ኮሮናቫይረስ፡ ትምህርት ሊጀመር ስለመሆኑ ትምህርት ማኀበረሰቡ ምን ይላል?

ተማሪዎች በትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Bartosz Hadyniak

አኮቴት የሻው የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ እየተዘጋጀ ሳለ ነው የኮሮቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ መግባቱ የተነገረው። ስለ መጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሲናገር ሞዴል ሊፈተን እየተዘጋጀ እንደነበርና ቅድሚያ ትምህርት ሲዘጋ ለሁለት ሳምንት ብቻ መባላቸውን ያስታውሳል።

"ሰኞ ሞዴል ልንፈተን እየተዘጋጀን እያለ ነው ትምህርት የለም ተብሎ የተነገረን" በማለት በጊዜው በእሱና በጓደኖቹ ዘንድ የፈጠረውን ደስታ አይረሳም።

ነገር ግን ትምህርት ለ15 ቀን ብቻ ሳይሆን ለተራዘመ ጊዜ እንደሚዘጋ ሲታወቅ እቅዱ ሁሉ ተስተጓጎለ።

እርሱን ጨምሮ አብዛኞቹ ተማሪዎች በተለያዩ አገራት የትምህርት እድል ለማግኘት እየሞከሩ ስለነበር የወረርሽኙ መከሰት እና የትምህርት መቋረጥ እቅዳቸውን ዳግም እንዲከልሱ አድርጓቸዋል።

ለሰባት ወራት ከትምህርት ገበታ ውጪ የነበሩት እነ አኮቴት የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ለፈተና እየተዘጋጁ ነው። ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል ተብሎ ሲጠየቅም "ዝግጅቱ እንደመጀመሪያው አይሆንም" ይላል።

ትምህርት ሚኒስቴር ለተፈታኝ ተማሪዎች የ45 ቀን የዝግጅት ጊዜ እንዳዘጋጀ ይፋ ሲያደርግ ተማሪዎች ራሳቸውን ከቴክኖሎጂ እና ከትምህርት ቤት ድባብ ጋር ዳግም ማስተዋወቅ ራሱን የቻለ ጊዜ እንደሚጠይቅ በማንሳት ጊዜው በቂ አለመሆኑን ይናገራል።

ትምህርት ቤት ውስጥ ቢሆኑ ኖሮ በርካታ ሞዴል ፈተናዎችን እንደሚወስዱ የሚጠቅሰው አኮቴት በጊዜው እጥረት "ብዙዎቻችን ደስተኞች አይደለንም" ይላል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ምንም ቢሆን ፈተናውን ተፈትኖ ለመገላገል ያስባል። ለዚህ የሚጠቅሰው ምክንያት ደግሞ እየሞከራቸው ያሉት የትምህርት ዕድሎችን ለመቀጠል የመልቀቂያ ፈተና ውጤት ማስፈለጉን ነው።

"መከፈቱ ደስተኛ አላደረገኝም"

ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በደረጃ ለመክፈት ውሳኔ ያሳለፈው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት ዝግጁነታቸውን ለማጣራት ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጣው ኮሚቴ ሲያረጋግጥ ብቻ እንደሚሆን አስታወቋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ይሁንታ የሚሰጠው ኮሚቴ በአብላጫው ወላጆች የሚሳተፉበት ሆኖ ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከአስተዳደር ዘርፍና ከወላጆች የተሰባሰበ እንደሆነ ገልጿ።፡

የትምህርት ቤቶች መከፈት የፈጠረባቸውን ስሜት የጠየቅናቸው መምህር ተስፋሚካኤል ክፍሌ 'የለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት' ርዕሰ መምህር ናቸው።

ትምህርት ቤታቸው ለ2013 የትምህርት ዘመን 2000 ያህል ተማሪዎችን መመዝገቡን የሚናገሩት አቶ ተስፋሚካኤል፣ በምዝገባ ወቅት ያስተዋሉት የተማሪዎቹ ቸልተኝነት አስደንግጧቸዋል።

በዚህ ዓይነት ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት በእረፍት ሰዓት በሽታውን በምን መልክ መከላከል ይቻላል የሚለው ስጋት ፈጥሮባቸዋል።

"ተማሪዎቹ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸው ብቻ ከቫይረሱ የሚያስጥላቸው ነው የሚመስላቸው" በማለት የአካል ርቀትን ማስጠበቅ ግን ፈተና መሆኑን ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸው በግላቸው ትምህርት እንዲከፈት መወሰኑ የፈጠረባቸውን ስሜት ሲጠየቁም "መከፈቱ ደስተኛ አላደረገኝም" ሲሉ መልሰዋል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው ትምህርት በተዘጋበት ወቅት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ነው።

ተማሪዎቹ የኮሮናቫይረሰ ስርጭትን ለመከላከል ስለተቀመጡት መንገዶች ተገንዝበው ንቁ ሲሆኑ አይታዩም የሚሉት መምህሩ ጥግግታቸው በጣም የተቀራረበ መሆኑን በምዝገባ ወቅት ማስተዋላቸውን ያነሳሉ።

