ሳዑዲ አረቢያ ፡ በእስር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ላይ እንዳሉ አምነስቲ አመለከተ

ጠባብ ቦታ ላይ የሚገኙት ስደተኞች
የምስሉ መግለጫ, ጠባብ ቦታ ላይ የሚገኙት ስደተኞች በእንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ይናገራሉ

በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች አያያዝ በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባካሄደው ምርመራ አዳዲስና አሰቃቂ ዝርዝር መረጃ ማግኘቱን አስታወቀ።

ድርጅቱ እንዳለው በዚህም ሳቢያ የስደተኞቹ ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን አመልክቶ ሦስት ኢትዮጵያዊያን መሞታቸውን በእስር ቤቶቹ ካሉ ስደተኞች ማረጋገጡን ስለሁኔታው ባወጣው መግለጫ ጠቅሰወል።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ጨምሮም የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹ ያሉበት አደገኛ ሁኔታ እንዲያሻሽል እንዲሁም ነጻ እንዲወጡ የጠየቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም የስደተኞቹ አያያዝ እንዲስተካከል ግፊት እንዲያደርግና ፈቃደኛ የሆኑትም ወደአገራቸው እንዲመለሱ የሚደረግበትን መንገድ እንዲፈልግ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በስደተኛ ማቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ጉዳይ ሪፖርቶች ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ጀምሮ እየተከታተለ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ለቢቢሲ ገልጸው፤ በተጨማሪም ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ የሚገልጹ ሪፖርቶች በሚወጡ ጊዜም ጉዳዩን ለሳዑዲ ባለስልጣናት በማሳወቅ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ከመጠየቅ ተቆጥበው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የየመን አማጺያን በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊን ስደተኞችን፣ ከየመን አስወጥተው በማባረራቸው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገብተው ለሕይወት አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።

አምነስቲ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደተናገሩት ለሁለት ሆነው በሰንሰለት መታሰር፣ በታሰሩበት ክፍል ውስጥ እንዲጸዳዱ መደረግ፣ ለ24 ሰዓታት በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ ማድረግን ጨምሮ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ የመከራ ሕይወትን እየመሩ ነው።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ከተለያዩ ታሳሪዎች ያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ እንዳመለከተው በእስር ቤቱ ውስጥ የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። በተጨማሪም በገለልተኛ ሁኔታ ለማረጋገጥ አልቻልኩም ያላቸው ቢያንስ የአራት ኢትዮጵያውያንን ሞት መስማቱን አመልክቷል።

በእስር ቤቱ ውስጥ ባለ በሽታ፣ የምግብና ውሃ ችግር እንዲሁም የህክምና አገልግሎት አለመኖር ለሞት የሚዳረጉትን ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ሪፖርቱ ጠቅሷል።

"የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከአገራቸው የወጡት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ለማሰብ አስቸጋሪ የሆነ ጭካኔ እየገጠማቸው ነው። በተጨናነቀ ሁኔታ በበሽታና ሞት ተከብበው ካሉት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገዋል" ያሉት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የስደተኞች ጉዳይ አጥኚና አማካሪ የሆኑት ማሪ ፍሪስቲየር ናቸው።

ጨምረውም በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እርጉዝ ሴቶች፣ ጨቅላ ህጻናትና ልጆች እንዳሉ አመልክተው የሞቱ ልጆች እንዳሉ መስማታቸውን ተናግረዋል።

"የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ተጨማሪ ስደተኞች ከመሞታቸው በፊት የእስር ቤቱን ሁኔታ እንዲያሻሽሉትና በጅምላ ታስረው የሚገኙትን ሁሉንም ስደተኞች በአስቸኳይ እንዲለቋቸው እንጠይቃለን" ብለዋል።

አምነስቲ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹ እንዲቆዩ የተደረገበትን ቦታ በጊዜያዊነት እንዲያሻሽል ግፊት እንዲያደርግና ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎቹ ወደ አገራቸው በአስቸኳይ የሚመለሱበትና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን መንገድ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል።

ይህንንም በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታዋ ወ/ሮ ጽዮን ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "በስደተኞች ማቆያ ቦታዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየተነጋገረ ነው" ብለዋል።

ጨምረውም ኢትዮጵያውያኑ ባሉበት ቦታ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩና ቀስ በቀስም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህጻናት ልጆች ያሏቸው እናቶችና ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች ቅድሚያ በመስጠት፣ በተለያዩ ጊዜያትም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንና ይህም እንደሚቀጥል ወ/ሮ ጽዮን ገልጸዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ስላሉበት ሁኔታ በዝርዝር ለመረዳት ከባለፈው ዓመት ሰኔ እስከ ሐምሌ ድረስ በእስር ቤቱ ውስጥ ያሉ 12 ኢትዮጵያውያንን በማነጋገር በተለያየ መልኩ የተረጋገጡ መረጃዎችን መሰብሰቡን አመልክቷል።

ቢቢሲ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ በተለያዩ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ኢትዮጵያዊያንን በማነጋገር ተመሳሳይ መረጃ ማውጣቱ ይታወሳል።

በተጨማሪም ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ስላሉበት አሰቃቂ ሁኔታ በተመለከተ ከዘገቡ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የተለያዩ ተቋማት በሳዑዲ መንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን መሰማታቸው ይታወሳል።