ኮሮናቫይረስ ፡ ልጆቻችንን ትምህርት ቤት ባንልካቸውስ?

ህጻናት እጃቸውን ሲታጠቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስኪ ስለ ተማሪዎች ከማውራታችን በፊት ስለ አስተማሪዎች በአጭሩ እናውራ።

መምህራን ከሌላው በላቀ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ናቸው? አጭሩ መልስ 'አይደሉም' ነው።

ይህንን በተመለከተ የእንግሊዝ የኅብረተሰብ ጤና ማዕከል ጥናት አድርጎ ነበር። ድምዳሜው አንድ አዲስ ነገር አለው።

መምህራን ከትምህርት ቤት ውጭ ወይም ከባልደረቦቻቸው በሚያደርጉት መስተጋብር እንጂ ከትንንሽ ተማሪዎቻቸው ጋር አብሮ በመሆን ቫይረሱን የመቀበል እድላቸው እጅግ አነስተኛ ነው።

በአጭሩ መምህራን ከልጆች ጋር እየዋልኩ ቫይረሱ ያዘኝ ቢሉ አይታመኑም።

እናም ጥናቱ በመጨረሻ መምህራንን ምን ይመክራል መሰላችሁ፤ ልጆች በቫይረሱ ይለክፉኛል ከምትሉ ይልቅ ራሳችሁን ከሌሎች ጠብቁ፤ ለምሳሌ ከባልደረቦቻችሁ።

ጥናቱ ዝም ብሎ ወደዚህ ድምዳሜ አልመጣም። ትንንሽ ልጆች በኮቪድ-19 የመያዝ፣ ተይዞ የመታመም እድላቸው በጣም አነስተኛ መሆኑ ስለተደረሰበት እንጂ።

አንዲት የመዋዕለ ሕጻናት መምህርት ከምታስተምራቸው ልጆች ቫይረሱ ሊይዛት የሚችለው በስንትና ስንት እጥፍ ከመምህራን ቢሮ፣ ወይም ከትምህርት ቤቱ ኮሪደር ወይም ወደ ትምህርት ቤት ከመጣችበት አውቶቡስ ሊይዛት የሚችልበት እድል ሰፊ ሆኖ ታይቷል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ለወረርሽኝ አደገኛ ቦታዎች፣ ወይም የወረርሽን መፈልፈያዎች አድርጎ አይፈርጃቸውም።

ነገር ግን ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ጠቃሚ መመርያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ቦታዎች እንደሆኑ ይታመናል፤ ለምሳሌ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ።

ልጆችን አራርቆ ክፍል ውስጥ ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል። ልጆችን አራርቆ ተጫወቱ ማለት ግን ይቻላል? ልጆችን ያን አትንኩ፣ ይህን አትንኩ እያሉ ማስቆምስ ይቻላል? ልጆች ለቁጥጥር ፈታኝ የሆኑ ፍጥረታት ናቸው። ለዚህም ነው ትምህርት ቤቶች ፈታኝ ቦታዎች የሚሆኑት።

መምህርና ተማሪዎች በክፍል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስ ለልጆች ምን ያህል አስጊ ነው?

ከሕጻናት እስከ አዳጊዎች ሁሉም የልጆች ዕድሜ ላይ ያሉ ለኮሮናቫይረስ የሚበገሩ አልሆኑም። ይህ መልካም ዜና ይመስላል።

ሊይዛቸው ቢችል እንኳ የመታመም እድላቸው አናሳ ሆኖ ተገኝቷል። ይሄም ጥሩ ዜና ነው።

ከልጆች ይልቅ አዋቂዎች በተለይም ጎልማሶችና ሽማግሌዎች ቫይረሱ በሚመርጠው ዕድሜ ላይ ያሉ ፍጡራን ናቸው።

ሽማግሌዎች ሌላ ተጨማሪ በሽታ ስለማያጣቸው ቫይረሱ ሲያገኛቸው አፈፍ አድርጎ ወደ ሞት ሊያደርሳቸው ይችላል።

የዩናይትድ ኪንግደም ዋናው የመንግሥት የጤና አማካሪ ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲ እንደሚሉት ሕጻናት በኮሮናቫይረስ ተይዘው የመሞት እድላቸው ሲበዛ ዝቅተኛ ነው።