እንደ እርሳቸው ከሆነ ትምህርት ቤታቸው የትምህርት ሚኒስቴርን መመሪያ ተከትሎ በአንድ ክፍል ውስጥ 25 ተማሪዎችን ብቻ ለማስተማር ይቸገራል።

"በሦስት ፈረቃ ከሆነ ብቻ በ25 ልናስተናግድ እንችላለን። እንጂ በሁለት ፈረቃ 35 ነው [ማስተናገድ የምንችለው]" ይላሉ።

በመዋዕለህጻናት የምትማር ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild

ለዚህም ምከክንያታቸው በአሁኑ ወቅት በአንድ ክፍል እስከ 70 የሚደርሱ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ነው። እነዚህን ተማሪዎች በሁለት ፈረቃ ይማሩ ቢባል እንኳ 35 ተማሪዎችን ብቻ በአንድ ክፍል ውስጥ ማስተናገድ እንደሚችሉ ይገልፃሉ።

ትምህርት ተዘግቶ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ሥራዎች ማከናወናቸውን የሚገልፁት መምህሩ፤ የንጽህና ቤቶች ቁጥርን ከፍ ማድረግና በንጽህና ቤቶቹ አካባቢ የውሃ መስመር ዝርጋታ መከናወኑ ይናገራሉ።

መማሪያ ክፍሎች በአጠቃላይ የፀረ ተዋህሲያን ርጭት እንደተደረገላቸው፣ በትምህርት ቤቱ ውስጥም ስለበሽታው ግንዛቤን የሚፈጥሩ የተለያዩ ማስታወቂያዎች መለጠፋቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

በመጪዎቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥም ትምህርት ቤቶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከላክሎ ለማስተማር የሚያስችል ደረጃ ላይ መሆናቸውንና አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልተው ትምህርት መጀመር መቻላቸውን ኮሚቴው ገምግሞ ውሳኔ እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

የተማሪ ወላጆች ትምህርት ሊጀመር በመሆኑ ደስተኛ ናቸው ያሉት መምህሩ፤ ልጆቻቸው ቤት ውስጥ ተቀምጠው የኮሮናቫይረስ መከላከያዎችን በአግባቡ እየተገበሩ ስላልሆነ አንደኛውኑ ትምህርት ቤት ሄደው ቢውሉ ይሻላል የሚል አስተያየት መስማታቸውን ይናገራሉ።

የወላጆች ኮሚቴ፣ ኅብረተሰቡም ተማሪዎቹ ትምህርት መጀመር እንዳለባቸው ሙሉ እምነት እንዳለው በማከልም "ከነችግሩም ቢሆን ወደ ትምህርት መግባት አለብን" የሚል አመለካከት እንዳላቸው ይናገራል።

ኮሮና
Banner

ሁለት ልብ

አቶ ኤፍሬም ታዬ ሁለት ልጆች ያሏቸው ሲሆን ሁለቱም በእዲስ አበባ በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስመዝግበዋቸዋል።

ልጆቹን በአካል ትምህርት ቤት ልኮ ለማስተማር ስጋትና ፍራቻ ቢኖርባቸውም እንዳስመዘገቧቸው ግን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልጆችን በአንድ አካባቢ ሰብስቦ አትነካኩ ማለት ፈታኝ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ኤፍሬም፤ እስከ መቼ ድረስ ከትምህርት ቤት ርቀው በዚህ ሁኔታ ይቆያሉ የሚለው ሌላው መንታ ስሜት ውስጥ የከተታቸው ጉዳይ ነው።

የአቶ ኤፍሬምና የባለቤታቸውን ልብ የከፈለው ነገር ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎችን ሲቀበሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ማሟላት ስላለባቸው ነገሮች ተዘርዝሮ አለመስማታቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ መከላከል ሥራውንና ቫይረሱ ያለበትን የስርጭት ሁኔታ ሲመለከቱ "የግድ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው መማር አለባቸውን?" ሲሉ እንደሚጠይቁ ይናገራሉ።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የግል ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው በቆዩባቸው ወቅት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ልጆቹ እየተማሩ ዓመቱን መጨረሳቸውን ያስታውሳሉ።

ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት በሚልኩበት ወቅት ትምህርት ቤቱ ያሟላቸውን ነገሮች ለመገምገምና ከትምህርት ቤቱም ጋር ለመነጋገር የሚያስችላቸውን መከታተያ መስፈርት ከትምህርት ሚኒስቴር አለመስማታቸው ውሳኔያቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚጥለው ይገልጻሉ።

አቶ ኤፍሬም ልጆቻቸው ከሚማሩበት ትምህርት ቤት አስተዳደር ጋር መነጋገራቸውን ቢገልጹም ወረርሽኙን በሚመለከት ማሻሻያ ሲያደርጉ አለመመልከታቸውን ይናገራሉ።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር የሰሙት ተማሪዎቹን ግምሽ ቀን ለማስተማር እቅድ መኖሩን እንደሆነ አስታውሰው፤ ነገር ግን የተማሪዎቹን ንክኪ ለመቀነስ እንዲሁም ንጽህናቸውን በመጠበቅ ስርጭቱን ለመከላከል ምን እንዳሰቡ አለማወቃቸውን ተናግረዋል።

