ኢትዮጵያ፡ በደረሰው የጎርፍ አደጋ 130 ሺህ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል

በኬንያና በኢትዮጵያና ድንበር አካባቢበጎርፍ የጠትለቀለቀ መንደር (ፎቶ ፋይል)

በኢትዮጵያ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተነሳ 170 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ጉዳት ሲደርስባቸው 130 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር ለቢቢሲ ገለፁ።

ኮሚሽነሩ አቶ ዳመነ ዳሮታ ከዚህ በፊት የነበረውን ልምድ ከግንዛቤ በማስገባት በዚህ ዓመት ክረምት ወቅት በጎርፍ ምክንያት ወደ 2 ሚሊየን ያህል ሰዎች ሊጎዱ እንዲሁም 434 ሺህ ያህሉ ደግሞ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሎ ግምት መያዙን ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ ከሆነ እስካሁን ድረስ በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ በአፋር ክልል የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ወደ 67 ሺህ 885 አካባቢ ሲሆን፣ 40 ሺህ 130 አካባቢ ደግሞ መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ኮሚሽነር ዳመነ አክለውም ደቡብ ኦሞ ዳሰነች አካባቢ በኦሞ ወንዝ ሙላትና የግቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ ውሃ በተወሰነ መልኩ መልቀቁን ተከትሎ በደረሰ የጎርፍ አደጋ በኦሞ በሚገኙ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች እንዳይጎዱ ከሚኖሩበት አካባቢ የማውጣት ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል።

እነዚህ ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ መደረጉን ገለፀው ከ10ሺህ በላይ ለሚሆኑት የተለያዩ ድጋፎች ደርሷል ብለዋል። ለቀሪዎቹ 5ሺ ሰዎች ደግሞ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

ዘንድሮ በጎርፍ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ለቢቢሲ የገለፁት ኮሚሽነሩ፣ ነገር ግን ኮሚሽኑም ሆነ መንግሥት ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ ዝግጅት ያደረጉበት ዓመት እንደነበር ለቢቢሲ አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት በልግ ወቅት በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት 470 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ጉዳት ሲደርስባቸው ከ300 ሺህ በላይ ደግሞ መፈናቀላቸውን ኮሚሽነሩ ጨምረው አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ይህን የበልግ ወቅት አደጋን በመቋቋም ላይ ባለበት ወቅት የክረምቱ ዝናብ ከበልጉ ዝናብ ጋር ተያይዞ በመምጣቱ ወንዞችና ግድቦች በመሙላታቸው በርካቶች ለአደጋ መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ በተለየ ሶስት ጊዜ የጎርፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱን ገልፀው ሁለቱ ማስጠንቀቂያዎች የወጡት በዚህ ክረምት ወቅት መሆኑን አብራርተዋል።

እስከ መስከረም መጨረሻ ተከታታይ ዝናብ ስለሚኖር ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሊከሰት እንደሚችል የገለፁት ኮሚሽነሩ ነሐሴ መጨረሻዎቹ ላይ የተንዳሆ ግድብ ሊሞላ ስለሚችል ቀጣይም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ፣ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስም የከሰምና፣ የቆቃ ግድቦች እየሞሉ እንደሚሄዱ በመግለጽ ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመከላከኛውና፣ የታችኛው አዋሽ ላይ ከፍተኛ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው በመግለፅ በዚህም የተነሳ በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ በዚህ የክረምት ወቅት የደረሰው ጉዳት መቀነሱን ተናግረዋል።