ይህንን በስታትስቲክስ እንደግፈው ከተባለ በአገሪቱ የብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ በእንግሊዝና በዌልስ በመጋቢትና በሰኔ የሟቾችን ቁጥር የሰነደበትን ዶሴ ማየት ይበቃል።

የሟቾችን ዕድሜ ዘርዝሮ ያስቀምጣል። በሁለቱ ወራት ማለትም በመጋቢትና በሰኔ የሞቱ ሕጻናት ጠቅላላ ቁጥር 10 ብቻ ነው።

ከ20 ዓመት በላይ ያሉ ሟቾች ደግሞ እስከ ዛሬ 46 ሺህ 725 ደርሰዋል። ይህ የሚያሳየን የፕሮፌሰር ክሪስ ዊት ድምዳሜ ልክ መሆኑን ይሆን? ልጆች ለኮቪድ-19 እጅ የማይሰጡ ትንንሽ ጀግኖች ይሆኑ?

በሌላ ጊዜ ደግሞ በሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ 55ሺህ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ላይ ጥናት ተደርጎ ነበር። ከታማሚዎቹ ውስጥ ምን ያህሉ አደጋ ውስጥ ናቸው ብትባሉ ስንት ትላላችሁ? 10ሺህ?

ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የነበሩት ከ55ሺዎቹ 1 እጅ አይሞሉም፡፡ የ55ሺህ አንድ ፐርሰንት ስንት ነው?

አንዳንድ ልጆች ደግሞ አንዳንድ ምልክቶችን እያሳዩ መሆኑ የጤና ባለሙያዎችን እያነቃ መጣ።

ትንሽ ጉሮሯቸው አካባቢ የመከርከርና የካዋሳኪ ዓይነት የሕመም ምልክቶች የሚያሳዩ ልጆች በዝተው ነበር አንድ ሰሞን።

ካዋሳኪ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ላይ የሚታይ ምንነቱ የማይታወቅ ትኩሳትን የሚያበረታ በሽታ ነው።

ይህን ምልክት ልጆች እያሳዩ ያሉት ምናልባት የኮቪድ-19 ቫይረስ ተተናኩሏቸው ነገር ግን ሰውነታቸው ተከላክሎት ሲያበቃ የዚያ ግብግብ ርዝራዥ ዘግይቶ የሚያሳየው ምልክት ይሆናል በሚል የሕክምና ሰዎች ይህን ጠርጥረው ነገሩን አስፍተው መመራመር ጀምረዋል።

ህጻናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልጆች ቫይረሱን ያጋባሉ?

ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን እና ለንደን ስኩል ኦፍ ሐይጂን እና ትሮፒካል ሜዲስን ተባበሩና አንድ ጥናት አጠኑ። ጥናቱም ያው ከዚሁ ከቫይረሱና ከልጆች ጋር የተያያዘ ነው።

የደረሱበት ድምዳሜ ልጆች ከአዋቂዎች ይልቅ 50 እጅ በቫይረሱ የመያዝ ዕድል ብቻ እንዳላቸው ነው።

ይህ በሌላ ቋንቋ ምን ማለት ነው? የማስተላለፍ እድላቸውም በዚያው መጠን አናሳ ነው ማለት ነው።

ይህ የሁለቱ ዩኒቨርስቲዎች ጥናት በዓለም ላይ የተሰሩ 6ሺህ ምርምሮችን ፈትሿል። ነገር ግን 18ቱ ብቻ ጠንከር ያለ የጥናት መርህን የተከተለ ውጤት ሰንደው አግኝቷቸዋል። ከእነዚህ ወረቀቶች ተነስቶ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው።

ብቻ ወደ ሁሉም የጥናት ድምዳሜዎች ስንመለስ ሁሉም ጥናቶች ውጤት ያመላከተው ልጆች በአስተላላፊነትም፣ በታማሚነትም እዚህ ግባ የሚባል ስጋት እንደማይፈጥሩ ነው።