የግል ንጽህና መጠበቂያ፣ የመምህራኑ ዝግጅት እንዲሁም ሌሎች ዝግጅቶችን ለወላጆች ማሳወቅ እንደሚገባ በመጥቀስ "ጥቅምት 30 ትምህርት እንደሚጀመር ተገልጿል፤ ከዚያ በፊት በአካል ሄጄ ዝግጅታቸውን አይቼ ነው ልጆቼን ለመላክ የምወስነው?" ሲሉ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

አቶ ኤፍሬም ልጆቸቸውን በሚያስተምሩባቸው ትምህርት ቤቶች የመምህራን እና የወላጆች ሕብረት መኖር አለመኖሩን እንደማያውቁ ተናግረው ሁሉም በግሉ አስተያየት ሲሰጥ ማስተዋላቸውን ገልፀዋል።

ነገር ግን ኮሮናን ለመከላከል ወላጆች ሰብሰብ ብለው መስራት እና ትምህርት ቤቱ ማሟላት ያለበትን ነገር እንዲያሟላ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው ይናገራሉ።

የማልድ ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Konjit Moges

በሚገባ ተዘጋጅተናል

ቆንጂት ሞገስ የማልድ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ስለ ትምህርት ቤታቸው ዝግጁነት ቢቢሲ ጠይቋቸው ሲያስረዱ በመዋዕለ ሕጻናቱና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ያደረጉት ዝግጅት እንደሚለያይ ገልፀዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ከማስመዝገባቸው በፊት መጠይቅ መበተናቸውን የሚገልፁት ቆንጂት፤ በዚህም ወላጆች ምን ምን መሟላት እንዳለበት ሃሳባቸውን መስጠታቸውን ይናገራሉ።

ትምህርት ቤታቸውን በፈረቃ መስራት እንደማያስፈልገው በመግለጽ፤ አዲስ ባለ ስድስት ፎቅ ሕንጻ ዘንድሮ በመከራየታቸው ከሌሎች የተሻለ እድል እንዳላቸው እና አንድ ተማሪ አንድ ወንበርና ጠረጴዛ እንዲኖረው በማድረግ እንዳዘጋጁ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ሲገቡ እጃቸውን የሚታጠቡባቸው መታጠቢያዎች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም ሠራተኞች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ንክኪን ለማስወገድ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚጠቀሙባቸው አልባሳትና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በትምህርት ቤቱ እንደተዘጋጀላቸው አመልክተዋል።

ይህም በተለይ የመዋዕለ ሕጻናት ተማሪዎች ከመምህራኖቻቸው ጋር እጅጉን የቀረበ ንክኪ ስላላቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ መምህራኖች ከትምህርት ቤቱ ውጪ የለበሷቸውን ልብሶች በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ላለመልበስ መወሰናቸውንም ገልፀዋል።

የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛም እንዲሁ እያንዳንዱ መምህር እንዲኖረው ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ የእጅ ንጽህናቸውን የሚጠብቁበት መታጠቢያም ቢሆን ከእጅ ንክኪ ነጻ እንዲሆን ማድረጋቸውንም ለቢቢሲ አብራርተዋል።

በአንድ ክፍል 15 ተማሪዎችን ብቻ እንደሚያስተምሩ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ ክፍሎቹም ሰፋፊ መሆናቸውና እንደልብ አየር መዘዋወር እንደሚችል ገልፀዋል።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ ተማሪዎች የሚጋሯቸው መማሪያዎችና መጫወቻዎችን ለመቀነስ ለእያንዳንዱ ተማሪ መማሪያ ቁሳቁሶቹን ማስቀመጫ የሚዘጋ ላስቲክ መዘጋጀቱን እንዲሁም መምህራኖቻቸው ንጽህና ማጽጃ በመጠቀም እንዲያፀዱ መመሪያ መስጠታቸውን ይናገራሉ።

ትምህርት ቤቱ የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚያሳዩ ተማሪዎች ካሉ በሚል ለልጆቹ የተለየ ለይቶ ማቆያ ክፍል ማዘጋጀቱን ጨምረው ገልፀዋል።

የማልድ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ቆንጂት እንደሚሉት ከሆነ ትምህርት ቢሮ ከሚያደርገው ክትትል ባሻገር ወላጆች በየጊዜው ልጆቻቸው የሚማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች እንዲከታተሉ ይጠይቃሉ።

ለዚህም እርሳቸው የበጎ ፈቃደኞች ወላጆችን እየመለመሉ መሆኑን ገልፀው፣ ይህ በየዕለቱ የትምህርት ቤቱን የኮቪድ-19 የመከላከል እንቅስቃሴን ለመከታተልና ክፍተት ካለም ለማረም እንደሚረዳቸው ገልፀዋል።