሁ እወጣለሁ ብለዋል።

‹ከፍርሃት ይልቅ ተስፋን፣ ከልቦለድ ይልቅ እውነትን ከአድሎ ይልቅ ፍትህን ይዤ መጥቻለሁ።›

ጆ ባይደን የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩነቱን በይፋ በተቀበሉበት ንግግራቸው አንድም ጊዜ ‹‹ዶናልድ ትራምፕ›› የሚል ስም ባያነሱም ትራምፕ ጆ ባይደንን ስም ባነሱባቸው አብዛኛዎቹ አጋጣሚዎች ‹‹እንቅልፋሙ ጆ›› በሚል ያንጓጥጧቸዋል።

ይህ የትራምፕ ስልት በሂላሪ ጊዜም የነበረ ነው። ሒላሪ ክሊንተንን ‹‹ቀጣፊዋ ሒላሪ›› ይሏት እንደነበር አይዘነጋም።

የጆ ባይደንን የማሳረጊያ ንግግር ተከትሎ ትራምፕ በፍጥነት ወደ ትዊተር ሰሌዳችው ገብተው ‹‹ጆ ባይደን ላለፉት 47 ዓመታት በፖለቲካ ዓለም ሳለ አሁን የሚናገረውን ነገር አንዱንም አላሳካም፣ ወሬ ብቻ›› ብለዋቸዋል።