ሌላው በቫይረሱ የተያዙ ቤተሰቦች ላይ የተደረገ ምርመራም ነበረ። በቻይናና በፈረንሳይ።

ምርመራው ማጣራት የፈለገው የተያዙ ሰዎች ቫይረሱን መጀመሪያ ከማን ተቀበሉት ብሎ ምንጩን መፈተሸ ነበር። ከእነዚህ በአንድ ቦታ በድንገት ከተከሰቱ በርከት ያሉ ወረርሽኞች ውስጥ አንዱም ታዲያ ልጆች አልጀመሩትም።

የሁሉም ምንጭ አዋቂዎች ነበሩ።

ሌላም ምርምር ተደርጎ ነበር፤ በአይስላንድ፣ በደቡብ ኮሪያና በጣሊያን። ድምዳሜው አሁንም ሕጻናት በሽታውን በመቀበልም ሆነ በማቀበል፣ በመያዝም ሆነ በመታመም ዕድላቸው አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ግሎባል ቲም የተሰኘ የአጥኚዎች ቡድን ደግሞ ቫይረሱን በማስተላለፍ የሕጻናት ሚና ለጊዜው ግልጽ አይደለም ይላል።

ሆኖም ግን ቫይረሱን ወደ ቤተሰብ በማምጣትም ሆነ በቫይረሱ ተለክፎ አልጋ በመያዝ ሕጻናት በፍጹም አይታሙም።

የሆነስ ሆኖ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ባንልካቸውስ? ቢቀርባቸውስ?

ምንም እንኳ ልጆች በቫይረሱ የመያዝ፣ ተይዞ የማስያዝ፣ ተይዞ አልጋ የመያዝ ዕድላቸው ከአዋቂዎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም ለምን በትንሹም ቢሆን ተጋላጭ እናደርጋቸዋለን? ይህ የአብዛኛው ወላጅ ድምዳሜ ይመስላል።

የእንግሊዝ መንግሥት ዋናው የጤና አማካሪ ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲ ትንሽ ወጣ ያለ አተያይ አላቸው። ልጆች ትምህርት ቤት ባለመሄድ የበለጠ ይጎዳሉ ብለው ነው የሚያምኑት።

እንዴት?

ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ "ከተጋላጭነት ነጻ የሆነ ቦታና ሁኔታ የለም" ባይ ናቸው ፕሮፌሰሩ።

ስለዚህ የትምህርት ቤቶች ተመልሶ መከፈት ወላጆችም መምህራንም አምነውበት፣ ሙሉ ጥንቃቄ እያደረጉ ሊፈጸም የሚገባው ተግባር ነው ይላሉ።

ትምህርት ቤት ያልሄዱ ልጆች በሥነ ልቡና መጎዳታቸው አይቀርም፣ አእምሯዊ እድገታቸውን ይጎትተዋል፣ "ስለዚህ ቤት ማስቀረት አንዱ ጉዳት ቀንሶ ሌላ ጉዳት መጨመር ማለት ነው" ብለው ያምናሉ አማካሪው ፕሮፌሰር።

ትንንሽ ልጆች ቤት ከሚማሩት ይልቅ ትምህርት ቤት መማራቸው ከፍተኛ ልዩነትን ያመጣል።

የትምህርት ሂደቶች በጥንቃቄ መካሄድ ከቻሉ ለልጆች አደጋ አይሆኑም፤ አደጋው እንዲያውም ቤት ሲመለሱ ሥራ ውለው ከሚመለሱ ወላጆቻቸው ነው የሚጋረጥባቸው።

ይህ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ መሰረት ተደርጎ የተጻፈው የእንግሊዝን ትምህርት ቤቶች፣ የተማሪ ቁጥር፣ የተማሪ ቤት ስፋትና መሠረተ ልማትን ግምት ውስጥ አስገብቶና ተመርኩዞ ነው።

ሁኔታዎች ወደእኛ አገር ሲመጡ ፍጹም መልካቸው እንደሚቀይሩ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

ኮሮና
Banner